ነገረ መለኮት እና መጽሐፍ ቅዱስ አቃቤ እምነት

የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች ነን? እንዴት? የእግዚአብሔር ልጆችስ ነን? እንዴት?

 

የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነት ጥቅስ በ2ጴጥ. 1፥4 የሚገኘው ነው። ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። 2ጴጥ. 1፥4

መጀመሪያ ያልሆንነውን ነገር እናስተውል።

  1. እኛ መለኮት አይደለንም። መለኮት አንድ ብቻ ነው። እኛ አማልክት አይደለንም። እኛ በምድር ላይ ውር ውር የምንል ትንንሽ እግዚአብሔሮች አይደለንም። መዝ. 82፥6 ላይ የሚገኘው፥ እኔ ግን፦ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ የሚለው ቃል ስለ አምላክ ሳይሆን ስለ ሰዎች እንደሚናገር ቀጥሎ ቁጥር 7 ላይ ያለው፥ ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ። የሚለው ቃል ይመሰክራል። አምላክ አይሞትምና እነዚህ ከሞቱ ቃሉ ስለ መለኮት አለመናገሩ መሆኑን እናውቃለን። ጌታም በዮሐ. 10፥34 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? ብሎ ሲጠቅስ ያንኑ አሳብ መግለጡ ነው። ቃሉ ኃያላን፥ ክቡራን ማለት ነው። ‘እነዚያ እንኳ እንደዚያ ከተባሉ፥ እኔ ከአብ የመጣሁት ያንን ብል ተገቢ ነው።’ ማለቱ ነው።
  2. እኛ በፍጥረታችን የመለኮት ባሕርይ የለንም። ስንፈጠር ሰዎች ነን እንጂ አማልክት ወይም መናፍስት አይደለንም። ሕይወት ያለን፥ የሕይወት እስትንፋስ እፍ የተባለብን፥ ሕያዋን ወይም ከተፈጠርንባት ቅጽበት ጀምሮ ዘላለማውያን የሆንን ሰዎች ነን። ይህ ስለ አዳምም ስለ እኛም፥ ወይም በአዳም በኩል ስለ እኛም ነው።
  3. የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነት በምንም መልክ የክርስቶስ እኩዮች ወይም አቻዎች አያደርገንም። ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፤ ወይም ከሥላሴ አካላት አንዱ ነው። እኛ ግን ፍጡራን እና ፍጡራን ብቻ ነን።
  4. የኛ ልጅነት ከክርስቶስ ልጅነት በሁሉ ረገድ፥ በመልኩም፥ በዓይነቱም፥ በደረጃውም የተለየ ልጅነት ነው። ግን ልጅነት ነው። እኛ ልጆች የተደረግን ልጆች ነን። ጌታ፥ ‘አባቴና አባታችሁ’ ሲል ይህንን ያሳያል። ‘አባታችን’ አላለም። “‘አባቴና አባታችሁ’ ሲል ያው አባት አንድ መሆኑን መናገሩ ነው፤ አይደል?” ሊባል ይቻላል። ልክ ነው፤ አባት አንድ ነው፤ አባትነቱ ግን የተለያየ ነው። ‘አባታችን ሆይ’ ብለን እንጸልይ የል?’ ሊባል ይቻላል። አዎን፤ ግን፥ ‘ብላችሁ ጸልዩ’ ነው ያለው። እዚያው ያንን ባስተማረበት ክፍል ውስጥ፥ ‘የሰማዩ አባታችሁ’ እያለም አስተምሯል፤ ‘የሰማዩ አባታችን’ አላለም። ለአይሁድ አባታችን እያለ ሳይሆን አባቴ እያለ መናገሩ ምን ማለቱ እንደሆነ፥ በግልጽ ራሱን ከአብ ጋር ማስተካከሉ እንደሆነ ገብቷቸዋል። ሊወግሩት የቃጡት አሳልፈውም የሰጡት ስለዚህ ነው። ይሁን እንጂ ልጆች ሆነናል፤ በመደረግ።
  5. እኛ ከፍጥረታችን ወይም በተፈጥሮአችን የአዳም፥ የወደቀው አዳም ልጆች ነን። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌ. 2፥3። እነዚያ ‘የአብርሃም ልጆች ነን’ እያሉ ለሚኩራሩት የአብርሃም ሳይሆን የዲያብሎስ ልጆች መሆናቸውን በግልጽ ነበር የነገራቸው፤ ዮሐ. 8፥39-44።

