አምልኮ/Worship

እንዴት እዚህ ደረስን? ቀጥሎስ ወዴት?

ይህ ጽሁፍ በወንድም ረታ ጳውሎስ የተጻፈ ነው፤ በጸሃፊው ፈቃድ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል፤

ክፍል 2
የወንጌል አማኝነት ክርስትና (Evangelical Christianity) በሀገራችን በሙላት ከገባ በትንሹ 95 አመታትን አስቆጥሯል። ሆኖም በ1889 አካባቢ በባህረ ነጋሽ (ኤርትራ) ተጀምሮ የነበረውን የሚሽነሪዎች አገልግሎት ከጨመርን 120 ዓመት ያልፋል። የስዊድን፣ የፊንላንድ እና የኖርዌይ..ወዘተ ሚሽነሪዎች ይህንን የወንጌል ተልዕኮ ይዘው ወደ ሀገራችን ሲመጡ ለህዝቡ ያስተማሩት ቃሉን ብቻ ሳይሆን መዝሙሮቻቸውንም ጭምር ነበር። የመዝሙሮቹ የዜማ ዘውግም የሚሽነሪዎቹ ሀገር ሲሆን አዘማመሩም በህብረት እና በሐርመኒ (በአራቱ መሠረታዊ ድምጾች) ነበረ።መዝሙሮቹ በመጽሐፍ ተጽፈው (በታይፕ ወይም በእጅ) ጉባኤ ሲሰበሰብ በየወንበሩ ይሰራጫሉ፣ የሚዘመረው ዝማሬ ገጹ ተገልጦ በፒያኖ ወይም በኦርጋን በመታጀብ በፕሮግራም መሪ (ኮንዳክተር) እየተመራ ይዘመራል። የመጀመሪያው የመዝሙር መጽሐፍ በ1890ዎቹ በባህረ ነጋሽ የተጻፈው 40 መዝሙሮችን የያዘው መጽሐፍ እንደሆነ ይነገራል። በገጠሩ አካባቢ ደግሞ እዚያው በጉባኤ የሚፈጠር የቅብብሎሽ ዝማሬ (Antiphonal Chanting) ይታወቅ ነበረ።

በተለይም በጌድኦ፣ በሲዳማ፣ በከምባታ፣ በወላይታ እና በሀዲያ ህዝብ የተለመደ እና የደመቀ ጉባኤያዊ (Liturgical) አዘማመር ነበረ። ሊተርጂካል አዘማመር ማለት ጉባኤው ዋና ተዋናይ ወይም ሚና ተጫዋች የሆነበት የአዘማመር ዘዬ ማለት ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከሐዋሪያት ጀምሮ በሮማ ካቶሊክ ቀጥሎም በሉተራን የነበረ ሰፊውን የቤተክርስቲያን ታሪክ ሞልቶ የያዘው አዘማመር ይህ ሊተርጂካል አዘማመር ነበረ ቢባል አይጋነንም። ዋናው ዘማሪ ህዝቡ ነበረ!!ከመጽሐፉ እና ከቅብብሎሽ ባህላዊ አዘማመር ቀጥሎ ጊዜው በውል ባይታወቅም በግምት ከ1950ዎቹ መጨረሻ የሶሎ ዝማሬ፣ የኳየር ዝማሬ እንዲሁም የሀገርኛ ቅኝት ዘመናዊ አዘማመሮች የተጀመሩበትና በሚገርም ፍጥነት እየተስፋፉ የመጡበት ጊዜ ነበር። በሶሎ ዝማሬ እነ አዲሱ ወርቁ፣  ለገሰ ወትሮ፣ ደረጀ ከበደ፣ ሸዋዬ ዳምጤ፣ ታምራት ወልባ፣ ተስፋዬ ጋቢሶ፣ ታምራት ኃይሌ፣ ሙሉ ሀይሉ፣ አስቴር ተፈራ…ወዘተ

