ቤተ ክርስቲያን

የምክር ቃል ለስደተኛዋ ቤተክርስቲያን

ክርስቶስን መከተል ወንጀል በሆነባቸው አካባቢዎች ድልን ለመቀዳጀት የሚረዱ ስልቶች

በክርስቶስ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ብዙ የስደት ዘመናት ነበሩ፡፡ አንዳንዴ በጣም የከፋ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስውር ቢሆንም ስደት ያልነበረበት ዘመን አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ችግር በተለያዩ መንገዶች ተስተናግዷል፡፡

በመጀመርያ ደረጃ እኛን የሚጠላ ጠላት (ሰይጣን) መኖሩ መታወቅ አለበት፤ ስለዚህ ስደት የአማኝ ሕይወት አካል መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ተከታዮቹ ስለ ጉዳዩ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡

ማቴዎስ 5፡10-12 የተራራው ስብከት ተብሎ የሚታወቀው ምንባብ ክፍል ነው፡፡ በቁጥር 3 ና 9 ላይ ኢየሱስ በፅድቅ ስለተባረኩ ሰዎችና ይህ ባሕርይ ምን ይዞ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡

በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።

የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።

የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።

ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።

የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።

ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።

ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።

የዚህ ስብከት ዓላማ አዳዲስ የተሾሙትን ሐዋርያት ከዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች እንዴት ልዩ መሆን እንዳለባቸው ለማስተማር ሲሆን ቁጥር 10-12 እንዲህ ይላል፡-

ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።

ማቴዎስ ሁላችንም እንዲኖረን ከምንፈልጋቸው አዎንታዊ ነገሮች ወደማይፈለጉ አሉታዊ ነገሮች ይሄዳል፡፡ ስለ ጽድቅ ስለመሰደድና በውጤቱም መንግሥተ ሰማያትን ስለማግኘት ይናገራል፡፡ “ይህ ከተፈጸመባችሁ ብሩካን ናችሁ” ይላል፡፡ በቻይና የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ስደት ካልደረሰባችሁ መንፈሳዊ ሕይወታችሁ ደካማ እንደሆነና ለሰይጣን ስጋት እንዳልሆናችሁ ያስባሉ፡፡ ስለዚህ ስደት በአማኝ ሕይወት ውስጥ ከእግዚአብሔር በረከቶች መካከል አንዱ መሆኑን እናያለን፡፡

ያዕቆብ 1፡2-8 እንደሚናገረው መከራ ፅናትን፣ ፅናት ደግሞ ብስለትን ያመጣል፡፡ በዚሁ አውድ ውስጥ ቁ. 5-8 ላይ ስለ ጥበብ እንድንጸልይ ሲናገር በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔርን በረከት ማየት ስለምንችልበት ጥበብ ነው፡፡ ምንባቡ ከምንም ይልቅ ስደትን የተመለከተ ነው፡፡

1ጴጥሮስ 3፡13-22 እና 4፡12-19 ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ በጽድቅ ምክንያት የሚመጡት ስደቶች ሁሉም እንዳልሆኑ ይናገራል፡፡ አንዳንዴ በራሳችን ኃጢአት ምክንያት ይመጣሉ፡፡ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እንግዳ ነገር እዳልሆነና በክርስቶስ መከራ ውስጥ መካፈል እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህ መፍራት ሳይሆን መልካም ነገር ማድረግን መቀጠል ያስፈልገናል፡፡

2ጢሞቴዎስ 3፡12 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ መከራና ስደት ለጌታ ስንኖርለት እንደሚገጥመን ጢሞቴዎስን ያሳስበዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ስለ መከራ የሚናገሩ ብቸኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ባይሆኑም መሠረታዊውን መርህ ያሳዩናል፡፡ ከነዚህ ጥቅሶች የተወሰኑ ድምዳሜዎችን ማውጣት እንችላለን፡-

መከራና ስደት በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የማይጠበቁ አይደሉም፡፡

ለእግዚአብሔር የበለጠ ስንኖር ስደት ይጨምራል፡፡

ያለ ፍትህ ብንሰደድና ብንወነጀል እንኳ ንጹህ ህሊና ሊኖረን ይገባል፣ “በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።” 1ጴጥሮስ 3፡16

