ማሕበረሰብ ስለ እኛ ቤተ ክርስቲያን

ስለ ብሽሽቅና ፉክክር-ተኮር ስብከቶች ጥቂት ልበል!

                   በወንድም ጌታሁን ሄራሞ ተጻፈ በጸሃፊው ፈቃድ በዚህ ድረ ገጽ ወጥቷል፤
    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ብቅ ያሉ አንዳንድ የ”Emerging Churches” አገልጋዮች የሚያምኑትን እውነት ለሌሎች ለማስተላለፍ እየሄዱበት ያለው አካሄድ ከወንጌል ማዳረስ ዓላማ ይልቅ ብሽሽቅና ፉክክር የነገሰበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የወንጌል መልዕክት አውዳዊ ይዘቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ከሐዋሪያው ጳውሎስ የበለጠ ያስተማረን የለም። ይህን አውዳዊ የወንጌል ስብከት ጥበብን ግልፅ ለማድረግ በቀዳሚነት ወደ ሐዋ ሥራ ምዕራፍ 17 መዝለቅ ግድ ይላል።
     በክፍሉ ሐዋሪያ ጳውሎስ የግሪክ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ አቴንስ በገባ ጊዜ መንፈሱ እንደተበሳጨበት በክፍሉ ተቀምጧል። ከአንድ እግዚአብሔር ውጭ ሌላ ጣዖት ሲመለክ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ማንም ሰው መንፈሱ ይበሳጭበታል፤ እንዲያውም ግራ ሊገባን የሚገባውና ራሳችንን መፈተሽ ያለብን መንፈሳችን ባይበሳጭ ነው፤ ይህን እውነት መካድ አይቻልም።
ታዲያ ይህን የውስጥ ብስጭት አምቆ ይዞ የእውነት ወንጌልን በፍቅር ለሌሎች ለማድረስ ራስን የመግዛት መንፈስና ጥበብ ልንካን ይገባል። ለምሣሌ ሐዋሪያ ጳውሎስ በተበሳጨበት ልክ…የአቴና ሰዎች ሆይ እናንተ የምታመልኩት ጣዖት ነው፤ እንጨት ነው፤ ጣውላ ነው፤ ቁም ሳጥን ነው.. ወዘተ” እያለ ስብከቱን አልጀመረም። ሆኖም ሐዋሪያው የአቴና ሰዎች ከያዙት እምነት ውስጥ የጋራ እሴቶችን ፈለገ። ወደ አንድ መሠረታዊ እውነትም ደረሰ…የአቴና ሰዎች ቢያንስ በፈጣሪ መኖር ያምናሉ…They are not atheists! This shared spiritual value is a good starting point for his preaching. እናም የነርሱን ነባራዊ ሁኔታን “acknowledge” አድርጎ ስብከቱን ቀጠለ፦ “ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ። የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ።” ቁ. 22 በመቀጠልም ሐዋሪያ ጳውሎስ ሌላ ሁለተኛ የጋራ መንፈሳዊ እሴት በእምነታቸው ውስጥ አገኘ፦” የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።” ቁ 28እንዲያውም እዚህ ጋ ሐዋሪያው ባለቅኔዎችን “እንደተናገሩ” እያለ “Quote” ሲያደርጋቸው እንመለከታለን። ደግሞም ባለቅኔዎቹ የእግዚአብሔር ዘመዶች ነን ማለታቸውን… እግዚአብሔር ከሰው ሩቅ አለመሆኑን…ለማስገንዘብ ሲጠቀም እናስተውላለን።ሆኖም ከላይ የጠቀስኩትን ሁለቱን እሴቶች ከጠቀሰ በኋላ ሐዋሪያው እውነትን በፍቅር እንዴት እንደገለፀ እንመልከት፦
” የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና።እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።” ቁ 23
       በዚህ በሐዋሪያ ጳውሎስ ማብራሪያ ውስጥ “ሳታውቁ የምታመልኩትን” የሚለውን አስምሩልኝ። ምን ማለት ነው? አምልኮ ዕውቀትን ይቀድማል? ወይስ ዕውቀት አምልኮን ይቀድማል? በእኔ አረዳድ የሰው ነፍስ የፈጣሪዋን እስትንፈስ ስላለባት ዕውቀት በሌለበትም ፈጣሪዋን ፍለጋ ትኳትናለች ስለዚህም ሐዋሪያው ጳውሎስ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚለውን አባባላቸውን በጥበብ ወደ እውነተኛው አምላክ ለመጠቆም ተጠቅሞበታል…It is just as if writing the exact payable amount on a blank cheque paper! ሁለተኛውን የጳውሎስ ማስተካከያ ደግሞ በቁ 29 ተጠቅሷል። ” እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።” እዚህ ጋ የጳውሎስ አመክንዮ ግልፅ ነው፤ የአመክንዮው መነሻው የራሳቸው እምነት ነው…እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን…የሚለው! የጳውሎስ ጥያቄ… እንግዲህ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ዝምድና ካለ እናንተ በእግዜር አምሳልም ከተፈጠራችሁ ከተቀረፀ ድንጋይ ወይም ወርቅ ጋር እንዴት ልትቆራኙ/ልትዛመዱ ቻላችሁ? የሚል ነው። በሌላ አነጋገር ዝምድናው ካለ “ዲ.ኤን. ኤ”ያችሁ በየትኛው አመክንዮ ወደ ድንጋይ ሄደ? ማለቱ ነው።
     እንግዲህ ከላይ ያለውን የአውዳዊ ስብከት ዘዴን ጠቅሰን ስንሞግት አንዳንዶቻችን መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ላይ… ደንቆሮዎች፣ ዕውሮች፣እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣ በውጭ በኖራ የተለሰነ መቃብር…ወዘተ” የሚሉ ኃይለ ቃሎችን ተጠቅሞ የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል። ይህ የማቴዎስ 23 መልዕክት ለማን address እንደተደረገ ካለማወቅ የመነጨ ጥያቄ ነው። ቁጥር 13 እንደሚያመለክተው መልዕክቱ የተላለፈው ለግብዝ ፈሪሳውያንና ጻፎች እንጂ ለተራው ምዕመን አይደለም። ኢየሱስ በሌሎች የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ግብዝ የሃይማኖት መሪዎችን ፊት ለፊት ነበር የሚጋፈጣቸው… ስብከቶቹና ትምህርቶቹ እንደእኛዎቹ ፈፅሞ ጅምላ ጨራሽ አይደሉም። ለምሣሌ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ 4 ኢየሱስ ሴትዮው አመንዝራ መሆኗን እያወቀ እንኳን ተግባቦቱን የጀመረው “አንቺ ሴተኛ አዳሪና 5 ባሎች የነበሩሽ ነሽ” በማለት ሳይሆን “ውኃ አጠጪኝ” በሚል ልመና ነበር….እንዲሁም ነቢዩ ናታን ንጉሥ ዳዊት በዝሙት ኃጢአት መውደቁን ካወቀ በኋላ በቀጣይነት ለመልዕክቱ ሜቴዶሎጂ የፀለየ ይመስለኛል…መልዕክት መቀበል አንድ ነገር ነው…የተቀበልነው መልዕክት እንዴት ይተላለፍ?