ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮት እና መጽሐፍ ቅዱስ

  የመንጋ ብቻ አስደሳች ሰው መልክ

ሳኦልም፥ ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን አለው። ፩ሳሙ. ፲፭፥፲፭
ሰሎሞንም … አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና። ፪ዜና ፩፥፲
ያንን የለመኑትንም፥ ስለ ሁከት ሰውንም ስለ መግደል በወኅኒ ታስሮ የነበረውን አስፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው። ሉቃ. ፳፫፥፳፭

በዘመናችን ሰዎችን ለማስደሰት ሲሉ ከመስመራቸው ወጥተው የሚሄዱ ብዙ አገልጋዮች አሉ። ይህን የሚያደርጉት ከሥጋ አንጻር ከታየ ወይ ብዙ ቁጥር በማስመዝገብ ለዝናና ለመታወቅ ነው፤ ወይም የንዋይ ምንጫቸውን መደብ ለማስፋት ነው። ከሰይጣናዊ አሠራር አንጻር ሲታይ ደግሞ ይህ ሌላ ክርስቶስና ልዩ ወንጌል ነው። ዋጋ ስለማይጠይቅም ለብዙዎች ሥጋዊና ዓለማዊ አመላለስ የሚመች ስለሆነ የሚሳቡ ጥቂት አይሆኑም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መሳይ ሌላ ክርስቶስና ልዩ ወንጌል ወደተቀበሉ የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት ሲጽፍ የሰዎች አስደሳች ስላለመሆኑ እንዲህ አለ፥ ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም፥  ገላ. 1፥10።

በዚህ ዘመን ሰውንና የሰዎችን ምኞት ለመመገብ ታጥቀው ተሰናድተው የቆሙ ‘አገልጋዮች’ እልፍ ናቸው። ሰዎችን የሚያስደስታቸው ምን እንደሆነ አጥብቀው ያጠናሉ። እና ያንን ያቀርቡላቸዋል። የሚያቀርቡት ብቻ ሳይሆን አቀራረባቸውም ማራኪ ነው፤ ይስባል። የሰውን መንፈስ ሳይሆን ስሜት የሚያገለግሉ ከታወቀ የመንፈሳዊ ሆቴሎችና ቱሪዝም ተቋም በማዕረግ የተመረቁ ይመስላሉ።ዘልቀን ስናጤናቸው እነዚህ ሰዎች ለሰዎች  በስሱ   የሚገድዳቸው ይመስላሉ። ይሁን እንጂ የሚያገለግሉአቸውን  ሰዎች መጠቀሚያና መኖሪያ የሚያደርጉ መሰሪ መሪዎች ናቸው። ትንቢት ሲናገሩ ለነገ ሳያስቀሩ የበረከት ናዳ ዘንቦ እንደማያባራ፥ ተዝቆ እንደማያልቅ ዛሬውኑ እንደሚወርድ የሚያውጁ ናቸው። የነዚህን ሰዎች ሕዝባዊ ሰውነትና ሰዎችን ለማስደሰት ያሚጓዙትን ረጅም ጎዳና ለማወቅ እንዲረዱን በመጀመሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቂት ምሳሌዎችን እንድንመለከት እወዳለሁ። የመጀመሪያው የሕዝብ ሰው ንጉሥ ሰሎሞን፥ ሁለተኛው ንጉሥ ሳኦል፥ ሦስተኛው ጲላጦስ ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን የታወቀና የተወደደ የእስራኤል ንጉሥ ነው። እጅግ የሚታወቀው በጠቢብነቱ፥ በዓለማዊነቱ፥ በተመራማሪነቱ ነው። በአባቱ በዳዊት አልወጣም። ከእርሱ ቀጥሎ የነገሠው ልጁ ሮብዓምም በእርሱ አልወጣም። የወረሰውም ያወረሰውም ነዋሪ ባህርይ አልነበረውም። ሰሎሞን በሰዎች የተፈለገና የተወደደ መሪ ነው። ጥበቡ ሕዝብን በእጅጉ ያስደመመ፥ ዝናው የወጣ፥ አገር አቋርጠው ሊሰሙት የሚፈልጉት ሰው ነው። እስራኤል በታሪካቸው ንጉሥ ነግሦላቸው ተደላድለው መኖር የቅርብ ታሪካቸው ነውና ሰሎሞን ገና ሦስተኛ ንጉሣቸው ብቻ ሳይሆን ብርቅ ሰው ነው። ሰሎሞን የእግዚአብሔር ሰው ሳይሆን የሰዎች ሰውም ነው። ይህንን እውነት ከሦስት ነገሮች አንጻር እንድንመለከት እወዳለሁ።