ለክርስቶስ ስንል መከራን የምንቀበል ከሆነ እግዚአብሔር እኛንና ሌሎችን ለመባረክ ይጠቀምበታል፡፡

ቤተክርስቲያን ስደትን የተጋፈጠችበት ሁኔታ

ቤተክርስቲያን በሮማ ኢምፓየር ውስጥ

በጥንቷ ሮም ውስጥ ቤተክርስቲያን ለ300 ዓመታት ያህል ክፉኛ ስትሰደድ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ የመጀመርያው ክርስቲያን ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እስከነገሠበት ጊዜ ድረስ ለቤተክርስቲያን ታስቦ የተሠራ ሕንፃ አንመለከትም፡፡ ክርስቲያኖች በግላጭ አይሰበሰቡም ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሮም ውጪ “ካታኮምብ” የተሰኙ ዋሻዎች ይገኛሉ፡፡ በእነርሱ ውስጥ ክርስቶስን የሚያከብሩ ጽሑፎችን እንመለከታለን፡፡ የክርስትና ምልክት የሆነው ታዋቂው የዓሣ ምስል ከዚህ ዘመን የመጣ ነው፡፡ አማኞችን ለይቶ ለማወቅ ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡ ዓሣን የሚያመለክተው የግሪክ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና አዳኝ የሚል ምህፃረ ቃል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አንድ ሰው ቢያጋጥማችሁና ክርስቲያን መሆኑን እርግጠኞች ካልሆናችሁ ግማሽ የዓሣ ምስል ትስሉና ሰውየው ክርስቲያን ከሆነ ይጨርሰዋል፡፡

የመጨረሻውና አስከፊ የሚባለው ስደት በንጉሥ ዲዮቅላጢስ ዘመን የተደረገው ነው (284-305 ዓ.ም.)፡፡ ራሱን አምላክ ስላደረገ በሮም ግዛት የነበረ ሰው ሁሉ ለእርሱ መሥዋዕት ማቅረብ ነበረበት፡፡ መሥዋዕት ካቀረባችሁ በኋላ መስማማታችሁን የሚገልፅና ለባለሥልጣናት የምታሳዩት ምልክት ይሰጣችኋል፡፡ ያንን ካላደረጋችሁ ልትገደሉ ትችላላችሁ፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ባለመስማማታቸው ምክንያት ተገድለዋል፡፡ አንዳንዶች በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በጫወታ አደባባዮች ውስጥ ለዱር አውሬዎች ተጥለዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ያልተለመደ ነገር መታየት ጀመረ፡፡ ሰዎች ክርስቲያኖች ለስደት የሰጡትን ምላሽ በመመልከት ማመን ጀመሩ፡፡ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ጠርጡሊያኖስ እንደተናገረው “የሰማዕታት ደም የቤተክርስቲያም ዘር ነው፡፡” እነዚህ ሰዎች መሥዋዕቱን በመሠዋት ብቻ ከሞት ማምለጥ ይችሉ ነበር ነገር ግን ያንን በማድረግ ጌታን ከማቃለል ሞትን መርጠዋል፡፡ ይህ ሌሎችን ገድሎ መሞትን ከሚያስተምረው የእስልምና የሰማዕትነት አስተሳሰብ ምንኛ የተለየ ነው!

የፕሮቴስታንት ተሓድሶ

በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ነገሥታት ሕዝባቸው የእነርሱን እምነት ብቻ እንዲከተሉ ይፈልጉ ነበር፡፡ ብልሹ ሁኔታ ውስጥ የገባችው የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አውሮፓን ተቆጣጥራ የነበረች ሲሆን ከህትመት ማሽን መፈጠር ጋር ተያይዞ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ዕድል አግኝተው ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም ግን ጥቂት ሰዎች ብቻ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ዕድል የነበራቸው ሲሆን አብዛኞቹ ካህናት እንኳ ምን እንደሚል አያውቁም ነበር፡፡ በጀርመን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያስተምር የነበረ ማርቲን ሉተር የተባለ መነኩሴ የሮማ ቤተክርስቲያን አብዛኛው አስተምሕሮና ልማድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማማ አስተዋለ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱን ለማረም ቢሞክርም ጳጳሱ በመጨረሻ አውግዞታል፡፡ ለሉተር ጥበቃን ያደረጉለት የጀርመን ልዑላን ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሉተር ላይ ተፅዕኖ አሳድራለች፡፡