1ኛ፥ ልጆች ነን።
ልጅ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። የሥጋ ልጅ ልጅ ነው፤ ልጅ ናት። በቀጥታ ከወላጅ የተወለደም፥ በቀጥታ ሳይሆን የልጅ ልጅ የሆነም፥ ዘር የሆነም ልጅ እየተባለ ተጠርቶአል። ሁለቱ የዮሴፍ ልጆች፥ ለምሳሌ፥ የያዕቆብ ልጆች ተብለው ከ12ቱ ነገድ ጋርም ተቆጥረዋል። በሥጋ ያልተወለዱም ልጆች ተብለዋል፤ ያም ባሕርይን ገላጭ አሳብ ነው፤ የሚያስተራርቁ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለዋል፤ የእፉኝት ልጆች፥ የቁጣ ልጆች፥ የዲያብሎስ ልጆች ሲል በሥጋ መወለድን መናገሩ አይደለም። ምስስልን መናገሩ ነው። ምሳሌያዊና ባሕርያዊ ልጅነቶችም አሉ፤ ለምሳሌ፥ የነጎድጓድ ልጆች፥ እና የመሰሉትን አላወሳሁም።ልጅነት የግንኙነት ገላጭ ነው። በቀጥታ ብንወለድም ግንኙነት አለ፤ ልደቱ ወይም ልጅነቱ አካላዊ ባይሆንም ወይም ካልሆነም ግንኙነቱ ግን አለ። እስራኤል የእግዚአብሔር ልጅ ወይም በኵር ልጅ ሲባሉ የግንኙነት ጉዳይ የተሰመረበት ነው። ከአብርሃም ጋር የተገባ ኪዳንና ግንኙነት አለና፥ በጠቅላላው እንደ ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት ማዕከላዊው ቦታ ላይ የሚገኝ ነው።እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናችን እውነት በግልጽ የተጻፈ ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እኛ በጌታ የሆንን ቅዱሳን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ምንም ሳይንተባተብ ይነግረናል። የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይህን ግልጽ ነው። ልጆች ነን።ግን እንዴት ልጆች ሆንን? ይህ ትልቅ ጥያቄ ነው። የልጅነታችን ሂደትስ እንዴት ነው የተከናወነው? ልጆች የሆንንበት መንገድ ደግሞ አለ፤ ልጆች የሆንንበትን መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ በገላጭ ቃላት ይገልጠዋል።

ሀ፥ ስጦታ፤ ልጅነት ስጦታ ነው። ልጅነት ስጦታችን ነው። ስጦታ ይለዋል። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐ. 1፥12። ክርስቶስን ስንቀበለው የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን። ሰጣቸው ሲል የተሰጠ ሥልጣን መሆኑ ይታያል። የተሰጠን፥ የተቀበልነው ሥልጣን ነው። ቀድሞ እኛ ልጆች አልነበርንም፤ ሥልጣኑም አልነበረንም። ኋላ ግን ተሰጠንና ኖረን፤ እኛም ልጆች ሆንን።ይህ ስጦታ የተሰጠን በእምነት በኩል፥ ክርስቶስን በመቀበል ነው፤ በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ገላ. 3፥26። ስጦታ ከሆነ የተሰጠን ነን ማለት ነው። የተቀበልን ከሆንን የሰጠን አለ ማለት ነው። የተሰጠን ሆነን እንዳልተሰጠንና እንደተቀዳጀነው ሆነን የምንኮፈስበት ምንም ምክንያት ሊኖረን አንችልምም፥ የተገባም አይደለም። አስቀድመን የእግዚአብሔር ልጆች ያልነበርን የቁጣ ልጆች ነበርን፤ በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌ. 2፥3።

ልጅነት እውነት ነው፤ ልጅነታችን እርግጥ ነው። እርሱም በፍቅር የተሰጠንና በትሕትና የተቀበልነው ስጦታ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም። ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። 1ዮሐ. 3፥1-2። ልጅነታችን በፍቅር የተሰጠንና የተቀበልነው ስጦታ ነው። ስጦታ ሽልማት አይደለም። ሽልማት በሆነ ነገር በልጠን፥ ልቀን የምናገኘው የኛ ሥራ ያለበት የሌሎችን አድናቆት የምናገኝበት የሥራ ፍሬ ነው። ይህ የኛ ልጅነት ድንቅና ግሩምም ነው። ግንኙነት ነው፤ ሥልጣን አለበት፤ ወራሽነትም ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ስጦታና ስጦታ ብቻ ነው። ስጦታ ከሆነ ሰጪ አለ፤ ተቀባይ አለ። እኛ ተቀባዮች ብቻ ነን።

