ቤተ ክርስቲያን አምልኮ/Worship

“መዝሙር ወይስ መዝናኛ?”

የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ረታ ጳውሎስ ነው፤ በጸሃፊው ፈቃድ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል፤

ክፍል አንድ

የዜማ ስርአተ አምልኮ ውድቀት
ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት ሁሉ መዘመር የተለመደ ነገር ነው። ደቀ መዛሙርቱም ከኢየሱስ ጋር ሆነው ዘምረዋል። ማቴ 26:30
ሐዋርያው ጳውሎስ ዘምሩ ተቀኙ ብሏል። ኤፌ 5:19 በአዲስ ኪዳን ዘመን ሁሉ በብዙም በጥቂት፣ በዝግታም በጩኸት ሲዘመር ነበረ እየተዘመረም ነው።
አሁን ግን ያለው እድገት የሚመስል ዝቅጠት ቃሉን ከመዘመር፣ በማስተዋል ከመዘመር፣ የምር ከመዘመር፣ ለአምላክ ከመዘመር ያፈነገጠ ተዝናኖታዊ ፈንጠዚያ (ዘፈናምነት አለ ዘላለም መንግስቱ) እንደ ወረርሽኝ እየተራባ ነው።
ዋን ማኖቹ ጋ ደግሞ ብሷል። ዋናውን ካላስደሰትክ ማይክ ሁሉ ትነጠቃለህ!! ጉባኤውን አስተኛህብኝ፣ ዘጭ አረክብኝ ተብለህ ከመድረክ እያለህ በምልክት መዝሙር ቀይር አልያም ለሌላ ሰው ስጥ ትባላለህ። አድምቀው፣ ቀውጠው፣ ከፍ አርገን፣ ሿሿ ሸምበለላ፣ እሳት፣ እሪሪሪ…እንጂ የንሰሀ መዝሙር??? በጌታ ስም ይወጋል። የጥልቅ አምልኮ፣ የጤናማ ሙዚቃ እና ድምጽ ለዛ ፈጽሞ የሚገባቸው አይመስልም። ባንዱ በሲንኮፕ ምት ፋታ የሌለው ሙዚቃ መጫወት አለበት። ዝግ ያለ ነገር ዝቅ ያደርጋቸዋል አይወዱም። ጭር ሲል ይጨንቃቸዋል፣ ሕዝቡ ጥሎ የሚሄድባቸው ይመስላቸዋል። ጌታ በጣም ከበረ ተመለከ የሚባለው ከፍተኛ ጩኸት (120 db) ፣ ከፍተኛ ዝላይ እና ላብ ያለበት ዝማሬ ሲሆን ነው።

“ዋናውን ካላስደሰትክ ማይክ ሁሉ ትነጠቃለህ!! ጉባኤውን አስተኛህብኝ፣ ዘጭ አረክብኝ ተብለህ ከመድረክ እያለህ በምልክት መዝሙር ቀይር አልያም ለሌላ ሰው ስጥ ትባላለህ።”

እንዴት አይነት ምስኪንነት ነው? ድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ ያላችሁ የአሻገዳዎ አፍቃሪያን ጌታ ልቦናችሁን ያብራ። ችግሩ አትሰሙም፣ እናንተን ማን ያስተምራል? አስተማሪህን ልታስተምር አትችልም ብሏል እኮ አንዱ ዋና ማን ኦፍ ጎድ። እኔ የአርኪቴክቸር አስተማሪዬን በአንድ ወቅት ጊታር አስተምሬዋለሁ። ስጦታ ልዩ ልዩ ነው። አርኪቴክቸር ላይ እኔ የእሱ ተማሪ ነኝ፣ ጊታር ላይ እሱ የእኔ ተማሪ ነው አለቀ!! ሁሉን እኛ እናውቃለን የምትሉ ጓዶች እስቲ አደብ ግዙ። ስለ ድምጽ፣ ዜማ፣ አምልኮ…ወዘተ ተማሩ። ሁል ጊዜ እናንተ ደረጃ መዳቢ፣ አስመስካሪ፣ አስተማሪ፣ አናዛዥ ሆናችሁ እናንተን ማን ያገልግል? በሌሎች አገልግሎት አትነኩም አትባረኩም እናንተ ሁሌም ነኪ፣ ባራኪ፣ ሰጪ ናችሁ። ጥሩ ነው ጎሽ ከማለት ውጪ ከበታቻችሁ ያሉ አገልጋዮች ሲያገለግሉ ተባርኬአለሁ ነጽናንቻለሁ ጌታ ተናግሮኛል ማለት በእናንተ ዘንድ ነውር አይደለም ወይ? ተአምር ቢሆንላችሁ እንኳ ትመሠክራላችሁ ወይ?

ዛሬ ትንሽ ጠንከር ብያለሁ ይቅርታ!! ከፍቅር ከመንፈስ ነው እየተናገርኩ ያለሁት!

ወደ መዝሙሩ እንመለስና እባካችሁ ማስተዋላችንን አትንፈጉን! ዘማሪዎችም “ዘምሮ አደር” ከመሆን ይልቅ ለእውነት ሙቱ!! እንጀራም ውሀም ይቅር የጠራችሁ ጌታ፣ መዝሙር የሰጣችሁ ጌታ አዕምሮም ሰጥቷችኋል እየሰራችሁ ማገልገል ትችላላችሁ። የማታምኑበትን የአስረሽ ምቺው ዳንኪራ አገልግሎት ለማይረባ መብል ብላችሁ አትስጡ!!!! በቃ በሉ!!! መዝሙር በመንፈስ ከመሞላት፣ በቃሉ ከመሞላት፣ ከልብ ፈልቆ ለእውነተኛ አምላክ በመሠዊያው የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ የመድረክ ትወና አይደለም። ቆላ 3:15
ይህንን ሁሉ ስጽፍ በከፍተኛ ሁኔታ ለእውነተኛ የዜማ አምልኮ የሚተጉ ጉምቱ አገልጋዮችን ባለመዘንጋት ነው።