…የሚለው ጥያቄ ሌላው ቀጣይ የቤት ሥራ ነው። ደግሞም ለዳዊት መልዕክት ማስተላለፍና ለሌላ መደበኛ እሥራኤላዊ መልዕክት ማስተላለፍ ሜቶዶሎጂው ለየቅል ነው። እናም ናታን በጣም “poetic” በሆነ መልኩ ነበር ዳዊትን በግለ-ሂስ (self-criticism) ቅርቃር ውስጥ ያስገባው(2ኛ ሳሙ ምዕ 12)። በነገራችን ላይ ስህተትን ከማረም አኳያ ከሁሉም በላይ ስኬታማ ተግባቦት የሚባለው ሰዎች ራሳቸውን criticize እንዲያደርጉ የሚያስችለው ሜቶዶሎጂ ነው…ልክ ነቢዩ ናታን ዳዊት በራሱ ላይ እንዲፈርድ ያደረገበትና ኢየሱስም ከላይ የጠቀስኳት ሴት “ባል የለኝም” በማለት በራሷ “confess” እንድታደርግ ያስቻለበትን መንገድ ማለቴ ነው።
         በእኔ አተያይ ኢየሱስ በኃይለ ቃል ግብዞችን የገሰፀበትን ግሳፄ ለግብዞች “forward” ማድረግ እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን “forward” ከማድረግ ባለፈ ኢየሱስም ይሁን ቀደምት ሐዋሪያትና ነቢያት(መጥምቁ ዮሐንስን ጨምሮ) ግብዞችን በገሰፁበት ልክ መገሰፅ የምንችልበት “Authority” ይኖረን እንደሆነ ለኔ ግልፅ አይደለም(እሱን ለሥነ መለኮት ምሁራን ልተዋው)። ስለዚህም አሁን በአንዳንድ “Emerging Churches” እየተስተዋሉ ያሉ ጅምላ ጨራሽና አውድ-አልባ የቃላት ብሽሽቆች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን ነው። በአቴናው በሐዋሪያው ጳውሎስ አውድ-ተኮር መልዕክት ንስሐ የገቡ የአቴና ሰዎች አሉ፤ የቀሩትም ስብከቱን እንደገና ለመስማት ለጳውሎስ ቀጠሮ ሰጥተውታል(የሐዋ ሥራ 17፤34)። በተቃራኒው ጅምላ ጨራሽ ብሽሽቅና ከወንጌል ስብከት ጥበብ የፀዳ የስብከት ዘዴ የቱን ያህል ውጤት እንደሚያስገኝ መገመት ያን ያህል አያዳግትም።
      በነገራችን ላይ የነዚህ ቡድኖች ጮክ ብሎ ብሽሽቁን ማጧጧፋቸው ሌላም ድምፀት አለው። “ነባርና ዕድሜ-ጠገብ የፕሮቴስታንት ቤ/ክርስቲያናት ለዓመታት በፍርሃት ተሸብበው ያልሰበኩትን ወንጌል እኛ አዳዲሶቹ ዛሬ አሃዱ ብለን ደፍረን አጥር ጥሰን እየሰበክን ነው” የሚል በትዕቢት የተሞላ ድምፀት! ሆኖም ነባር የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናት ቀደም ሲል ለወንጌል ዋጋ የከፈሉት እንደነሱ በተንቆጠቆጡ ቪላዎች እየኖሩና ቅንጡ መኪናዎችን እያሽከረከሩ ሳይሆን መስዋዕትነትን መክፈል አስፈላጊ በሆነበት ቅፅበት ሁሉ በወህኒ ቤት እየማቀቁ እንደነበር ማን በነገራቸው? ዛሬ የወቅቱን የፖለቲካ አውድ በዘዴ ፈትሾ ለወንጌል መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ የሚመስሉ “opportunists” ስልትና ስሌት እንኳን ከእግዜሩ ከሰውም የተሰወረ አይደለም። አባቶቻችን ለወንጌል ዋጋን የከፈሉት ወንጌል ተቋማዊ በሆነ መልኩ በመንግስት ተቃውሞ በደረሰበት ዘመን እንጂ እንደ ዛሬዎቹ የወቅቱን የመንግስት መዋቅርና ሕገመንግሥት አቋም አስልተው አልነበረም።
በመጨረሻም እነዚህን “Emerging Churches” ያቀፈ አንድ ካውንስል አለ መሰለኝ። ይህ ካውንስል አቅሙና ብቃቱ ካለው ለግለሰቦቹ ከብሽሽቅና አጉል ፉክክር የፀዳ አውድ-ተኮር ወንጌል እንዴት በጥበብ እንደሚሰበክ ሥልጠና ቢሰጣቸው መልካም ነው እላለሁ።