ማሕበረሰብ ቤተ ክርስቲያን

ሰልፊ (እኔው፣ ከኔው፣ ለኔው፣ በኔው)

Photo by Steve Gale on Unsplash
Photo by Steve Gale on Unsplash

ሰልፊ የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት የ2013 የዓመቱ ቃል ለመባል የበቃ ዘመነኛ ቃል ነው፤ ትርጉሙ አንድ ሰው ራሱን በተለይ በስማርት ፎን ወይም በዌብ ካም ራሱን በራሱ ፎቶ ካነሳ በኋላ በመገናኛ ብዙሃን (ሶሻል ሚድያ) ገጾች ላይ በመጫን ራሱን ሲያስተዋውቅ እንደማለት ነው።

ሰዎች ሰልፊ በማድረግ በፌስቡክም ሆነ በየትኛውም የመገናኛ ብዙሃን (ሶሻል ሚዲያ) በማውጣታቸው ምንም ችግር የለውም (በግሌ ክፋቱን አላይም)። በጨዋደንብና ስርዓት የጠበቀ እስከሆነ ድረስ ማለቴ ነው።
ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመለስና በአማርኛችን ብንተረጉመው ምን እንደሚባል እንጃ ግን “ራስ በራስ” እንበለው? ለአማርኛ ቋንቋ ተርጓሚዎች ብተወው እመርጣለሁ። ይሄ ቃል ጎላ ባለመለኩ የሰማሁት በ2013 የደቡብ አፍሪቃው መሪ ማንዴላ የቀብር ስነስርዓት ላይ ታድመው ከነበሩ የሃገር መሪዎች መካከል የአሜሪካኑ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ እንዲሁም የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሮን እና የዴንማርኳ ጠቅላይ ሚንስትር ሄሌ ቶርኒንግ የዓለማችንን ሚድያ ትኩረት ስበው በነበረበት ወቅት ነው። እነዚህ የሦስት አገራት መሪዎች ሰልፊ ፎቶ ሲነሱ በመታየታቸው ምክንያት ማለት ነው።

ሰልፊ አሁን በመዝገበ ቃላት ወጣ እንጂ አዳሜ እና ሔዋኔ ቀድሞውኑ ሰልፊ (ራስ በራስ) ናቸው። በተለይ የአሁኑ ባሕል ይሄን የሰው ልጅ ማንነት እያጎላው መጥቷል ራስን ከፍ ማድረግ ማስቀደም በአገራችንስ ብዙ ብሂሎች አሉ አይደል “ከራስ በላይ ንፋስ” ፡“ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል”። አሁን አሁን የማሕበረ ሰብ መገናኛዎች (social network) መበራከታቸው ማንነታችንን እየገለጡት ነው ብዬ ብል ማጋነን አይሆንብኝም “በፊት ገጽ” (Facebook) ገጾቻችን ላይ የምንመለከታቸው የምንታዘባቸው ነገሮች አሉ።

