አምልኮ/Worship

በዝማሬ አምልኮ ዙሪያ

Photo by Haley Rivera on Unsplash

በወንድም ለዓለም ጥላሁን (ላሊ) የተጻፈ በጸሃፊው ፈቃድ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል

በአምልኮ ጊዜ:
የምናመልከው (ምናልባት ባለማስተዋል) ራሳችን በምናባችን እንደመሰለን የሳልነውን “አምላክ” ሳይሆን ራሱን በቃሉና በመንፈሱ የገለጠውን ህያው እግዚአብሔርን መሆኑን እርግጠኞች እንሁን!! የዝማሬ አምልኮአችን ይዘትና ጥልቀት ጥራትና ፍሬያማነት እንዲለወጥ ከአምልኮ በፊት የምናደርገው ቅድመ ዝግጅት ወሳኝነት አለው- በቴክኒክ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ!!
የሚመለከው ማነው? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ስንመልስ የአምልኮአችን አቅጣጫ በትክክለኛው የልብ ቅኝት መገራቱ አይቀሬ ይሆናል!! መረሳት የሌለበት ቁምነገር ግን ዝግጅቱ የሚደረገው ቅዳሜ ማታ ወይም ዕሁድ ጠዋት ሳይሆን ከሰኞ እስከ ሰኞ ሊሆን የግድ መሆኑ ነው!! አምልኮ የሚያነጣጥረው በተመላኪው ላይ ብቻ ነው! ሁለት ተሞጋሾች ሁለት ተወዳሾች ሁለት ተደናቂዎች የሉም! ተመላኪው አንድና አንድ እርሱም “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ” ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው!!
አምልኮ በተመላኪው ስምና ዝና ላይ ተንጠላጥለን ለራሳችን አድናቆት የምናተርፍበት ሳይሆን በተመላኪው ፊት ሁለንተናችንን ዝቅ አድርገን በትህትና “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባኛል” የምንልበት መንፈሳዊ አሰራር ነው!!
1. አምልኮ በየዕለቱ ከተመላኪው ጋር የሚደረግ የቅርበት ግንኙነት የወለዳቸው የትናንሽ ደመናዎች ጥርቅም እንጂ ድንገት የፕሮግራም ቀን ሳይታሰብ የሚከሰት የበረከት ዝናብ አይደለም! በልባችን መሰዊያ ላይ እንደበራ የሚቀጥል የየዕለት የህይወት ዘይቤ እንጂ የፕሮግራም ለት ክስተት አይደለም!
2. በአምልኮ ሰዓት
መዝሙሩና ሙዚቃው ከመቃኘቱ በፊት ልብ መቃኘት አለበት! ሙዚቃው የመዝሙሩን ዜማ ሳይጀምር በፊት የአምላኪው ልብ በራሱ ዜማና melody አምልኮ መጀመር መልመድ ይኖርበታል! ምክኒያቱም እግዚአብሔር አስቀድሞ የልባችንን ዕጣን ሳያሸት የዝማሬያችንን ዕጣን አያሸትምና!!
3. ሳያዩ ማምለክ ስለማይቻል ለማምለክ መገለጥ ይጠይቃል! እግዚአብሔር በዚህ ሳምንት ስለራሱ ምን ገለጠልን? ምን በራልን ነፍሳችን ምን ተረዳች? ምን አወቀች?
የሚገርመው ነገር አንድ ጠብታ መገለጥ አንድ አገር አምልኮ ይወልዳል! ከብዙ መዝሙር ይልቅ በመገለጥና በጥልቅ መረዳት የተዘመረ አንድ ወይም ጥቂት መዝሙር ረጅም መንገድ ያስኬደናል! በአንፃሩ ደግሞ በዛሬ ዓመቱ መገለጥ ብቻ ብዙ ርቀት መሄድ አስቸጋሪ ሆኖ እናገኘዋለን!
4. አምልኮ ስጦታ ይዞ መቅረቢያ ሳይሆን ራስን ስጦታ አድርጎ ማቅረቢያ ነው!
ለዚህ ነው: “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ህያው ቅዱስም መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ….እለምናችሁዋለሁ” ብሎ ሃዋርያው ጳውሎስ በአፅንዖት የሚያሳስበን (ሮሜ 12:1)
5. አምልኮ የሰውን ሁለንተና ይጠይቃል! ከላይ ያለው ጥቅስ “ሰውነታችሁን” ሲለን ስጋችሁን ማለቱ አይደለም! ሁለንተናችሁን አቅርቡ እያለን ነው – ስሜትን ፈቃድን ሃሳብን ነፍስን ስጋንና መንፈስን!!