ስለ እኛ

ታላቅ ሩጫ

healthy lifestyle asian woman running at seaside

ሁላችን ሯጮች ነን።

ዛሬ እሁድ ጥር 15 2014 (Jan, 23, 2022) በአዲስ አበባ ታላቁ ሩጫ ይደረጋል። ይህን ስጽፍ ሊጀምር አንድ ሰዓት ይቀረዋል።

ለምን ታላቁ እንደተባለ አላውቅም። ‘ታላቅ’ ሳይሆን፥ ‘ታላቁ’ ነው የሚባለው። በእርግጥ ከአፍሪቃ የጎዳና ሩጫዎች ትልቁ ነው። ያ ይሆን ታላቁ ያስባለው? አላውቅም። ከእርሱ የሚበልጡ አሉ። 21 ዓመት ሆነው። ‘ዓላማው እስፖርትን ሩጫን ማበረታታት፥ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት፥ በጎ መልእክቶችን ማስተላለፍ፥ ኢትዮጵያን በበጎ ማስተዋወቅና ቱሪዝምን ማስፋፋት ነው።’ እንደ አስተባባሪዋ። የዘንድሮው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀኑ ተራዝሞአል። ባይለወጥ ኅዳር 5 ነበር ሊደረግ የነበረው። በዛሬው ወደ 25 ሺህ ሯጮች ይጠበቃሉ።

የሚደረግበት ቀን እሁድ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ቢሆንም ከጠዋቱ 11:30 (5:30 a.m.) ጀምሮ ብዙ መንገዶችና ጎዳናዎች ይዘጋሉ። እሁድ ነውና አምልኮም ይስተጓጎላል።

ሩጫ መልካም ነው። ይህ ሩጫም መልካም ነው። ማናቸውም ሩጫም መልካም ነው። ሕይወት ራሷ ሩጫ ናት።

ሁላችን ሯጮች ነን፤
ሁሌ እንሮጣለን፤
ከእንጀራችን ኋላ፤
ምንም አሸንፈን ዋንጫውን ባንበላ።

ብሏል ባለቅኔ ደረጀ በላይነህ።

ሐዋርያው ጳውሎስ፥ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ (2ጢሞ. 4፥7) ሲል፥ ለሟቾች የመቃብር ድንጋይ ሐረግ መጣሉ አይደለም። እውነትም ሩጫውን የሮጠ ሰው ነው።

እኛም ሁላችን በሩጫ ላይ መሆናችንን ሲያስገነዝበን የዕብራውያን ጸሐፊ፥ እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። አለ፤ (ዕብ. 12፥1-2)።

ሁላችን ሯጮች ነን። ሕይወት ሩጫ ስለሆነ። አንዳንዶች በአጭሩ ይጨርሱታል። አንዳንዶች ዘለግ ይልባቸዋል፤ ወይም ይልላቸዋል። የአንዳንዶቹ ረዥም ነው።

የዕብራውያን ጸሐፊ፥ ‘እንሩጥ’ ይላል። ይህን ያለው በተለይ ለዕብራውያን አማኞችን ቢሆንም፥ በክርስቶስ ላመኑ ቅዱሳንም ሁሉ ነው። ቀደም ሲል በዕብ. 6፥1 ‘እንሂድ’ ብሎ ነበር፤ ስለዚህ የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ። ወደ ግብ፥ ወደ ፍጻሜ ከሆነ መሄድም መሮጥም ጉዞ ነው።

በተለይ፥ ‘እንሩጥ’ ሲል ከፊታችን የሮጡትን ምስክር አድርጎ ነው። ብዙ ናቸው። እንደ ደመና የከበቡን እስኪመስሉ ብዙ ናቸው። በዕብ. 11 ጥቂቶቹ ብቻ ተጠቅሰዋል።

እንድንሮጥ የተነገረን ሁለት ነገሮችን እያደረግን ነው፤

  1. ከኃጢአት ጋር ወዳጅ ባለመሆን፤ ወይም ባላጋራ በመሆን። እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ . . . እንሩጥ።
  2. ከፊታችን በጽድቅ ሮጦ የጨረሰውን እያየን። የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።

ታላቁ ሩጫ ለምን ታላቁ ሩጫ እንደተባለ ባይገባኝም፥ ሁላችንም ሯጮች መሆናችንን አንርሳ። ስንሮጥም በእውነት እንሩጥ። በጽድቅ እንሩጥ። ለማሸነፍ ሳይሆን ለመጨረስ እንሩጥ።