  1. ጥበብ መሻቱ

ሰሎሞን የታወቀው በጀግንነቱ ወይም እግዚአብሔርን ፈጽሞ በመከተሉ አልነበረም። ሰሎሞን በመጽሐፍ ቅዱስም በዓለማውያን መጻሕፍትም ሳይቀር የታወቀው በጥበቡ ነው። ሰሎሞን ለጥበብ ጸልዮ ጥበብን ከእግዚአብሔር እንደተቀበለ እናውቃለን። ለሰሎሞን ጥበብን የተመኘና የጸለየ ሌላ ሰው እንደነበረ ግን አስበን እናውቃለን? አባቱ ዳዊት ጸልዮለት ነበር። ይህ ዳዊት ሰሎሞንን የመረቀበት ምርቃት ጥበብን ለጥበብነቱ ብቻ እንዲያገኝ ሳይሆን በምክንያት ነበረ። ብቻ የአምላክህን ይህን ነበር ያለው፥  የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሠ ጥንህ፤ 1ዜና 22፥12።

ዳዊት ሰሎሞን ጥበብና ማስተዋል እንዲኖረው የተመኘው የአምላኩን የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቅ ዘንድ ነው። ዳዊት እግዚአብሔርን የሚወድና በሚወስዳቸው እርምጃዎቹ እግዚአብሔርን የሚጠይቅ ሰው መሆኑ ከታሪኩ ይታያል። እግዚአብሔርን ባለመጠየቅ ወይም ባለመስማት የሳተባቸው ጊዜዎችም አሉ። ምልስ የሆነ ሰው ነውና ቶሎ ይመለሳል። ለልጁ የተመኘው እርሱ እንደሆነው እየወደቀ እየተነሣ እንዲያገለግለው ሳይሆን ሕጉን እየጠበቀ እንዲኖር ነው። ስለዚህ ይህን ሕግ ይጠብቅ ዘንድ ጥበብና ማስተዋል እንዲያገኝ ጸለየለት።ንጉሡ ሰሎሞንም ለጥበብ ጸልዮአል። የራሱ ጸሎት ግብ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። እንዲህ ጸለየ፥ አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና 2ዜና 1፥10፤ 1ነገ. 3፥9። የአባትና የልጁን ቃል ስናስተውል (የተሰመረበትን ሐረግ ልብ ይሏል) የዳዊት ለልጁ ጥበብን መሻቱ በእግዚአብሔር ሕግ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ሲሆን የሰሎሞን ግን ሕዝብ ተኮር ነው። በሕዝቡ ፊት ይወጣና ይገባ ዘንድ ጥበብን ለመነ። ሕዝቡን ታላቅ አድርጎ አየ። እርግጥ ነው ሕዝቡ ታላቅ ነው፤ ታላቅነቱ ግን ከሕዝቡ ከራሱ የተነሣ ሳይሆን ከሕዝቡ አምላክ የተነሣ ነው። ስለዚህ ትኩረቱ በሕዝቡ ሳይሆን ሕዝቡን ሕዝብ ባደረገው አምላክ ላይ መሆን ነበረበት።

