እግዚአብሄር አዳምና ሄዋን እንደሚበሉና እንደሚወድቁ ካወቀ ወይም እያወቀ በኤደን ገነት ውስጥ ዛፍ ተክሎ አትብሉ ለምን አላቸው? የዛፏ መኖር ለምን አስፈለገ? (መ. መ)
. . . . .
መ. መ.፥ ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። እኔም ራሴ ገና አዲስ ክርስቲያን በነበርኩባቸው በርካታ ዓመታት (አሁንም፥ ሁሌም አዲስ ክርስቲያን ነኝ) ደጋግሜ ጠይቄአለሁ። የዚህን ጥያቄ መልስ አንኳር የወሰድኩት መጀመሪያ መጻፍ ሀ ስል ከጻፍኩት (በኛ 1985) አዲስ ሕይወት የሚባል የትመማ መጽሐፍ ነው።
በመጀመሪያ የጥያቄው መነሻ የሆነውን ጥቅሱን በመጻፍ ልጀምር፤
እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ። ዘፍ. 2፥9። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍ. 2፥16-17።
የዛፏ መኖር ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄ አጭሩ መልስ ትርጉም ላለው የፍቅር ግንኙነት ነው።
በተን አድርጎ ለመረዳት ደግሞ የግንኙነትን መስፈርት መረዳትን ይጠይቃል። ግንኙነት ሲባል የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ኅብረት አስፈልጎት ነበር ማለት አይደለም። እርሱ በዘላለማዊ ግንኙነትና ኅብረት ውስጥ የሚኖር አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ሠለስቱ አካል፥ አሐዱ አምላክ ነው። እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን፥ ወይም እኔንና አንተን የፈጠረው እርሱ ኅብረት አስፈልጎት ሳይሆን እኛ ኅብረት ይኖረን ዘንድ ነው። ዮሐንስ ስለዚህ ኅብረት ሲጽፍ በ1ዮሐ. 1፥3 እንዲህ ይላል፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።
ኅብረት ከእርሱ ጋር ይኖረው ዘንድ ሰውን መፍጠሩ ድንቅ የቸርነት ሥራው ነው። ሰውን መፍጠሩ ምንም ግዴታ ኖሮበት ሳይሆን እንዲያው የቸርነቱና የነጎነቱ ብዛት ብቻ ነው። መፍጠሩ ደግሞ እንዲያው እንደ እንስሳ ሁሉ በልቶና ጠጥቶ፥ ወልዶና አሳድጎ፥ ኖሮና ሞቶ ያለ መታሰቢያ እንዲቀር ሳይሆን ትልቁን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ያደርግ ዘንድ ነው። ለዚህም ነው ከእንስሳት የለየውን የራሱን እስትንፋስ እፍ ያለበት። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ሰውን ከሌሎች ምድራውያን ፍጡራን ሁሉ ለይቶ ዘላለዋሚ ያደርገዋል፤ እግዚአብሔር ራሱ ዘላለማዊ ነውና።
ለግንኙነት ወይም ለኅብረት ደግሞ ፍቅርና ፈቃድ የግድ ያስፈልጋል። ለእንስሳዊ ግንኙነት ይህ አያስፈልግም። ለዚህ ደመ ነፍስ ብቻውን በቂ ነው። ለሰውና ሰው፥ እንዲሁም ለሰውና እግዚአብሔር ግንኙነት ግን ፍቅርና ፈቃድ ያስፈልጋሉ። ፍቅር ከፈቃድ የሚመነጭ ሲሆን ፈቃድ ራሱ ግን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሕይወት ቀጥሎ የሰጠው ትልቅ ስጦታ ይመስለኛል።