ሰልፊ ከፌስቡክ ወደ ቤተ እምነት

በፌስ ቡክ ብቻ ሳይሆን ሰልፊ በመድረኮችም መታየት ከጀመረ ሰንበትበት ብሎአል፡ በፊት በፊት በተለይ ሃይማኖታዊ በሆኑ ቦታዎች (መድረኮች) ይታዩ የነበሩት የመላክት ምስሎች ወይም የቅዱሳን ሰማእታን ወይም የቅድስት ድንግል ማርያም ተብለው የሚጠሩ ምስሎችን ነበር፡ (በኦርቶዶክስ) ማለቴ ነው። በፕሮቴስታንቱ ደግሞ በመድረኮቻችን ጎልተው የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ቢበዛ ቢበዛ መስቀል ይታይ ነበር አሁን ግን ነገሩ እንደዚህ አይደለም የሰባክያኑ ምስል በትልቁ ተለጥፎ እናያለን በአንዳንድ የቤተ እምነት መድረኮች ብቻ ስይሆን በጎዳናዎች ላይ ባሉ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ በትልልቁ የተለያየ ስያሜ የተሰጣቸው ሰዎች ይታያሉ “ሰልፊ” ይሏል ይሄ ነው።
ከአንድ ወዳጄጋ ሰለ ተለያዩ ጉዳዮች አንስተን ስንወያይ በአጋጣሚ በኢትዮጵያ በአንድ ፕሮግራም ዝግጅት ላይ የሆነውን በማዘን አጫወተኝ፡ ነገሩ እንዲህ ነው ለፕሮግራሙ ዝግጅት የተሠራውን ፖስተር (Poster) ተጋባዥ የሆኑቱ (አገልጋዮች) አስቀድመው እንዲያዩት በተደረገበት ጊዜ (ለፕሮግራሙ የተጋበዙ በርከት ያሉ ዘማሪያን ሰባኪያን ስለነበሩ)፡ ከእነዚህ ተጋባዦች (ሰባክያን) አንዱ ይሄ በፍጹም አይሆንም በማለት ቅሬታውን ለአዘጋጆቹ ገለጠ ነገሩ ግራ የገባቸው ወገኖች “ምን ተፈጠረ?” ብለው ሲጠይቁት ይሄ ወንድም “እንዴት አድርጋችሁ ነው የኔን ፎቶ ከሌሎች እኩል አሳንሳችሁ በማስታወቂያው ላይ የምትሰሩት? ይኔን ፎቶ ጎላ አድርጋችሁ ነው ማሰራት ያለባችሁ።” የሚል ትእዛዝ በመስጠት የፕሮግራሙ ጋባዦች እንደገና ፖስተሩን  የአገልጋዩን ፎቶ ጎላ በማድረግ በድጋሚ ለማሰራት እንደተገደዱ ሰማሁ።
መቼም ከጀመርኩት አይቀር አንድ ካነበብኩት ልጨምር ያነበብኩት ከፌስብክ ሲሆን የገጹ ግድግዳ ባለቤት (ጸሃፊ) “www.facebook.com/pages/ምስባከ-ጳውሎስ-Pauls-Pulpit” መሆኑን በቅድሚያ በማሳውቅ ጽሁፉ እንዲህ ይላል…
ወጣቶቹ መኪና ላይ ትልቅ ስፒከር ጭነው በማስታወቂያ ከተማውን ቅወጣ ተያይዘዋል፡፡ እየደጋገሙ ሕዝቡን ሲያደነቁሩበት የነበረው ማስታወቂያ “ሐዋርያው ዳንኤል ከለንደን ተመልሷል” የሚል ነበር፤ ከዚያም ሰዎች እርሱ ወደሚተውንበት ቦታ እንዲመጡ ይጋብዛሉ፡፡ ማስታወቂያው ለብዙ ክርስቲያኖች አስደንጋጭ ነበር፤ ቁልቁለቱን እየወረድንበት ያለው ፍጥነት የማይታመን ነው፡፡ ይህን ማስታወቂያ ሲሰሙ ከነበሩ ወገኖች አንዷመብራት ወዳቆመው መኪና ጠጋ አለችና “የጌታን መመለስ እያወጃችሁ መሆኑ ነው?” ስትል ማስታወቂያ ነጋሪዎቹን ጠየቀቻቸው፣ ተገቢ ጥያቄ ነበር፡፡ እነርሱ ግን የአቶ ጌታቸውን ልጅ መመለስ ነበር ሲያውጁ የነበሩት፡፡ በዚህ ዘመን የጌታን ስም ከሚጠሩ ሰዎች የሚብሱ የወንጌል ጠላቶችን እናገኛለን ብዬ መቼም አላስብም፡፡ (ከምስባከ ጳውሎስ የተገኘ)

የእኛን ግዝፈት አልቀን ለማሳየት የሚደረገው ሙከራ! አንድ ሰባኪ እንዲህ ሲል ሰምቻለሁ “ፓስተርና ፖስተር መለየት አቅቶኛል” እውነቱን ነው። ለነገሩ በነጳውሎስ ዘመን የሆነ ታሪክ አለ በሐዋርያት ሥራ (14:8-18) በእነ ጳውሎስ እጅ የተደረገውን ተአምራት ሕዝቡ በተመለከተ ጊዜ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ሊሰዉላችው በፈለጉ ጊዜ ልብሳቸውን በመቅደድ እነሡ እንደማናቸውም ሰዎች መሆናቸውን በተደረገው ተአምር የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው አምላክ ጣት እንጂ የነሱ ምንም ነገር እንደ ሌለበት አሳይተዋል እነጳውሎስ “ሰልፊ” የሚባለው ቃል በእነርሱ የመዝገበቃላት የሌለ አገልጋዮች ናቸው።