ለ፥ ዳግም ልደት፤ ልጅነታችንን ገላጭ የሆነው ሌላ ቃል ዳግም ልደት ወይም መንፈሳዊ ልደት ነው። ይህ ማለት መንፈሳችን ለብቻው ዳግም ተወልዶ ነፍሳችንና ሥጋችን ደግሞ በዝግመትና በትንሣኤ ዳግም ይወለዳሉ ማለት አይደለም። እኛ ኋላ የምንገጣጠም ቁርጥራጮች አይደለንም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁለንተናችንን ሰው ብሎ ይጠራዋል። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። . . . ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ዮሐ. 3፥3 እና 7። ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ነው ያለው። ዳግም መወለድን ከመንፈስ መወለድም ይለዋል፤ ቁጥር 5። ዳግመኛ መወለድን ከማይጠፋ ዘር በእግዚአብሔር ቃል መሆኑንም ይነግረናል፤ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። 1ጴጥ. 1፥23። እዚህ ዘር የተባለው ቃሉ ራሱ ነው። ይህ ዘር ቃሉ መሆኑን የምናገኘው ከቀጣዮቹ ሁለት ጥቅሶች (ከቁ. 24-25) ነው። ይህ ዳግመኛ መወለድ እንደገና መወለድ ነው። እዚሁ 1ጴጥ. 1፥3-4 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይላል። በሥጋ ስንወለድ የወላጆቻችን ልጆች እንደምንሆን እንደገና ወይም ዳግመኛ ስንወለድ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን። ይህ ልደት የመንፈስ ልደት ወይም መንፈሳዊ ልጅነት ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን መንፈስ መሆን አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት መወለድና የእግዚአብሔር ልጆች መሆን ነው። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ሮሜ. 8፥15። እዚህ ጥቅስ ውስጥም፥ ልጅነትን ወይም የልጅነት መንፈስን መቀበላችንን ይነግረናል። መቀበል ከኖረ ሰጪ አለ። መቀበል ከኖረ፥ ከመቀበል በፊት ያ ነገር በእኛ ዘንድ ያልነበረ ነገርና ኋላ የኖረ ነገር ነው።

ሐ፥ ሦስተኛው ልጆች መደረጋችን ነው።
ሦስተኛው ልጆች የመሆናችን ገላጭ ቃል ልጆች የመደረጋችን እውነት ነው። ቃሉን ከወደድን ማደጎ እንበለው፤ ከፈለግን ጉዲፈቻ እንበለው፤ ከፈለግን የእንግሊዝኛውን ወስደን adoption እንበለው፤ ቃሉ ቢጥመንም ባይጥመንም አሳቡ ግን ያ ነው። ይህንን ቃል በአዲስ ኪዳን በጳውሎስ ተደጋግሞ ተጽፎ እናገኘዋለን። ይህ የግሪክ ቃል υἱοθεσία ሁዮቴሲያ የተባለው ነው። ትርጉሙ ልጅ መደረግ፥ እንደ ልጅ መደረግ፥ ልጅ ተደርጎ መወሰድ ማለት ነው። በአዲስ ኪዳን ቃሉ በተጻፈባቸው ቦታዎች ሁሉ በጳውሎስ ነው የተጠቀሰው። ይህ ጳውሎስ ልጆች መሆናችንን አበክሮ የጻፈ ሐዋርያም ነው። እና ልጆች መሆናችንን ሲናገር ይህን ቃል መጠቀሙ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት እንጂ ባለማወቅ ወይ በመሰለኝ አይደለም። ልጅ መሆንና ልጅ መደረግ የሚጋጩ ሁለት ነገሮች አይደሉም። ሁለት የልጅነት እርከኖች ወይም ደረጃዎችም አይደሉም። ሁለቱም አንድ ልጅነት ናቸው።

ዳግም ልደት በሥጋ ከወላጆቻችን እንደተወለድነው፥ በዮሐ. 3 ጌታ ለኒቆዲሞስ እንዳብራራው፥ በመንፈስ ወይም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት መንፈሳዊው ማንነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ሲሆን ነው። ይህ ማለት ቀድሞ በአካላዊ ሕይወት ኖረንም ልጆች አልነበርንም ማለት ነው። በቲቶ 3፥5 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ይላል። እዚህ አዲስ ልደት (παλιγγενεσία) እንደገና መወለድ ነው። ቃሉ እዚህና ማቴ 19፥28 ብቻ የሚገኝ አዲስነትን ገላጭ ነው። ዳግም ስንወለድ አንዲስ ፍጥረት ነው የምንሆነው፤ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ቆሮ. 5፥17። ዳግም ልደት እና ልጅ መደረግ ያው አንዱ ነገር ነው በተለያዩ መግለጫ ቃላት የተገለጠው እንጂ ሁለት እርከኖች ወይም ደረጃዎች አለመሆናቸውን ደግመን እናስብ።

ልጅ መደረግ ለሚለው ቃል ጳውሎስ የጻፋቸው ጥቅሶች እነዚህ ናቸው፤

አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ሮሜ 8፥15።

እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። ሮሜ. 8፥23።

እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ ሮሜ. 9፥4።

ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ገላ. 4፥4-5።

በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። ኤፌ. 1፥5።

እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን። የሆንነው ደግሞ በመደረግ ነው። ተደርገን ነው። ማለትም፥ እግዚአብሔር ወድዶ ልጆቹ አድርጎን ነው። በፍጥረታችን ወይም በአፈጣጠራችን ልጆች አልነበርንም። እግዚአብሔር ግን ልጆቹ እንድንሆን ወደደና ልጆቹ አደረገን፤ እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበለን። ልጅነት የተፈጥሮ መብታችን አይደለም። ከተደረግን በኋላ ግን፥ ይህ ልጅነት ከተሰጠን በኋላ ግን፥ ልጅነት መብት ብቻ ሳይሆን ሥልጣንም ሆነ። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐ. 1፥12። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ስናስብና ስንደሰትበት፥ ልጆች የተደረግን መሆናችንንም አንዘንጋ። ልጆች የተደረግን ልጆች ነን።