ዴቪድ ዳንኤልስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በተሐድሶ ላይ የነበራት ተፅዕኖ ብዙ ምሑራን ዕውቅናን ከሰጡት የላቀ ነው፡፡ በዳንኤልስ መሠረት ማርቲን ሉተር ተሓድሶን በጀመረ ጊዜ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከሮማ ካቶሊክ ጳጳስ ውጪ የምትገኝ ለሉተር ተሓድሶ እንቅስቃሴ ሕጋዊ መሠረት የሰጠች ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከሐዋርያት ዘመን ተያይዛ የመጣች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን መሆኗ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንደ የጌታ እራት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስና ጋብቻ የፈፀሙ ካህናትን የመሳሰሉ ልማዶች እንዳላት አስተውሏል፡፡ እነዚህም ነገሮች በሉተራን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡

በ1534 ዲያቆን ሚካኤል የተባለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ሉተርን ካገኘው በኋላ የኦግስበርግ የእምነት መግለጫ የተባለውን ተመልክቶ “ጥሩ የእምነት መግለጫ ነው” በማለት አፅድቆታል፡፡  በተጨማሪም ማርቲን ሉተር የጌታ እራት አቀባበል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ከዚህም የተነሳ የሉተራን አብያተ ክርስቲያናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጋር ሙሉ ሕብረት ያደርጋሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ከዊኪፒድያ የተገኘ ነው፡፡ https://en.wikipedia.org/wiki/Michael_the_Deacon

እንዲሁም በፕሮፌሰር ዴቪድ ዳንኤልስ ድረገፅ ላይ የገኛል፡፡ https://www.christiancentury.org/blog-post/guest-post/martin-luthers-fascination-ethiopian-christianity

ይህ ጊዜ ካቶሊክ ባለ ሥልጣናት ፕሮቴስታንቶችን የሚያሳድዱበትና አንዳንዴም ፕሮቴስታን ባለ ሥልጣናት ካቶሊኮችን የሚያሳድዱበት ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም በካቶሊክ ወገን እጅግ የከረረ ነበር፤ ለምሳሌ ያህል አሳቃቂ የነበረውን የእስፔን የማጥራት ዘመቻን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመጨረሻም ይህ ሁኔታ ወደ ግልፅ ጦርነት ተሸጋገረ፡፡

የቻይና ቤተክርስቲያን

የማኦ ኮሚኒስቶች ቻይናን በተቆጣጠሩ ጊዜ መጀመርያ ያደረጉት ክርስቲያኖችን ለመቆጣጠር መሞከር ነበር፡፡ የሚስዮናዊነትን ሐሳብ በመያዝ ቤተክርስቲያን ከዓለም አቀፍ ክርስቲያኖች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ ሞክረዋል፡፡ በሰሜን ቻይና የሚገኝ አንድ ሚስዮናዊ የሚስዮን ዋና ዓላማ ራሷን ችላ ራሷን የምትመራና ወጪዎችዋን በራሷ የምትሸፍን ቤተክርስቲያን ማቋቋም ነው የሚል አመለካከት በሰፊው ተቀባይነት እንዲኖረው አደረገ፡፡ የማኦ ተከታዮች ያንን ሐሳብ በመጠቀም ሚስዮናውያንን ያስወገዱ ሲሆን ክርስቲያኖችንም በሁለት ቤተ እምነቶች ስር ብቻ በመመደብ በአምላክ የለሾች ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ካቶሊኮች የቻይና አርበኞች ካቶሊክ ተብለው ከሮማ ጳጳስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ሁሉም ፕሮቴስታንቶች ደግሞ ሦስቱ ራስ ገዞች የሚል ስም ተሰጥቷቸው ወደ አንድ ተጨፍልቀዋል፡፡ እነዚህ ሁለቱም አምላክ የለሽ በሆነው የሃይማኖቶች ሚኒስቴር ስር እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ጋር ያልተስማማ የትኛውም አማኝ ይታሠራል፣ ይሠቃያል፡፡ አንዳንዶች ታስረዋል፣ አንዳንዶች ተገድለዋል፣ ሌሎች ደግሞ ፀረ አብዮት ተብለው ተደብድበዋል፡፡ ሦስቱ ራስ ገዞችን የሚመሩ መሪዎችም ከእነርሱ ጋር የማይስማሙትን ያሳድዱ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ይወድሙ ነበር፡፡ በወቅቱ ሁሉም ሚስዮናውያን የተባረሩ ሲሆን ወደ 2 ሚሊዮን ክርስቲያኖች እንደነበሩ ይነገራል፡፡