1960ዎቹን እና 70ዎቹን በተለየ ውበት እና ጣዕም ወንጌልን ያበሰሩበት፣ ቅዱሳንንም በዚያ ሁሉ ስደት ያጽናኑበት ወርቃማው ዘመን ነበር። እዚህ ውስጥ በሙዚቀኝነት እና የኳየር አሰልጣኝነት ጋሽ ደበበ ለማ ( አሁን ፓ/ር) ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ ብዙ አገልገዮች በየስፍራው ነበሩ። በአጭሩ ነው!ቀጣዩ የጉባኤ አዘማመር የነበረው የአዝማች ምርጫ ነው። ፕሮግራም መሪው ቆሞ ጉባኤውን መዝሙር ያስመርጣል፣ በጊታር ወይም በአኮርዲዮን ካልሆነም በእህቶች እገዛ የመግቢያ ፒች ይሰጣል ጉባኤው ይዘምራል።  ፕሮግራም መሪው ቢዘምርም ባይዘምርም ፣ መዝሙሩን ቢችልም ባይችልም ችግር የለም- ህዝቡ የሚወዘወዘውን እጅ እያየ ቅልጥ ድምቅ አድርጎ ይዘምራል።

በመጨረሻም እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ የቀጠለው ይህ ህዝባዊ አዘማመር በ1990 ዓ/ም ባልሳሳት በእህታችን ሊሊ እንዲሁም ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መመስረት ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ የተለመደው አምልኮ መሪ (Worship leader) እና የአምልኮ ቡድን (Worship team) የተባለው የጉባኤ አዘማመር ዘውግ ተከሰተ።

የሽብሸባ ኳየር ፣ ዘማሪ እንዳልካቸው ሐዋዝ፣ ቤተልሔም ወልዴ …ወዘተ በወቅቱ አስደናቂ በሆነ የመንፈስ ቅዱስ ህልውና እና መነቃቃት ጉባኤውን በዝማሬ መምራት ጀመሩ። አዲስ ነገር ነው!! በጣም ይማርካል!! ብዙዎችን አጽናንቷል አነቃቅቷል አረስርሷል። እኔም በወቅቱ ከተባረኩት አንዱ ነኝ ክብር ለጌታ ይሁን!

ይህ የአምልኮ መሪ የሚለው አደረጃጀት ከተለያዩ አብያተክርስቲያናት ከባድ ተቃውሞ እየገጠመው ምናልባት እስከ 1993 ዓ/ም ብቻ ቆየ እንጂ ከመካነ ኢየሱስ፣ ከቃለ ህይወት ጀምሮ ሁሉንም አጥቢያ ሞላው። የካሴት መዝሙሮችን እያጠኑ በአንድ ፒች እና ሪትም የሚሄዱ ብዙ መዝሙሮችን እየቀጣጠሉ መዘመር ታሪኩ በአጭሩ ይህን ይመስላል። አሁን ይህ ጉዳይ ምን ላይ ነው ያለው? ያ ሁሉ ከጅምሩ የነበረው ውበት እና በረከት ለምን ወደ ብስጭት፣ ግልብ ዝላይ፣ የተለመደ ጩኸት…አታታታታ….ራቻቻቻቻ…እእሪሪሪ…የት አለ ጩኸት አይሰማኝም…ውውውይይይ…እንዴት ተቀየረ??

በዋልዝ:- አቤት ምህረት የበዛለት ብሎ ጀምሮ በመሀል 6/8 ወሎ፣ 12/8 ችክችካ (ዋጋው በገዠፈ ቴምፖ) ምን ልሁና ምን ልሁና፣በመጨረሻም በፈጣን ዲስኮ በመንፈሱ ስሆን..ዳራ ራራራ…የሚሄደው የተሸመደደ (Predictable) ከልብ ያልሆነ ግልብ አዘማመር የዋን ማኑን አይን አይን እያዩ፣ ስሜቱን እየተከታተሉ አልሰለቻችሁም ወይ??

መዝሙር የአርፋጅ ፕሮፌቶች መጠበቂያ፣ *የትንቢትና ስም ጥሪ* ማዳመቂያ፣ የህዝብን ስሜት ብቻ በማጦዝ ለሁሉ “አሜን” እንዲል ማደንዘዣ፣ እንደው እንደ ዲጄ ሙዚቃ መዛፈኛ መፈንጠዣ፣ ጭር እንዳይል በሰርግ ቤት ተበርቻቻ ሆኖ የሚቀጥል አይምሰላችሁ። ሊዘመርለት የተገባው የቤቱ ባለቤት ጅራፉን ያነሳል!!!

እንግዲህ እቀጥላለሁ በክፍል 3

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጉባኤያዊ አዘማመር እና የህብረት አምልኮ መርህ፣ አላማ፣ ስርዓት፣ አመራር … እንዴት ነው??