በነገረ መለኮት፥ በተለይም በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ሰብዕ፥ የባሕርይ ልጅ እና የጸጋ ልጅ ሲባል ሰምተን እናውቅ ይሆናል። (የባሕርይ ተካፋይ ስለሚለው አሳብ ለብቻ እመለሳለሁ።) የባሕርይ ልጅ ሲባል ከአድራጊው ጋር አንድ መሆንን አመልካች ነው። ይህ ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የምንጠቀምበት የስነ መለኮት ቃል ወይም ሐረግ ነው። (እዚህ ላይ፥ የጳውሎስ ፈቃዱን የእግዚአብሔር ልጅ መጽሐፍ በጠቅላላው፥ በተለይ የኛን ልጅነት በተመለከተ ደግሞ በምዕራፍ 8 እና 9ን ተንትኖታልና፥ ይህንን እንድታነብቡ፥ እንድታነብቡ ብቻ ሳይሆን እንድታጠኑ፥ አደራ እላለሁ።) ባሕርይ የሚለውን ቃል ተፈጥሮ እንዳንለው ኢየሱስ ፍጡር አይደለምና የተፈጥሮ ልጅ አይባልም። (ሆኖም፥ አዲስ ኪዳን ይህንን ቃል በአንዳንድ ጥቅሶች ውስጥ ተፈጥሮም ይለዋል።) ሥሪት እንዳይባልም እርሱ ሠሪ እንጂ ተሠሪ አይደለምና ይህም አያስኬድም።

የባሕርይ ልጅ መሰኘቱ ወልድ እና አብ አንድ ባሕርይ ወይም በእንግሊዝኛ essence በግሪክ οὐσία ወይም ούσιος የተባለውን መሆናቸውን ነው። የኒቅያው ጉባኤ አብ እና ወልድ አንድ ባሕርይ ὁμοούσιος ሆሞኡሲዮስ ወይም ὁμοούσιον ሆኖኡሲዮን ያለው ያንን ነው። አብ የሆነውን ሁሉ ወልድም ነው፤ ኹነታችው በሁሉ አንድ ነው። በዚህ ረገድ እግዚአብሔርን የሚመስል እግዚአብሔር ብቻ ነው። አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አንድ ናቸው። እግዚአብሔርን በዚህ ማንነቱ ከፍጥረት ወይም ከፍጡር የሚመስለው ምንም፥ ማንም የለም። ሰውን በመልኩና በምሳሌው መፍጠሩም ሰውን የመለኮት ባሕርይ አያላብሰውም ወይም አያቀዳጀውም። ሰው ሲፈጠር ሰው እንጂ፥ የተሰጠው ሥልጣን አለው እንጂ አምላክነት የለውም። መንፈሳዊነት አለው እንጂ መንፈስ አይደለም።

እግዚአብሔር መንፈስ ነውና መልክና አምሳል ሲባል እንደ አካል መልክ አድርገን መውሰድ የለብንም። ይህ መልክና ምሳሌ ምንም አካላዊነት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን በሰውኛ አኳኋን ቢገልጠውም የሰው ዓይነት አይደለም። ስንዝር፥ ዓይኖች፥ ክንድ፥ ጀርባ፥ መሳቅ፥ መጸጸት፥ ወዘተ፥ በመሰሉ ቃላት ቢገልጠውም፥ ይህ ለሰው መረዳት ቃሉ የተጠቀመበት አገላለጥ ነው፤ anthropomorphism ይባላል፤ ስብዕናን ማላበስ ይባላል። ይህ ለእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለግዑዛን ነገሮችም ይደረጋል። ወንዞች ሲያጨበጭቡ፥ ተራሮች ሲዘልሉ፥ ፀሐይ እንደ አርበኛ ሲወይም ሮጥ ወዘተ፥ የዚህ ዘር ነው።

