ይህ ጽሁፍ በወንድም ረታ ጳውሎስ የተጻፈ ነው፤ በጸሃፊው ፈቃድ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል፤
ክፍል 3
የእውነተኛ አምልኮ ሀ ሁ በክርስቶስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፈቃድ የተደረግነውን ምንነታችንን (ማንነትን) ከማወቅ እና በምድርም (በጊዜ እና በቦታ) በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ተገልጦ ከልባችን እስከ መላው ሰውነታችን የምር ለአምላካችን “የሚያደርገንን መሆን እንጂ የተለመደ የተሸመደደ ተግባርን መድገም” አይደለም። በክፍል 2 ያነሳሁትን የጉባኤ ዝማሬ ሁኔታ በደንብ ስናጤን ሊተርጂካል አዘማመር በወቅቱ ስሜታዊ መስተጋብርን በጣም የሚቃወም ነበረ። በሉተራን አዘማመር ስርአት እልልታ፣ ሽብሸባ፣ ጩኸት እና ሌሎች በነፍስ መነካት የሚንጸባረቁ ነገሮች እጅግ በጣም ክልክል ነበሩ። እኔ ራሴ በማስታውስበት ዘመን በቃለ ህይወት እና በመካነ ኢየሱስ እልልታ ጭብጨባ ሀሌሉያ ጩኸት ፉጨት (አሁንም) የተወገዙ ነበሩ በቃለ ህይወት የማስታውሰው በዓመት ሁለት ጊዜ እልልታ ይፈቀድ ነበረ፣ በጌታችን ልደት እና በትንሳኤው ቀናት ብቻ። እሱም ኮሚቴ ተዋቅሮ በጥንቃቄ ነው። ስንት ጊዜ እልል እንደሚባልም ተወስኖ ለጉባኤ ተነግሮ ነው። ከተባለው ቁጥር ያሳለፈ ቀጥታ ተይዞ ወደ ጸሎት ክፍል ተወስዶ አጋንንት ነው ተብሎ ይገሰጻል።
መዘምራን ቆመው ሲዘምሩ እንቅስቃሴ ፈጽሞ ክልክል ነበረ። የተንቀሳቀሰ ከ 4-6 ወር አገልግሎት ይቀጣ ነበር። አንድ ወንድም በአኮርዲዮን ኳየሩን እያጀበ አጨዋወቱን ቀየር አድርጎ እንደ እልልታ ሲያደርገው አንዱ የቤ/ክ መሪ አወቀበት፣ አኮርዲዮኑን እልል አስብለሀል ተብሎ ተጠርቶ ተገሰጸ ተቀጣ። ይገርማል! ይህንን የመሣሰሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ። የሚተኮረው እውነት ላይ እንጂ ስሜታዊ ነገሮች ላይ አልነበረም። የዚያን ጊዜ ክርስቲያን ብርቱ ፣ መንፈሳዊ የሚባለው መከራን ተቋቁሞ ወንጌል ሲሰብክ፣ በመከራ ሲጸና፣ በጸሎት ሲተጋ እንጂ በጣም እየዘለለ ሲዘምር ወይም አሜን ሀሌሉያ ሲል አይደለም።
ሆኖም በስሜታችን ጌታን ማክበር ምንም ጥርጥር የለውም ተገቢ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። መንፈስ እና ስሜት ግን ይለያያል፣ ለየቅል ነው! መንፈስ ቅዱስ ስሜታችንን ሊነካ ይችላል? አዎ በደንብ!! ወይ ሊያስለቅሰን፣ አልያም ሊያስቀን ሊያስደስተን ይችላል። ሙዚቃ እና ዝማሬስ ስሜታችንን ሊነካ ይችላል? በሚገባ! እንኳን መዝሙር ዓለማዊ ዘፈንም ስሜትን ይነካል። ስሜታችን በማንኛውም አርት (ኪነ ጥበብ) ለመነካት ቅርብ የሆነ የተፈጥሯችን ክፍል ነው። ታላላቅ ፈላስፎችም ” The purpose of Art is Emotional infection” ብለዋል። ሙዚቃ የሰውን ብቻ ሳይሆን የእንስሳትንም ስሜት ይነካል።