ከላይ እንዳየነው ጸሎቱ ጥበብ ይሁን እንጂ የጥበቡ ዓላማ እግዚአብሔርን ለማክበር አልነበረም። ከሰሎሞን ሕይወትና ዘመን ውስጥ አምልኮና ወደ እግዚአብሔር የቀረበ አረማመድ የምናየው ቤተ መቅደሱ በተሠራባቸው ዓመታት እና አልቆ ሲመረቅ ነው። ምናልባት የሰሎሞን መንፈሳዊ ሕይወት የጦዘበት ጊዜ መቼ ነው ቢባል ቤተ መቅደሱ በተመረቀ ቀን ነው። በዚህም ሁሉ በሥራው ወቅት ባተሌ ከመሆኑ በቀር በሕይወቱ አምልኮ የሚታይበት ሰው አልነበረም። የምረቃ ቀን ቋንቋውም ለአንድ አገር መሪ የሚናገረው ተጽፎ እንደተሰጠው የሚመስል ፍጹም መንፈሳዊ ቋንቋ ነው።  የተለማመደውና የሸመደደው ነገር ይሆን? ወይስ በመጀመሪያ በመልካም ይሮጥ ነበር? ሕይወቱ በጠቅላላው ሲታይ ያን የመሰለ ጸሎትና የቡራኬ ቃል ከሰሎሞን መውጣቱ ያስደንቃል።  ከቤተ መቅደሱ ምረቃ በኋላ የሰሎሞን መንፈሳዊ ሕይወት መደብዘዝ ሳይሆን ጨርሶ አይታይም።

ከተሞችን ሲያጠነክርና ምሽጎችን ሲሠራ፥ የፈረሶችና የሠረገሎች ከተሞችን ሲከትም፥ የጎረቤት መንግሥታትን ገባሮች ሲያደርግ፥ የመርከብ ንግድ ሲያስፋፋ፥ ከመንግሥታት ጋር ጋብቻ ሲሆን፥ ሚስቶችና ቁባቶቹ አንድ ሺህ መሆናቸው፥ ጥበቡን ለመስማት ሰዎች አገር አቋርጠው ሲጓዙ፥ እንደ መክብብ ያለ ስብከት ሲሰብክ፥ ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ሲመስል፥ እንደ መኃልየ መኃልይ የመሰሉ ሺህ አምስት መዝሙራት ሲደርስ (1ነገ. 4፥32) ነው የሚታየው። በአጠቃላይ ሲታይ መንፈሳዊ ሳይሆን የጥበብ፥ የፍልስፍና፥ የፖለቲካ ምሑርና ሊቅ ሆኖ ይታያል።

ጥበብን ጠይቆ ነበርና ጥበብ ተሰጠው።
ጥበቡንም ለጠየቀው ዓላማ አዋለው።
የሕዝብ ሰው ሆነና ለሕዝብ አዋለው።
አሕዛብም  ፈለጉት፤  ወደ
እግዚአብሔር ግን አልመራበትም። የሰሎሞንን ሕይወት ዘመኑንም
ስንመረምር የእግዚአብሔር ሰው ሳይሆን የሕዝብ ሰው ሆኖ ኖረ።

የዘመናችን የሕዝብ ሰዎችም ለእግዚአብሔር ሳይሆን እውቀትና ጥበብን ለሰው የሚያውሉ ናቸው። ለሰው አእምሮ የሚመችን፥ ለጆሮ የሚጥምን፥ ፍልስፍና የሚመስልን፥ መብል ያቀርባሉ። ይህ የማይታኘክ፥ የማይቆረጠም፥ ጣፋጭ መብል ነው። ጣፋጭ መብል እንደምናውቀው ጥርስ ያበላሻል፤ እና ጥርሱ የተበላሸ ሰው ጠንካራ መብል መብላት አይችልም። ጣፋጭ በማቅረብ ጠንካራ መብል የማይበላ ብቻ ሳይሆን መናከስም የማይችል ጥርስ የለሽ ድዳም ነው እያደረጉ ያሉት።