እኛ በባሕርይ፥ በፍጥረት፥ ወይም በሥሪት የምንመሳሰለው ከአዳም ጋር ነው፤ በቀጥታ ልጁ የምንሆነውም የአዳምን ነው። ከአዳም ጋር ፍጹም አንድ ነን። በኃጢአት ከመውደቃቸው በፊት ከነበራቸው ንጽሕና በቀር አንድ ነን። አዳም ሲፈጠር ሰው እንጂ አምላክ አልነበረም። ሰው እንጂ መንፈስም አልነበረም። ፍጡር እንጂ ልጅም አልነበረም። እኛም ቀድሞ ልጆች አልነበርንም። በሆነ ጊዜ ግን ሆነን ተገኘን። በራሳችን አልሆንንም፤ ግን ተደረግን። ከላይ እንዳልኩት፥ ቃሉን ማደጎ እንበለው፥ ጉዲፈቻ፤ ወይም የእንግሊዝኛውን adoption እንውሰድ ወይም በሌላ በምናውቃቸው ቋንቋዎች እንጥራው ነጥቡ ልጆች ያልነበርን እኛ ልጆች #መደረጋችን፥ እንደ ልጆች መሆናችን፥ ልጆች መሆናችን ነው።

እኛ ቀድሞ ወገን አልነበርንም፤ ኋላ ግን ወገን ሆንን፤ ምሕረት ያገኘን አልነበርንም፤ ምሕረት ያገኘን ሆንን። እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። 1ጴጥ. 2፥10። ወገን ያልነበርነው ወገን ከሆንን፥ ተደረግን ማለት ነው። ቀድሞም ወገን የነበረ ሰው ወገን አይደረግም። ለምሳሌ፥ ለአጎቶቼ እኔ የወንድማቸው ወይም የእኅታቸው ልጅ ነኝ። ስወለድ ጀምሮም ወገን፥ ዘመድ ነኝ። ሊያደርጉኝ አይችሉም ቀድሞም ነኝና። ያልሆነ፥ ያልነበረ ሲደረግ ግን ያ ሌላ ነገር ነው። ደግሞም ይቻላል። በተለያዩ ባህሎች አንድ ወይ ሌላ ሥርዓት ይፈጸምና ዝምድና ይፈጠራል። ይህ የጋብቻ ዝምድናን አይጨምርም። አንድ ምሳሌ ብንወስድ፥ በአገራችን የጡት ልጅ የሚባል ልጅነት አለ። በሥርዓቱ ጡት ሳይሆን ጣት ነው የሚጠቡት። ግን አንድ ጡት ጠብተው ያደጉ ወንድማማች ወይም ወንድምና እኅት ይሆናሉ። በአንዳንድ ባህሎች ጣትና ጣት ተበጥቶ ደም ይደማና ደምና ደም ተነካክተው የሥጋና ደም ዘመድ ሆኑ ይባላል። እነዚህ ልጅ ወይም ዘመድ ያልሆኑ ወገን ሲደረጉ ነው። ጉዲፈቻ ከነዚህ ዓይነቶቹ አንዱ ወገንነቶች ወይም ልጅነቶች ነው።

እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከመሆናችን በፊት ልጆች አልነበርንም። ሳንሆን ኖረን፥ ስንሆን ያልነበርነውን ነው የሆንነው። ልጅ ነው የሆንነው። የሆንነውም በመደረግ ነው። ልጅነት ማንነታችን ነው። መደረግ ደግሞ የተደረግንበት መንገድ ነው። በብሉይ ኪዳን ልጆች ሳይሆኑ እንደ ልጅ መቆጠርም ልጆች ሆነው እንደ ሌላ ልጅ መቆጠርም አለ። ለሁለቱም አንድ አንድ ምሳሌ ላሳይ፤ ኤፍሬምና ምናሴ የዮሴፍ ልጆች ናቸው፤ ያዕቆብ ግን እንደ ራሱ ልጆች አድርጎ ወሰዳቸውና ከ12ቱ ነገድ ጋር ተቆጠሩ፤ ዘፍ. 48፥5-6። ልጅ ሆኖ ስላለመሆን ምሳሌ ደግሞ፥ በብሉይ ኪዳን የዋርሳ ሕግ የሚባል አለ። ባል ሳይወልድ ከሞተ የባል ወንድም ሚስቲቱን የራሱ አድርጎ ይወስዳል። ቢወልድም ልጆቹ ወይም ልጁ በሞተው ስም ይጠራል፤ የሟቹ ስምና ርስትም አይቋረጥም፤ ዘዳ. 25። ልጅ ሆኖ ልጅ አለመሆንም፥ ልጅ ሳይሆኑ ልጅ መሆንም አለ።

ጴጥሮስ በ1ጴጥ. 2፥10 ወገን ሳይሆኑ ወገን መሆንን የጠቀሰው ከሆሴዕ ትንቢት (ሆሴ. 1-2) የተወሰደ አስገራሚ የፈረሰና የታደሰ ግንኙነት ምስልም ታሪክም ነው። ይህ የኛ ወገንነትም ምስል ሆኖ በአዲስ ኪዳን በጴጥሮስ የተጠቀሰው ነው። የኛ ታሪክ የኛ ልጅነት ነው። የኛ ልጅነት ድንቅና ግሩም ነው። የኛ ልጅነት ሥልጣን ነው፤ ወራሽነትም ነው። ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ በኩል የተመሠረተ ግንኙነት ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ልጅነታችን በበጎነቱ የተሰጠን፥ የተቀበልነው ስጦታና ስጦታ ብቻ ነው እንጂ የተቀዳጀነው ድልና መብት አይደለም። አንዳንድ የሐሰት አስተማሪዎች ይህንን እኛ በበጎነቱ ልጆች የተደረግንበትን ቸርነት ከክርስቶስ ልጅነት ጋር እያነጻጸሩ፥ የኛ ልጅነት እና የእርሱ ልጅነት የመንትያ ያህል አንድ እንደሆነ ሲናገሩና የሰዎችን እምነት ሲገለብጡ ማየት ምንኛ አሳዛኝ ነው!