አማኞች ምን አደረጉ? ልክ እንደ ቀደመችዋ ቤተክርስቲያን በግል ቤቶች መሰባሰብ ጀመሩ፡፡ አንዳንዴ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሌላቸው በቃል ከሸመደዱት እየሰሙ ይጽፉ ነበር፡፡ ማኦ የባሕል ተሓድሶ ብሎ ሲጀምር ማናቸውንም ቤተክርስቲያኖች፣ መስጊዶችና ቤተመቅደሶች ሕገ ወጥ እንዲሆኑ አደረገ፡፡ ቻይና ምንም ዓይነት ሃይማኖት የሌለባት አምላክ የለሽ አገር መሆን አለባት አለ፡፡ ቤተክርስቲያን ግን አልጠፋችም፡፡ በርግጥ ማኦ ሞቶ ቻይና መጠነኛ ነፃነት ስታገኝ ከ 60-100 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ ቁጥርን አሳንሶ በመናገር የሚታወቀው የቻይና መንግሥት እንኳ ከሦስቱ ራስ ገዝ እንቅስቃሴዎች ውጪ የሚገኙ ክርስቲያኖች ቁጥር 45 ሚሊዮን እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

ዛሬ እንደገና የቻይና መንግሥት ቤተክርስቲያንንን፣ አልፎም ሙስሊሞችን ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት “መልሶ መማርያ” በተሰኙ ካምፖች ውስጥ እያጎራቸው ነው፡፡ በምዕራብ ቻይና ውስጥ በነዚህ ካምፖች ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ሙስሊሞች እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ የክርስቲያኖች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም፡፡ በቻይና ለሚገኙት ወንድሞችና እህቶቻችን መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ ከ1980ዎቹ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ይበልጥ ነፃነት የነበረ ይመስላል፡፡ አሁን ግን ልክ እንደ ማኦ ዘመን ነገሮች ዝግ እየሆኑ ነው፡፡

የኔፓልና የብሁታን ቤተክርስቲያን

የኔፓልን ቤተክርስቲያን ስጎበኝ ከብሁታን የመጡ ወንድሞችን የማግኘት ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ የሚደንቅ ምስክርነት አላቸው፡፡ ኔፓል የሒንዱ፣ ብሁታን ደግሞ የቡድሂስት አገራት መሆናቸውን አውጀዋል፡፡ የኔፓል ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢ እንደነገረኝ የኔፓል መንግሥት ኔፓላውያን ክርስቲያኖች መኖራቸውን ይክዳል፡፡ በ1960ዎቹ መጀመርያ ላይ በኔፓል ውስጥ 5 የታወቁ አማኞች ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ክርስቲያን መሪዎች ባስቀመጡት ግምት መሠረት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ አማኞች ይገኛሉ፡፡ ይህንን ለውጥ ያመጣው አብዛኛው የወንጌል ተልዕኮ ሥራ ከደቡብ ሕንድ በመጡ ሚስዮናውያን የተሠራ ነው፡፡ ድሮ ድሮ ፖሊስ ረጃጅም ዱላዎችን ይዞ ከቤተክርስቲያን ቅጥር ውጪ በመጠበቅ ሲወጡ እንደሚደበድባቸው ይናገራሉ፡፡ ፖሊሶች በደበደቧቸው ቁጥር አማኞች በብዛት ወደ ቤተክርስቲያን መሄዳቸውን ስለቀጠሉ በመጨረሻ ፖሊሶች ደክሟቸው ድብደባውን አቁመዋል፡፡ ዛሬ መንግሥት ዕውቅና ባይሰጣቸውም ክርስቲያኖች በቸልታ እየታለፉ ነው፡፡ እንዲያውም ክርስቲያኖች የሚሰበሰቡበት ቦታ የቤተክርስቲያን ጎዳና የሚል ስያሜን እስከማግኘት ደርሷል፡፡