  1. ገንዘብ መውደዱ

የሕዝብ ሰዎች ለጊዜው ሕዝብን ሸንግለውና ደልለው እንጀራ ያቀርባሉ። ግን እንጀራው የሕልም እንጀራ ነው። የበረከት፥ የድሎት፥ የምቾት፥ የአዱኛና ምድራዊ ብልጽግና፥ የጤንነትና የረጅም ዕድሜን ጥጋብ፥ የሰላምና መረጋጋትን፥ የስደትና መከራን መራቅ እና ወዘተ። ማንም አማካይ ሰው እነዚህን በረከቶች ይፈልጋቸዋል፤ ችግሩ እነዚህ ነገሮች የስኬታማ ክርስትና ምልክት ሆነው ሲደነገጉ ነው። በተለይ ገንዘብን የስኬት ትልቁ ምልክት አድርገው በደማቁ የሚስሉ ዘመነኞች ሰባኪዎች ቀንበር በተከታዮቻቸው ላይ እየጫኑ መሆናቸውን ይደብቃሉ። ይህን የሚሉት ለመንጋው ሳስተው ሳይሆን መንጋውን አስደስተውና ጉም እያስዘገኑ እኪሳቸውና እመቀነታቸው ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ልቡናቸው ያውቀዋል።

ንጉሥ ሰሎሞን እግዚአብሔር መጀመሪያ በሕልም በተገለጠለትና ምን እንዲሰጠው በጠየቀው ጊዜ ካልጠየቃቸው ነገሮች አንዱና ስላልጠየቀ እንደ ምርቃት ሆኖ እንደሚያገኘው ተስፋ የተሰጠው ባለጠግነት ነበር፤ 1ነገ. 3፥11 እና 13። ይህ ተስፋ ተፈጽሞአል። ሰሎሞን እግዚአብሔርን ፈጽሞ ቢከተል ኖሮ ይህ ተስፋ ያለ ችግር ይፈጸም ነበር። ነገር ግን የተፈጸመበት ሁኔታ፥ ማለትም፥ ሰሎሞን የከበረበት መንገድ የገዛ ሕዝቡን በማስጨነቅም ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን ገንዘብን የሚወድ ንጉሥ ነበረ። በዘመኑ ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ ማድረጉ በ1ነገ. 10፥27 ተጽፎአል፤ ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። ይላል። ይህ ብር ከብር ማዕድን ተቆፍሮ የወጣ ነው? ይመስለናል፤ ግን አይደለም። እርግጥ በስጦታ የሚመጣለት ብዙ ገጸ በረከት ነበረ፤ ነገር ግን ከምጣኔ ሀብቱና ከወጪዎቹ አንዱን ብቻ፥ የፈረሰኛ ሠራዊቱን መነሻና የፈረሶችና ሠረገሎች ስብስቡን ሂሣብ ብናሰላ በ1ነገ. 10፥26-29 1400 ሠረገሎች እና 12 ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት ይላል። ከግብጽ የሚገዛው የአንዱ ፈረስ ዋጋ 150 ሰቅል ነውና ወደ 2 ሚሊዮን ሰቅል ይጠጋል። ሠረገላው አንዱ 600 ነውና ወደ አንድ ሚሊዮን ይጠጋል። ይህ የባልደራሶቹ ብቻ በጀት መሆኑ ነውና ከገንቦው ጠብታው ነው። ይህ ወጪ ከየት መጣ? ይህ ብርን የሚወድድ ንጉሥ ራሱ ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፍ፥ ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አለ፤ መክ. 5፥10። ኑሮው የተንደላቀቀ መሆኑንም በዚያው መጽሐፍ ጽፎአል። የዚያ ሁሉ ወጪ ከየት የተገኘ ነው?ሕይወቱን ጠልቀን ስንመረምረው ከዚህ ፍቅረ ንዋይ የተነሣ ሰሎሞን ለሕዝቡም የተመቸ አልነበረም። አለመሆኑን የምናውቀው ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ልጁ ሮብዓም ነግሦ ሳለ እስራኤል ካቀረቡለት ልመና ነው። ኢዮርብዓምን የሚጨምረው የሕዝቡ ልዑካን ቡድን የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምን፥አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት ይላል፤ 1ነገ. 12፥4። ይህ በግልጽ የሚያመለክተው በሰሎሞን ዘመን ሕዝቡ ቀንበር የከበደውና በጽኑ አገዛዝ ስር የሚማቅቅ እንደነበረ ነው። ሰሎሞን የሕዝብ ሰው ሆኖ ሳለ የገዛ ሕዝቡን ግን አስጨንቆ ያኖረ፥ ጨቁኖ የገዛ ንጉሥ ነበረ። ቤተ መቅደሱም፥ ቤተ መንግሥቱም ተሠርተው ተጠናቅቀዋል። ቀንበሩ ግን ከሕዝቡ ጫንቃ ሳይወርድ ኖረ። ልጁም በአባቱ ወጥቶ ለሕዝቡ ደንታቢስ በመሆኑ ለእስራኤል መከፈል ዋናና መነሻ ምክንያት ሆነ።