ለምሳሌ: – በአውሮፓ በተደረገ ጥናት የወተት ላሞች ክላሲካል ሙዚቃ ሲከፈትላቸው ወተታቸውን በጣም ይለቁታል። በጃዝ ሙዚቃም ዶሮዎች እንቁላል የመጣል ፍጥነታቸው ጨምሯል። ተክሎችም ለሙዚቃ ምላሽ በመስጠት አበቦቻቸው ሙዚቃ ወደአለበት አቅጣጫ ዞረው ተገኝተዋል። ለዚህ ነው የተቀላቀለብን፣ ጥንቃቄም የሚያስፈልገን። “መንፈስ” የምንለው ነገር መንፈስ ቅዱስን ይሁን የመዝሙሩን ከባቢ (Atmosphere) አንዳንዴ ግልጽ አይደለም።
መንፈስ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ አይደለም!
ለምሳሌ: ዛሬ የፓርላማው ስብሰባ መንፈስ ጥሩ ነበረ ስንል መንፈስ ቅዱስ ወይም መንፈስ እርኩስ ለማለት አይደለም። ከባቢው፣ አንድምታው፣ ሁናቴው ለማለት ነው መንፈሱ የምንለው በተለምዶ። በጉባኤ ዝማሬ ወቅትም መንፈሱ ጠፋ ወረደ ወይም የሚገርም መንፈስ ነበረ ስንል ብዙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እያመለከትን አለመሆኑን ልብ በሉ።
ይሁንና መንፈስ ቅዱስ ግን ከሥላሴ አንዱ የሆነው ራሱ እግዚአብሔር ነው፣ የሚገኘውም እውነት ውስጥ እንጂ ስሜት ውስጥ አይደለም። ስሜት እውነትን የምንገልጥበት መንገድ እንጂ በራሱ እውነት አይደለም። ከራሱ ፣ ስሜት ካለው ከእግዚአብሔር የተሠጠን ድንቅ ስጦታ ነው ስሜት። እውነተኛ አምልኮ ለሙዚቃ ግለት የሚሰጥ ምላሽ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቸርነት፣ ማዳን፣ ድንቅ ስራ እና ለማንነቱ ውበት በእውነት እና በመንፈስ የሚሰጥ ምላሽ ነው። ምላሽ ካለ አነሳሽ አለ ማለት ነው፣ አነሳሹ ራሱ ተመላኪው ጌታ ነው። አንድ ጊዜ ጋሽ ንጉሤ ቡልቻ እንዳለው እግዜር ያልጠቀሰው ሊያመልከው አይችልም። ጥቅሻ በሰዎች ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ራሱን የቻለ የተግባቦት መንገድ መሆኑ እሙን ነው።
ስናጠቃልለው ዝማሬ ስንዘምር ስሜት አልባ እንሁን እያልኩ ሳይሆን ስሜታችን እውነትን ሸፍኖ ከአምልኮ መግለጫነት ወደ ተመላኪነት ከፍ ሲል ይህ ከፍተኛ ውድቀት መሆኑ ይታወቅ ነው እያልኩ ያለሁት። የስሜት አምላኪዎች (Worshippers of their emotions) እየበዙ ነው!! ዝማሬ ከልብ ከሆነ ፣ ከምር ከመንፈስ ፣ በቃሉ ቅኝት ከሆነ ስሜታችን አምልኮን ለመግለጥ ወሳኝ ቅመም ነው! እንኳን እግዚአብሔርን ሰውንም ስንወድና ስናመሠግን ስሜትን ካልጨመርን ውበት የለውም።
Add Comment