እዚያው ጎረቤት የብሁታን መንግሥት የበለጠ ጥብቅ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይዛችሁ ከተገኛችሁ ወይንም ክርስቲያኖች መሆናችሁን ካሳወቃችሁ ንብረታችሁ በሙሉ ከናንተና ከቤተሰባችሁ ይነጠቃል፡፡ ትታሠራላችሁ፡፡ የኔፓል ክርስቲያኖች የብሁታን ክርስቲያኖችን በመርዳት ተጠምደዋል፡፡ ወንጌል እዚያም በነጻነት እንዲሰበክ ይጸልያሉ፡፡ የኔፓል ክርስቲያኖች ጌታ የሂማልያ ተራሮች አካባቢን እንደሰጣቸውና ያንን አካባቢ በወንጌል የመድረስ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡

የአልቤንያ ቤተክርስቲያን

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አልቤኒያ በራሺያ ኮሚንስቶች ተወስዳለች፡፡ ያ መንግሥት የሶቪየት ሕብረት በእስታሊን ዘመን ከነበረው በከፋ ሁኔታ ጨቋኝ ሆኖ ነበር፡፡ ገና ከጅምሩ ሃይማኖት ሕገ ወጥ መሆኑን በማወጅ መጽሐፍ ቅዱስን፣ ቁርኣንንና ሌሎች የሃይማኖት መጻሕፍትን መውረስ፣ አማኞችን ወደ ማሰልጠኛ ማጎርያዎች ማስገባት ተያይዞ ነበር፡፡ የአልቤንያ መሪዎች እንዲያውም የሶቪየት መሪዎች ደካማና ንፁህ ማርክሲሳውያን እንዳልሆኑ ይናገሩ ነበር፡፡

የአልቤንያ ቤተክርስቲያን ምን አደረገች? በአገሪቱ ውስጥ የነበረ ሰው ሁሉ አንዱ ሌላውን የመሰለል ግዴታ ስለነበረበት በቤቶች ውስጥ እንኳ መሰባሰብ አልቻሉም ነበር፡፡ ካልሰለላችሁና የሆነ ነገር ከተፈጠረ እናንተም ትቀጣላችሁ፡፡ ከዚህ የተነሳ የአልቤንያ ክርስቲያኖች መሪዎች፣ የመሰብሰብያ ቦታና መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖራቸው አልቻለም ነበር፡፡ ስለዚህ እሑድ ጠዋት ጠዋት በመንግሥት በታዘዘው መሠረት እስፖርት በሚሰሩባቸው ፓርኮች ውስጥ ይገናኙ ነበር፡፡ 2 ወይም 3 ሆነው በቡድን ተከፍለው የእግር ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው የእግር ጉዞ ስለሚያደርጉ ማንም አይጠረጥራቸውም፡፡ እነዚህ አማኞች በቃል የሚያውቁትን ጥቅስ ይነጋገራሉ፣ እየተጓዙም በጸጥታ ይጸልያሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የአልቤንያ ቤተክርስቲያን ከመሞት ይልቅ እያደገች ሄዳለች፡፡ የሚጨቆኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ የተለያዩ መፍትሄዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ከጦርነቱ በፊት እዚያ የነበረ ሚስዮናዊ ቤተክርስቲያኒቱን “የእግሮች ቤተክርስቲያን” ብሏታል፡፡

የኢራን (ፋርስ) ቤተክርስቲያን

 የኢራን ቤተክርስቲያን ታሪክ ከቤተክርስቲያን የምሥረታ ዘመናት ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ከእስልምና መነሳት በፊት ብዙ ሰዎች ክርስትናን ተቀብለው ነበር፡፡ እስልምና ከተነሳ በኋላም ቢሆን ጠንካራ ቤተክርቲያን ነበረች፡፡ በእርግጥ ወደ ቻይናና ሞንጎልያ የተጓዙ ቀደምት ሚስዮናውያን በአብዛኛው ከንስጥሮሳውያን ወገን የሆኑ ፋርሳውያን ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የዚህ ዘመን የኢራን ክርስቲያኖች አርመናውያንና አሦራውያን ናቸው፡፡