ቀድሞ አባታችን ያልሆነ አባት የሌላው ልጆች የነበርነውን ልጆች አድርጎ ከተቀበለን የምን ልጅ ትባላለህ? የባሕርይ ልጅ አይደለንም። የባሕርይ ልጅ የሚባል ስለኛ የተነገረ ቃል ከቶም የለም። 1ጴጥ. 1፥4 የባሕርይ ተካፋዮች እንድንሆን በተስፋ ቃል መደረጋችንን ይናገራል። ይህንን በቀጣዩ እንመለከታለን።

  1. የባሕርይ ተካፋዮች

የልጅነታችን ሂደትስ እንዴት ነው የተከናወነው? የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው በተፈጥሮአችን ወይም በፍጥረታችን ሳይሆን እግዚአብሔር እንደ ልጆች አድርጎ ተቀብሎን ነው። ልጅነት የተሰጠን ስጦታ ነው እንጂ ከወላጆቻችን ስንወለድ በተፈጥሮ እንዳገኘነው ያለ መወለድ አይደለም። ቀደም ሲል ካየናቸው ጥቅሶች አንዱ በገላ. 4 የሚገኘው ነው። ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። ገላ. 4፥4-7።

ይህ ጥቅስ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ እና ልጆች እንደሆንን በግልጽ ይናገራል። የእግዚአብሔር ቃል በማያሻማ መንገድ ልጆች መሆናችንን ይመሰክራል። ልጆች ነን። ልጆች የሆንነው ደግሞ ምንም የራሳችን ፍሬ ኖሮን ሳይሆን እግዚአብሔር ልጁን እንዲዋጀን ልኮት በእርሱ የዎጆ ሥራ በኩል ነው ልጆች የሆንነው። እርሱን ስንቀበል ልጆች ሆንን። ልጆች የሆንነው እግዚአብሔር ልጆቹ አድርጎን ነው። እንጂ በልጁ በኩል ከራሱ ጋር ባያስታርቀን ኖሮ፥ በራሳችንማ ጠላቶች ነበርን። ቃሉ ልጆች መሆናችንንም ልጆች የሆንነው በመደረግ መሆኑንም ይነግረናል። እነዚህ ሁለቱ እርስ በርስ የሚጋጩ አይደሉም።

ልጆች የሆንነው ልጆች ተደርገን ተወስደን ነው። ከሆንን እና ከተደረግን፥ አድርጎ የወሰደን አለ ማለት ነው። ልንሆን ተወስነን ከሆነ የወሰነ አለ ማለት ነው። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። ኤፌ. 1፥5። ይህ ቃል አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ υἱοθεσία ሁዮቴሲያ መሆኑንም አይተናል። ልጅ መሆን፥ ልጅ መደረግ፥ እንደ ልጅ መወሰድ ማለት ነው። እኛ በክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር ልጆች ተደርገናል። ታዲያ ተደርገናል የሚለው ያልበቃቸው ሰዎች ከክርስቶስ ጋር እኩያ የሆኑ ልጆች እንደሆኑ ራሳቸውን ያሳብጣሉ። ልጅነት ሥልጣን ቢሆንም (ዮሐ. 1፥12) በሥልጣናችን የተቀዳጀነው ሥልጣን ሳይሆን የተሰጠን ሥልጣን ነው። ይህንን υἱοθεσία ሁዮቴሲያ የሚለውን ቃል ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች the adoption of sons ወይም the adoption of children ብለው ተርጕመውታል። ትክክለኛ ትርጉም ነው። አንዳንድ ሰዎች ማደጎ እና ጉዲፈቻ የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ። ይህ ቃል በአገራችን አሉታዊ የሆነ ምስል ስለሚቀርጽ ለአንዳንዶች ግራ ያጋባል። ያጋባ እንጂ ነገሩ ግን ያ ነው።

