ጥያቄዎቻችሁ

እግዚአብሔር ይጸጸታልን?

መጽሐፍ ቅዱስ ከ10 ጊዜያት በላይ እንደተጸጸተ ይናገራል። እነዚህን ጥቅሶች ስናነብብ ይህን እናገኛለን።

ዘፍ. 6፥6-7 እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፦ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ።

1ሳሙ. 15፥10-11 እና 35 የእግዚአብሔርም ቃል፦ ሳኦል እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቈጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። . . . ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ወጣ፦ ሳሙኤልም እስከ ሞተበት ቀን ድረስ ሳኦልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም፥ ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ።

1ዜና 21፥15፤ እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተጸጸተ፥ የሚያጠፋውንም መልአክ፦ በቃህ አሁን እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

መዝ. 106፥45፤ ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ።

ኤር. 18፥8፥10፤ ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ፥ እኔ አደርግለት ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ።

ኤር. 42፥10፤ ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።

ኢዩ. 2፥13-14፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቍርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?

አሞ. 7፥3፥6፤ እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር። . . . እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ዮና. 3:9-10፤ 4፥2፤ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም። . . . ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና፦ አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።

መጸጸት ለሰው ሲሆን ስሕተትን፥ መመለስን፥ መታረምን ያሳያል። እግዚአብሔር ተጸጸተ ሲባል እግዚአብሔር ተሳስቶ ነበር፥ እርማት አስፈልጎት ነበር ማለት ነው? ይህ ከሆነ እግዚአብሔር ይስታል ወይም ይሳሳታል ማለት ነው። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ጥቅሶች እግዚአብሔር አይጸጸትም ይላሉ። ለምሳሌ፥ ዘኁ. 23፥19፤ 1ሳሙ. 15፥29፤ መዝ. 110፥4፤ 132፥11፤ ኤር. 4፥28፤ 20፥16፤ ሕዝ. 24፥14፤ ዘካ. 8፥14፤ ሮሜ 11፥29፤ ዕብ. 7፥20-21። እነዚህ ጥቅሶች በግልጽ እግዚአብሔር አይጸጸትም ይላሉ። ስለዚህ ቃሉ እርስ በርሱ ይጋጫል ማለት ነው? ወይስ እውነት እግዚአብሔር ይጸጸታል?

መጸጸት ማለት ለሰው ሲነገር መሳሳትን ማስተዋል፥ ትክክል እንዳልሆኑ ወይም እንዳላደረጉ ማወቅ፥ መቆጨት፥ ከስሕተት መመለስ  ማለት ነው። መጸጸት ለእግዚአብሔር ከተነገረና በተመሳሳይ ትርጉም ካገናዘብነው እግዚአብሔርነቱን ያዋርዳል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍጹም ነው። ሁሉን አዋቂም ነው። ስለዚህም ሰው በሚሳሳትበት መንገድ ሊሳሳት ከቶም አይታሰብምና አይጸጸትም።

እግዚአብሔር ተጸጸተ ሲባል መታረሙን ወይም ራሱን ማረሙን ማሳየቱ ነው? አይደለም። እዚህ ጸጸት የተባለው ቃል נָחַם (ናኻም) የሚል ነው። ቃሉ እህህ! ማለት ማዘን፥ መራራት ማለት ነው። በብዙ ጥቅሶች መጽናናት እና ማጽናናት የተባለው ቃል ይህ ነው። ናሆም፥ ነህምያ፥ ኑሐሚን የሚባሉት ስሞች ምንጫቸው ይህ ቃል ነው። በበርካታ ጥቅሶች ውስጥም ቃሉ ማጽናናት ወይም መጽናናት እየተባለ ተጠቅሶአል፤ ለምሳሌ፥ ዘፍ. 37፥35፤ ሩት 2፥13፤ ኢሳ. 12፥1፤ 61፥2፤ ወዘተ። መጽናናት ወይም ማጽናናት እንደምናውቀው ከኀዘን ጋር የተቆራኘ ቃል ነው። ተጸጸተ የሚለው ቃል ከላይ እንዳየነው መሳሳት ሳይሆን ማዘን ወይም መራራት መሆኑን ለማየት ጥቂት በዚህ ትርጉም የተጠቀሱትን የዚህን ተመሳሳይ ቃል נָחַם (ናኻም) አጠቃቀሶች እንመልከት።

ዘጸ. 32፥12 እና 14፤ ግብፃውያንስ፦ በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።

ኢሳ. 49፥13፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፥ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፥ እልል በሉ።

በነዚህ ጥቅሶች መራራት የሚለው ቃል እና ቀደም ሲል ያየነው ተጸጸተ የሚለው አንድ ናቸው።

ዘዳ. 32፥36፤ ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥ የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል።

መሳ. 2፥18፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበርና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው።

2ሳሙ. 24፥16፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ኢየሩሳሌምን ያጠፋት ዘንድ እጁን በዘረጋ ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ክፉው ነገር አዘነ፥ ሕዝቡንም የሚያጠፋውን መልአክ፦ እንግዲህ በቃህ እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ነበረ። ይኸው ታሪክ በተጻፈበት ሌላ ስፍራ፥ በ1ዜና 21፥15፤ እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተጸጸተ፥ የሚያጠፋውንም መልአክ፦ በቃህ አሁን እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። በ2ሳሙ. 24፥16 አዘነ የተባለው ተመሳሳይ ቃል ነውና በ1ዜና 21፥15 ተጸጸተ ተብሎአል።

በእነዚህ ጥቅሶች ያለው ማዘን የሚለው ቃል እና ተጸጸተ የሚለው አንድ ናቸው።

ኤር. 15፥6፤ አንቺ እኔን ጥለሻል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጥፍቼሻለሁ፤ ከይቅርታ ደክሜአለሁ።

ይቅርታ የሚለው ቃል እና ተጸጸተ አንድ ናቸው።

ኤር. 26፥3፥13፤ 26፥19፤ ምናልባት ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ። . . . አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። . . . በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተውምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።

እዚህ መተው የተባለው ከመጸጸት ጋር አንድ ቃል ነው።

ሲጠቃለል፥ መጸጸት ማለት ለሰው ሲነገር መሳሳትን ማስተዋል፥ ትክክል እንዳልሆኑ ወይም እንዳላደረጉ ማወቅ፥ ከስሕተት ለመምመለስ ብሎ መቆጨት ማለት ነው። መጸጸት ለእግዚአብሔር ከተነገረና በተመሳሳይ ትርጉም ካገናዘብነው እግዚአብሔርነቱን ያዋርዳል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍጹም አይደለም ያሰኛል። እግዚአብሔር ግን ፍጹም አምላክ ነው። ሁሉን አዋቂም ነው። ስለዚህም ሰው በሚሳሳትበት መንገድ ሊሳሳት ከቶም አይታሰብምና አይጸጸትም። ነገር ግን ያዝናል፤ ይራራል፤ ይቅር ይላል፤ ይተዋል። ይህ ማዘን፥ መራራት፥ ይቅር ማለት፥ እና መተው ነው በአማርኛ መጸጸት የተባለው።

ዘ. መ.