በ1976 አክራሪ የሺኣ አንጃ ኢራንን በተቆጣጠረበት ወቅት 168,593 የሚሆኑ ክርስቲያኖች እንደነበሩ ይገመታል፡፡ መንግሥት በጣም ጨቋኝ በመሆን የክርስቲያኖችን እንቅስቃሴ መገደብ ተያያዘ፡፡ የፋርስን ቋንቋ በማይናገሩ ክርስቲያኖች ላይ ሳይቀር ከባድ እርማጅ ተወሰደባቸው፡፡ ወደ ክርስትና የሚቀየር ማንኛውም ሰው ይገደላል፡፡ የኢራንና የሺኣዎች ዋና ቋንቋ በሆነው በፋርሲኛ ምንም ዓይነት ክርስቲያናዊ ጽሑፍ እንዳይኖር አያቶላህ እግድ ጣለ፡፡ በ1996 በመንግሥት የተተመነው የክርስቲያኖች ቁጥር 78,745 ነበር፡፡

የኢራን ወጣቶች ብዙ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ስደትና ጭቆና ከተመለከቱ በኋላ መከላከል ጀመሩ፡፡ ከዚህም የተነሳ ለወንጌል ልባቸውን መክፈት ጀመሩ፡፡ እስልምናን እንደ ጨቋኝ ይመለከቱት ጀመር፡፡ ብዙዎች ለምዕራባዊ እሴት ብቻ ሳይሆን ለክርስትናም ልባቸውን መክፈት ጀመሩ፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በድብቅ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ዕድገታቸውን ቀጥለዋል፡፡ አያቶላዎችም ወጣቶችን እንዲያስተምሩ ብዙ አስተማሪዎችን አሰማርተዋል፡፡ በመንግሥት ግምት መሠረት በ2011 ዓ.ም. 117,704 የሚሆኑ ክርስቲያኖች በኢራን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ቁጥራቸው 500,000 እንደሚሆንና በ2020 ከሕዝቡ 10 በመቶ የሚሆነው ክርስቲያን እንደሚሆን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ድብቅ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ምዕመናን እንዳላቸው ይፋ ቢያደርጉ ለአደጋ ስለሚጋለጡ ቁጥራቸውን ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ የኢራን ቤተክርስቲያን በእስልምናው ዓለም ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ይልቅ ፈጣን ዕድገት እያሳየች እንደሆነ መናገር ብቻ በቂ ነው፡፡

ከላይ ለተጠቀሱት ሁሉ መሠረታዊ የሆነ ስልት

ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ አማኞች የጥንካሬያቸው መሠረት ደቀ መዛሙርት መደረጋቸው ነው፡፡ አማኞች ደቀ መዛሙርት ባለመሆናቸው ምክያት ደካማ የሆኑባቸው አብያተ ክርስቲያናት በስደት ሰዓት ወደ ኋላ የሚመለሱት ይበዙባቸዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረበት ምሳሌ በጭንጫ ላይ ከወደቁት ዘሮች ጋር ተመሳሳይ ናቸው (ሉቃስ 8፡5-15)፡፡  በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ማርቲን ሉተር ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተገንጥሎ ሲወጣ አብዛኞቹ ተከታዮቹ ቀደም ሲል ተማሪዎቹ የሆኑ ነበሩ፡፡

ሌላው ምሳሌ በሰሜን ምዕራብ አፍሪካ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ከእስልምና ወረራ በኋላ የግብፅ ቤተክርስቲያን ሕያው ሆና ስትቀጥል እነርሱ ለምን ጠፉ? ለዚህ ከፊል ምላሹ የግብፅ ቤተክርስቲያን የአካባቢውን ሕዝብ በሚገባቸው ቋንቋ በቅብጥኛ አስቀድማ መድረሷ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን በሰሜን ምዕራብ አፍሪካ የነበረችው ቤተክርስቲያን በከተሞች ተወስና አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በላቲን ቋንቋ ትጠቀም ነበር፡፡ የገጠሩን ሕዝብ ለመድረስም ሆነ በበርበር ቋንቋ ለማስተማር ያደረገችው ጥረት በጣም አናሳ ነበር፡፡

ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ለመለወጥ መሞከር የለባችሁም፡፡ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ጀምሩ፡፡ ተግባራችሁ የጽድቅ ከሆነ ሰዎች ወደ እናንተ ይመጣሉ፤ ፍሬያማም ትሆናላችሁ፡፡

ማጠቃለያ

ገብቶ ወንጌልን ለመስበክ በጣም ከባድ ስለሆኑት አገራት ብዙ ጊዜ በሚስዮን ክበባት እንነጋገራለን፡፡ እነዚህን አገራት ደግሞ ሥልታዊ መግቢያን የሚፈልጉ አገራት እንላቸዋለን፡፡ በነዚህ አገራት ውስጥ ለመሥራት ሰዎች የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅመው ገብተው ይቀመጣሉ፡፡