በአገራችን ባህል ቃሉ አሉታዊነት የተጫነው ይሁን እንጂ፥ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ዘመንና ዐውድ ይህ ቃልና ልማድ ግን ድንቅ ነገር ነው። በአገራችን ማደጎ ተደርገው የሚወሰዱ ልጆች፥ ችግረኞች፥ አሳዳጊ ያጡ፥ ምስኪኖች፥ ድሀ አደጎች፥ ወላጅ አልባዎች ናቸው። እንደዚህ ብቻ ብንወስደውም እንኳ ትርጉሙ ያስኬዳል። እኛም እኮ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች ከመሆናችን በፊት ምስኪኖችና ከጸጋ የራቅንና ከክብሩ የጎደልን፥ የወደቅን፥ የሞትን ሙታን ነበርን! ጳውሎስ ይህንን በጻፈበት የግሪክ ወሮሜ ባህልና በአዲስ ኪዳን ዘመን ችግረኛ ሕጻናት ብቻ ሳይሆኑ ትልልቅ ሰዎችም ልጆች ተደርገው ይወሰዳሉ። ወሳጁ ሰው ደግሞ ልጆች የሌሉት ወይም ያሉትም ሊሆን ይችላል። ልጆች ከሌሉት ያንን ልጅ አድርጎ የወሰደውን ሰው ወራሹ ሊያደርገው ከመፈለጉ በጎነት የተነሣ ብቻ ነው ልጅ የሚያደርገው። ልጆች ካሉትም አብሮ ወራሽ እንዲሆን፥ የልጆቹ ወንድም እንዲሆን፥ ቸርነቱ እንዲበዛ ሲል ልጁ ያደርገዋል፤ እኩል መብትም ያቀዳጀዋል። ልጁም በስሙ ይጠራል። ይህ የበጎነት ምልክት ነው።

እግዚአብሔር እኛን ልጆቹ ያደረገን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ነው። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። ኤፌ. 1፥5-6።

የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነትስ?

የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ ወደሚለው አሳብ እንምጣ። የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነት ጥቅስ በ2ጴጥ. 1፥4 የሚገኘው ነው። ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። 2ጴጥ. 1፥4

የአማርኛው ትርጉም ገና ሲጀምር በዓለም የሚገኝ ጥፋትን የሚያመጣ ክፉ ምኞትን በመግለጥና ከዚያ ማምለጥን በመናገር ይጀምራል። መለኮት መለኮት መጫወት የሚያምራቸውን ሰዎች ስናይ መጀመሪያ የምናስተውለው ነገር፥ ከዚህ ክፉ ምኞትና ዓለማዊ ጥፋት የራቁ ሳይሆኑ የተጣበቁ መሆናቸውን ነው። ከዓለምና የዓለም ከሆነ ነገር ጋር እየተጫወቱ የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነትን ማውራት ይመቻል? አይመችም። ዓለምን እንደ ሙጫ ተጣብቀውባት፥ ስጋዊነትን ተላብሰው፥ ገንዘብን እንደ ውኃ እየተጠሙና እየጠጡ የባሕርይ ልጆች ነን ሲሉ ያስደነግጣል።

የመለኮት ባሕርይ በሚለው ሐረግ ውስጥ፥ ‘መለኮት’ ግልጽ አሳብ ስለሆነ፥ ‘ባሕርይ’ የሚለውን ቃል እንመልከት። መለኮት አምላክነት ነው። አምላክ አንድ ብቻ ነውና እኛ በፍጥረታችን አምላክነት የለንም። ባሕርይ የሚለው ቃል በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ φύσις ፉሲስ ወይም ፊሲስ የሚል ነው። ቃሉ ምን ማለት እንደሆነ በሌሎች የተጠቀሰባቸው ቦታዎች ማየት ተገቢ ነው። ቃሉ በአዲስ ኪዳን ወደ 11 ጊዜያት ተጽፎአል። አራቱ ጥቅሶች ባሕርይ ሲሉ የቀሩት ፍጥረት ይሉታል። ፍጥረት የሚለው ቃልም አሳቡን ይገልጠዋል።

2ጴጥ. 1፥4 ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።

ሮሜ 1፥26-27 ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ ስለምንድር ነው የሚናገረው? ሴቶች ፍጥረታቸውን ወይም ሴትነታቸውን ትተው ከሴትነታቸው ሌላ፥ የሴትነት ባሕርይ ወይም ተፈጥሮ ያልሆነውን ሌላ ለመሆን መሞከራቸውን ነው። ባሕርይ የተባለው የተፈጠሩበት ነገር ወይም ፍጥረታዊ ማንነት ወይም ውስጣዊ ማንነት ነው።

ሮሜ 2፥14 ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ ይህም የሚያሳየው ሰዎች ሰዎች ብቻ ስለሆኑ መለኮታዊውን ተሻጋሪ ሕግ ወይም የሕሊና ሕግ ሊኖሩት ሊታዘዙት በውስጣቸው እንደሚያውቁት ይገልጣል። ይህ ባሕርይ የተሰኘው ነገር የውስጥን ማንነት ገላጭ ቃል ነው። ለምሳሌ፥ አትግደል የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ያልሰማና ያልተማረ ሰው፥ በፍጥረቱ መግደል መጥፎ መሆኑን ያውቃል።