ሰሎሞን ስለ ብልጽግና መስበክ ይችላል። እግዚአብሔር ያበለጽጋል ብሎ መናገርም ይችላል። ቢያስፈልግ የደለበ ንብረቱን ለዚህ ምስክር አድርጎ ሊጠራ ይችላል። ግን የገንዘቡ ምንጭ ከላይ እንዳየነው ቀንበር የከበደው ሰፊ ሕዝብ ነበረ። የዘመናችን ሕዝብ አደሳሳቾች፥ በተለይም ስለ ብርና ብልጽግና የሚሰብኩቱ የእግዚአብሔርን ቃል ትተው ለአድማጭ ጆሮ የሚመች ነገር የሚቀባጥሩት ለሕዝቡ በረከት ተመኝተው ሳይሆን አድማጮቻቸው ጆሮ ስር ያለው ትከሻቸው ላይ ተንፈላስሰው ሊያናጥሩ ስለሚወድዱ ብቻ ነው። ብዙዎቹ እንደ ሰሎሞን ባይሆኑም ባለጠጎች ናቸው። እንደ እርሱ ብርን የሚወዱ፥ ብርን የማይጠግቡም ናቸው። ብልጥግናቸው በራሱ ክፋት የለበትም። ክፋት የሚኖረው ግን ተሰባክያኑ ‘ትበለጽጋላችሁና ለዚህ አገልግሎት ስጡ’ የሚባል ቀንበር የሚጫንባቸው ሲሆን ነው። እንግዲህ እነዚህ ሰባኪዎች ሰዎች የሚያስደስቱ የሕዝብ ሰዎች ሆኑ እንጂ በአንክሮ ሲታዩ የሕዝብ ሳይሆኑ የራሳቸው ሰዎች ናቸው። ሕዝብን የሚያስደስቱት ለሕዝቡ ሳይሆን ለራሳቸው መኖሪያ ብለው ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአሜሪካ ውስጥ አንድ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የስድስት ክርስቲያናዊ ድርጅቶች የገንዘብ አያያዝና አወጣጥ ተጠርጣሪ ነውና ይፈተሽ ብሎ ኮሚቴ ተሰይሞ ነበር። ምርመራው የስድስቱንም ዋና መሪዎች እጅግ አስደንግጦ ነበር። ሁለቱ እንዲያውም በግልጽ ተቃውመው ይህ እኛን መመርመር የIRS፥ ማለትም፥ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት ሥራ ነው እንጂ የሴኔት ኮሚቴው ተግባር አይደለም ብለው ተናግረው ነበር። በመጨረሻው ውጤት የተጠርጣሪዎቹ ክሳቸው ቢሰረዝም ኪሳቸው እንደደለበ ነው የቀረው። የምርመራው ሂደት የአንዳንዶቹን የገንዘብ አያያዝና አወጣጥ በትንሹም ቢሆን ወደ አደባባይ አውጥቶአል። የአንዳንዶቹ ንብረትና የባንክ ደብተር ከአንድ አናሳ መንግሥት ጋር የሚወዳደር ነው።yehezb sew 4

የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች የገንዘብ    በረከት    መደበኛ የስብከታቸው  ርእስ  ነው። ዋናው  እንደ  አዝማች የሚደጋገመው  ሐረግ አድማጮቻቸው እግዚአብሔር በገንዘብ እንዲባርካቸው ከፈለጉ ገንዘባቸውን   መስጠት እንዳለባቸው ነው። የሚሰጡትም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ለሰባኪዎቹ ነው። እርግጥ፥ እግዚአብሔር የሚባርክ አምላክ ነው፤ የተባረከው ሕዝቡ ደግሞ በመስጠት እንዲባርክና በረከትን እንዲለማመድ ፈቃዱም ትእዛዙም ነው። ከመቀበል መስጠት ብጽዕና ነው። ግን የምንሰጠው ለማን መሆኑን እና ለምን መሆኑን ማወቅ አለብን። የምንሰጠው ለእግዚአብሔር ነው። ዋናዋ ይህን ስጦታ የምንከትትባት ጎተራም ቤተ ክርስቲያን ናት። የምናመልክባት፥ የምናገለግላትና የምንገለገልባት ቤተ ክርስቲያን። የምንሰጠውም በረከትን ስለተቀበልን ነው እንጂ ትርፍን ለመቀበል አይደለም። ከሆነ ግንኙነታችንን ያበላሸዋል። አምልኮ መሆኑ ቀርቶ የንግድና የትርፍ ሽርክና ይሆናል። ገንዘብም አምላክ ይሆናል።

  1. አምልኮው

ገንዘብን ትተን ወደ አምልኮ ስንመጣም ተመሳሳይ ነው። ለሕዝብ ሰው ሕዝቡ ከተደሰተ እግዚአብሔር ባይደሰትም ምንም አይደለም። የሕዝብ ሰው ራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የሌለው ሕዝብንም ከእግዚአብሔር ጋር የማያገናኝ ሰው ነው። ለአማልክት መስገድና ጣዖት አምልኮ የንጉሥ ሰሎሞን ሁለተኛ መታወቂያው ነው። 1ነገ. 11፥5-10 ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥ ተከተለ። ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፥ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም። በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ። ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ። ይላል። ይህ መንፈሳዊ መልኩ ነው። ለንጉሥ ሰሎሞን ሚስቶቹ ከተደሰቱ፥ የሲዶና፥ የአሞን፥ የሞዓብ አማልክትና ሕዝቡ ሁሉ ከተደሰተ እግዚአብሔር ባይመለክም ምንም አልነበረም። በእግዚአብሔር ፈንታ ሌሎች ግዑዛንና ርኩሳን ጣዖታት ቢመለኩ ምንም አይደለም።

የእግዚአብሔርን ቦታ ለመውሰድ ወረፋ ሊይዙ፥ ተራ ሊጠብቁ የሚያቆበቁቡ ብዙ አሉ። ቀደም ሲል እንዳየን ገንዘብ አምላክ ይሆናል። ሆድም አምላክ ይሆናል። አምላክ ሲባል እንደ ጣዖት ተክለን ወይ ገትረን የምንሰግድለት ብቻ ሳይሆን በኛና በእግዚአብሔር መካከል የሚገባ ማናቸውም ነገር ነው። ለእርሱ የምንሰጠውን ወይም ራሳችን የተሰጠን የምንሆንበትን ማናቸውንም ነገር የሚቀንስ ወይም የሚያስቀር ከሆነ አምልኮአችንን እየተገዳደረ ነው። የሕዝብ ሰዎች በሚያገለግሉአቸው ወገኖች ሕይወት ውስጥ ይህን ጣዖት ሲያዩ ውስጣቸው አይቆጣም። ለእግዚአብሔር ትራፊውና ውራጁ እንደሚበቃው ያስባሉ። ስሕተታቸው ይህ እንደሚበቃው ማሰባቸው ሳይሆን ይህ እንደተገባው መቁጠራቸው ነው። ሰሎሞን በአንድ ጀንበር ወይም በአንድ ሌት አልወደቀም። ሌሎችን አማልክት እንዳይከተል በግልጽ ተነግሮታል፤ 1ነገ. 11፥9-10። እግዚአብሔር ሰሎሞንን ይህን ያዘዘው በግልጽ ነበር፤ 1ነገ. 9፥6-9 ይህን ይነግረናል። ሌሎችን ሊያስደስት ብሎ ከአምላኩ ልቡን አራቀ፤ ተለየ። መርገምን፥ መተረቻ መሆንን፥ የሕዝቡንና ከፍ ብሎ የነበረውን ስፍራ መዋረድን አስከተለ። ፍጻሜው እንደ አጀማመሩ አላማረም። የሕዝብ ሰው ነውና::