አማኞች መከራን ለመቋቋም የተለያዩ መላዎችን መፍጠር የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ ተመሳሳይ ትክክለኛ መንገድ የለም፡፡ አንዳንድ መንገዶች ባለፉት ዘመናት ሠርተው ቢሆን እንኳ እግዚአብሔር ስለማይወሰን በነዚህ ስልቶች ብቻ ራሳችሁን አትገድቡ፡፡ መለኞች በመሆን ካጋጠማችሁ ሁኔታ ጋር አብራችሁ ለመራመድ ሞክሩ፡፡

ህቡዕ መሆን – ይህ ከዕይታ ውጪ ለመሆን የምንሞክርበት መንገድ ነው፡፡ የቻይና የቤት ለቤት አብያተ ክርስቲያናት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ትልልቅ ስብሰባዎችን አድርጎ ትኩረት ከመሳብ ይልቅ በትንንሽ ቡድኖች ተከፍሎ ድምፅን አጥፍቶ መንቀሳቀስ ይሻላል፡፡  የወንጌል ስርጭት ለማን እንምንናገር በማስተዋል በምሪት ይደረጋል፡፡ ባለ ሥልጣናት ብዙ ጊዜ ማን ይህንን እንደሚያደርግ ለማወቅ ሰላዮችን ይልካሉ፡፡ የአልቤንያ ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ ጥሩ ነበረች፡፡

ፅናት – የኔፓል ቤተክርስቲያን ይህንን ዘዴ ተጠቅማለች፡፡ ሐዋርያት በ 4፡19 ላይ ይህንን አድርገዋል፡፡ ይህንን መንገድ ስትጠቀሙ እጅግ ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት ያስፈልጋችኋል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 4 ላይ የተቀረውን የክርስቲያኖች ጸሎት ተመልከቱ፡፡ ሁኔታው እንዲወገድ ሳይሆን በሁኔታው ውስጥ ፅናት እንዲኖራቸው ነበር የጸለዩት፡፡

መብታችሁን መጠቀም – ጳውሎስ ከአደጋ ለማምለጥ የሮም ዜግነት መብቱን በተደጋጋሚ ተጠቅሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለ ሥልጣናት የበለጠ ጉዳት እርሱ ላይ ከማምጣት ይቆጠቡ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ሮም የሞት ፍርድ አስተላልፋበታለች፡፡

መሸሽ – አንዳንዴ ከመንገድ ዘወር ማለት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፡፡ ጳውሎስ ከደማስቆ ከተማ በቅጥሩ ላይ በቅርጫት ወርዶ ሸሽቷል፡፡ አንዳንዴ ታዋቂ አማኞች በአካባቢው መኖራቸው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ በቻይና በማኦ ዘመን ተደብቀው የቆዩ ምዕራባውያን ሚስዮናውያን ቤተክርስቲያንን ከመጥቀም ይልቅ ጎድተዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማሸነፍ ደቀ መዛሙትን ማፍራት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ሕልውናዋን ለማስቀጠል በውጪያዊ አካል ላይ የተደገፈች ከሆነች የስደትን ዘመን ለማለፍ ይሳናታል፡፡

አጋዥ ማፈላለግ – ለማርቲን ሉተር ጥበቃ ሲያደርግለት የነበረው የጀርመን ልዑል ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እናንተ ለምትሠሩት ሥራ ድጋፍ የሚሰጥ በሥልጣን ላይ ያለ ሰው ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ በቻይና ውስጥ የተመሰገነ ሥነ ምግባር ስለነበራቸው በባለ ሥልጣናት ጥበቃ ይደረግላቸው የነበሩ ሚስዮናውያን ነበሩ፡፡ በሙያቸውና በገንዘባቸው ሕብረተሰቡን ለማገልገል ይተጉ ስለነበር እንዲህ ያሉ ሰዎችን መጉዳት ሕብረተሰቡን መጉዳ ይሆናል፡፡ ለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መርህ እንዲህ የሚል ነው “መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው የሰማዩ አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ፡፡” (ማቴ. 5፡16)

የምናደርገውን ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ያስፈልገናል “ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባንን ይዛችሁ በፊቱ ግቡ፤ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።” (1ዜና 16፡29)