ለነገሩማ ጳውሎስ ስለ ስልፊ ሲያስረዳን እንዲህ አልነበር ያለን “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም…” ካለን በኋላ በዛው በገላትያ መጽሐፍ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት እኔም ለዓለም ከተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት፡ ከእኔ የራቀ ይሁን።

ከተወሰኑ ወራት በፊት እጅግ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተ በሩሲያ የተጀመረ ከዛም በሌሎች ብዙ ሃገራት ተቀባይነት ያገኘ አደገኛ፡ሰልፊ (Daredevil) ወይም “ተዳፋሪ ሰልፊ” በጣም  እጅግ ከፍ ያሉ አደገኛም የሆኑ ሕንጻዎች ጫፍ ላይ በመውጣት ራሳቸውን ሰልፊ በማንሳት ትኩረትን እይታ እንዲያገኙ የሚሹ ወጣቶች በሶሻል ሚዲያ ላይ ፎቶአቸውን በመለጠፍ ለሕዝብ እይታ፡በዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች ተስተውለዋል። እነዚህ ወጣቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚያደርጋቸው ከበስተጀርባ ያለው ነገር ነው። የቆሙበት ወይም የተንጠለጠሉበት። ሰልፊና እራስን ከፍ ማድረግ ጎላ አድርጎ ማሳየት አይመሳሰሉባችሁም? እኔ በጣም ይመሳሰሉብኛል፡:

እኛን ራሳችንን አጉልተን እና አግዝፈን ለማሳየት የምናደርጋቸው ጥረቶች አሉ በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በምንነዳው መኪና በቤታችን በንብረታቸን ወይም በተለያዩ መንገዶች። እንግዲህ ከግል ማንነታችን ጀምሮ እስከ አገልግሎታችን ልናየው ይገባል። አንዳንድ አገልጋዮች ክርስቶስ ኢየሱስን አስታከው ራሳቸውን ጎላ አድርገው ሊያሳዩን ይሞክራሉ (ይሰብኩናል) ወይም በእነሱ የተደረገውን ገድል ይዘክሩልናል፡ መቼም ጌታ የሠራውን ብንናገር በራሱ ክፋት ባይኖረውም በውስጠ ታዋቂነት ሰልፊ ኖሮት ሲነገር ግን ደስ አይልም (በዘመነኛው ቋንቋ አይመችም!) መቀባታቸውን ከእነርሱ በቀር ሌላ ቢጸልይ እግዜር የማይሰማ እንደሆነ ከዚህ የተነሳ ሰው እነሱን ተሳልሞ በእነሱ ደጅ ካላለፈ አይደለም የእግዚአብሔርን ፊት በጓሮው እንኳ እንዳልደረስን አድርገው ሊያሳዩን የሚሞክሩ ተበራክተዋል።  ግን መጽሐፉ የሚለው “ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ ከቁጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ።” (ሉቃ 17:10)

“ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከብራል፡” (ማቴ 23:12)
እግዚአብሔር በየትኛውም ነገራችን ለክብሩ እንድንኖር ይፈልጋል እኛ እንድንታይ ሳይሆን በእርሱ ሆነን እሱ በእኛ እንዲታይ ይሻል፡ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ተናገረው “”ከእኔ ይልቃል” (ዮሐ 1:15) ካለ በሁዋላ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል።” (ዮሐ 3፡30) ዮሐንስ ጎልቶ ሊታይ የሚገባውን  እንዲጎላ የምድረበዳ ድምጽ ብቻ እንደሆነ ተናግሮ ወደ ክርስቶስ አመልክቶ አለፈ።

ወገኖች እኛ (ሰልፊያችን) ምን ይመስላል?

About the author

Tebebe Mekonnen

ወንድም ጥበበ ባለትዳር እና የልጆች አባት ነው፤ ጌታን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ እየተከተለ ያለ፣ ባለበት ሕብረት ጌታን የሚያመልክ እና የሚያገለግል የጌታ ደቀ መዝሙር የሆነ ወንድም ነው፤