የዛፉ (መልካምና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ) መኖር አስፈላጊነት እንግዲህ እዚህ ላይ ነው። ይህ ግንኙነት በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ለመሆኑ ምስክር፥ መፈተሻ፥ ማረጋገጫ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ፈቅዶና ወድዶ ነው። በእርሱ በኩል ፈቃድ አለ፤ መውደድም አለ። አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወድዶአልና ነው ቃሉ የሚለን። በዚህ ኅብረት ውስጥ በአዳም በኩልም የፈቃድና የፍቅር ግንኙነት ሊኖር ግድ ነው። ወድዶ ፈቅዶ የሚገባበት ግንኙነት ነው፤ ካልፈለገ፥ ካልወደደና ካልፈቀደ ላይገባ መብት አለው። ፈቃድ አለውና። አዳምና ሔዋን በገነት ሲኖሩ ሙሉ ነጻነት ነበራቸው። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለመፈለግና ለመፈጸም፥ ኃጢአትንም ሳይሠሩ ለመኖር ችሎታ ነበራቸው።
እግዚአብሔር ሲጀመር አዳምንም፥ ዓለምንም ላይፈጥር ይችል ነበር። ዓለምም ባትፈጠር፥ እኛም ባንፈጠር ብለን እናስብ። ይህ ጥያቄም አይኖርም ነበር። ሌላው አማራጭ ዓለምን ፈጥሮ መልካምና ክፉ የሌለበት ማድረግ ወይም ስትፈጠርም መልካምና ክፉ የሚባል ነገር የሌለባት አድርጎ መፍጠር ነው። ይህ ደግሞ፥ ሁሉ ልክ የሚሆንበትና ትርጉም የሌለው እንስሳዊ ኑሮ እንደሚሆን መገመት አይሳነንም። ሌላው ምርጫ አዳምን መልካሙን ብቻ እንዲመርጥ አድርጎ መሥራት ነው። የዚህ ችግር ደግሞ ፈቃድ አልባነት ነው። አድርግ የተባለውን ያለ ምንም ምርጫ፥ ያለ ምንም ጥያቄ፥ አማራጭ ሳይኖር፥ ጥቅምና ጉዳት ሳይታወቅ፥ የግንኙነት ትርጉሙ ራሱም ሳይታወቅ፥ ልክ እንደ ሰው-ሠራሽ ሮቦት የተሠራበትን ተግባር ብቻ እንዲፈጽም፥ እንዲያደርግ ሆኖ ተሠራ ማለት ነው። ከሮቦት ጋር ግንኙነት መመሥረት አይቻልም። ሮቦት ነፍስና መንፈስ የለውም። ነፍስና መንፈስን መፍጠር የእግዚአብሔር ብቸኛ ሥልጣንና ችሎታ ነውና ሰው ነፍስን የመስራት ጥበብ ሊኖረውም አይችልም። የመጨረሻው አማራጭ በቃሉ ውስጥ የተጻፈውን አዳም መፍጠር ነው። ምርጫ ያለው፥ ፈቃድ ያለው፥ መታዘዝና አለመታዘዝ የሚችለውን፥ መውደድና አለመውደድ የሚችለውን አዳም መፍጠር። እግዚአብሔር ይህንን ነው ያደረገው። ማናችንም ከዚህኛው አማራጭ በፊት ያሉትን አማርጮች የምንፈልጋቸው አይመስለኝም።
ከአማራጮቹ ሁሉ እውነተኛ ኅብረትና ፍቅር ያለበት ግንኙነት ሊኖር የሚችለው በዚህ ፈቃድ ባለበት፥ ምርጫ ባለበት ግንኙነት ውስጥ ብቻ ነው። ምርጫ የመኖሩ አስፈላጊነት እግዚአብሔር የሚፈልገው በምርጫችን የምንግገዛለት ሲሆን ነው።
አዳምን ሲፈጥር ምንም ምርጫ ስለሌለው ሳይሆን ሙሉ የምርጫ ፈቃድ እያለው፥ ግን በፈቃደኝነት እንዲወድደው እግዚአብሔር ስለፈለገ በዔድን ገነት ውስጥ እንዳይበላ ያዘዘውን ዛፍ አኖረ። ይህም እግዚአብሔርን ታዝዞ በኅብረት እንዲኖር ወይም እግዚአብሔርን መታዘዙ በአዳም ፈቃድ ላይ እንዲመሠረት ስለወደደ ነው። አሳዛኙ ክስተት፥ አዳምና ሔዋን ለጥቂት ጊዜ (ምን ያህል መሆኑ አይታወቅም) እግዚአብሔርን ወደው ከተከተሉ በኋላ አለመታዘዝን መረጡ። እናም ውድቀት ሆነ። እዚህ ላይ፥ ‘ሰይጣን ባያስታቸው ኖሮ አይወድቁም ነበር፤ በመጀመሪያ ሰይጣን ለምን ተፈጠረ?’ ሊባል ይችላል። የዚህም መልስ ከላይ እንደተመለሰው ያለ ተመሳሳይ ነው። ሰይጣን ሲፈጠር ሰይጣን ሆኖ አልተፈጠረም፤ እርሱም እንደ ሰው ሁሉ ፈቃድ ያለው መልአክ ነበረ። እርሱም ፈቃዱን ተለማምዶ፥ አለመታዘዝን መርጦ የወደቀ ፍጡር ነው። ለአዳምና ሔዋን አለመታዘዝ ሳቢያው፥ ፈተናውን አቅራቢው ሰይጣን ሆነ እንጂ ውሳኔው የነ አዳም ነው። እምቢ ማለት ይችሉ ነበርና። ምርጫና ፈቃድ ነበራቸውና። ሰይጣን ባይፈትናቸውም ፈቃዳቸው አንድ ቀን ይጠይቃቸው ነበርና። የዛፉ (መልካምና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ) መኖር አስፈላጊነት እንግዲህ ለዚህ ነው።
ዘላለም።