ገላ. 4፥8 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ ገላ. 4፥8 በባሕርይ አምላክ አለመሆን ግልጽ ነው። ምንም አምላክ የለም፤ ከአንዱ በቀር። አምላክ ተደርጎ የሚመለክ የለም ማለት አይደለም። ግን ያ ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም። ወይም መለኮት አይደለም። እነዚህ ጣዖታት ፍጥረቶች፥ ፍጡራን፥ ወይም አጋንንት፥ ወይም የሰው እጅ ሥራ የሆኑ ቅርጻ ቅርጽ ናቸው እንጂ አምላክ ወይም መለኮት አይደሉም። በባሕርያቸው፥ በማንነታቸው ወይም በምንነታቸው አማልክት አይደሉም። ውስጣዊ፥ የራሳቸው የሆነ፥ ፍጥረታቸው የሆነ፥ አምላክነት የላቸውም።

ይህ φύσις የተባለው ቃል ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች ውስጥ ባሕርይ ተብሎ ሲተረጎም ወይም ሲሰኝ በተቀሩት ቃሉ በተጠቀሰባቸው ጥቅሶች በሮሜ 2፥27፤ 11፥21 እና 24፤ 1ቆሮ. 11፥14፤ ገላ. 2፥15፤ ኤፌ. 2፥3፤ ያዕ. 3፥7፤ ይኸው ተመሳሳይ ቃል (φύσις) በአማርኛ ፍጥረት እየተባለ ተተርጕሞአል። ፍጥረት ውስጣዊ ማንነት ነው። ባሕርይን በሚገባ ይገልጠዋል። ደስታ ተክለ ወልድ ባሕርይን ሲተረጕሙ፥ ‘ያልተፈጠረ፥ የማይመረመር፥ የማይታወቅ፥ ኅቡእ፥ ረቂቅ፥ ቅድስት ሥላሴን አንድ የሚያደርግ፥ በሥርው፥ በጕንድ፥ በነቅዕ የተመሰለ፤ የፈጣሪ ባሕርይ፤ አምላክነት’ ይሉታል። ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 162። ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች ውስጥ ባሕርይ የሚለው ውስጣዊ ማንነት ወይም ኹነትን ነው።

ቀደም ሲል በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ሰብዕ፥ የባሕርይ ልጅ እና የጸጋ ልጅ የሚለውን ስንመለከት የባሕርይ ልጅ ሲባል ከአድራጊው ጋር አንድ መሆንን አመልካች ነው። ይህ ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የምንጠቀምበት የስነ መለኮት ቃል ወይም ሐረግ ነው። ባሕርይ የሚለው ቃል በአንዳንዶቹ φύσις የሚለው ቃል በተተረጎመባቸው ቦታዎች ተፈጥሮ ቢባልም፥ ለመለኮት ተፈጥሮ እንዳንለው ማሰብ አይመችም። ኢየሱስ ፍጡር አይደለምና የተፈጥሮ ልጅ አይባልም። ሥሪት እንዳይባልም እርሱ ሠሪ እንጂ ተሠሪ አይደለምና ይህም አያስኬድም። ኢየሱስ የባሕርይ ልጅ መሰኘቱ ወልድ እና አብ አንድ ባሕርይ ወይም በእንግሊዝኛ essence በግሪክ οὐσία ወይም ούσιος የተባለውን መሆናቸውንና የኒቅያው ጉባኤ አብ እና ወልድ አንድ ባሕርይ ὁμοούσιος ሆሞኡሲዮስ ወይም ὁμοούσιον ሆኖኡሲዮን መሆናቸውን ለመግለጥ እንደተጠቀመበት ተመልክተናል።

ቃሉ አንድ ዓይነትነትን ገላጭ ነው። ὁμός ሆሞ ወይም ሆሞስ አንድ ወይም አንድ ዓይነት ወይም ምንም ልዩነት የሌለው ተመሳሳይ፥ οὐσία ኡሲያ ባሕርይ። ይህንን ὁμοούσιος የሚለውን ሐረግ ወደ እንግሊዝኛ “consubstantial” ብለው ነው የተረጎሙት። ይህ የኒቅያ ጉባኤ አርዮስ የተወገዘበት ጉባኤ ነው። አርዮስ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ወይም እኩል ያልሆነ ከሰው የሚበልጥ ከአብ ግን ያነሰ ወይም ሙሉ መለኮት ያልሆነ ያደርገዋል። (አርዮሳውያን የሆኑ የዘመናችን የዋችታወር ተከታዮች ወይም የይሆዋ ምስክሮች ነን የሚሉ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ወይም እኩል ያልሆነ ከሰው የሚበልጥ ከአብ ግን ያነሰ ወይም ሙሉ መለኮት ያልሆነ የተፈጠረ ፈጣሪ ያደርጉታል።) ኋላ በ381ዱ የቁስጥንጥንያ ጉባኤም ይኸው መግለጫ ጸና።