ይህ ጽሁፍ በወንድም ረታ ጳውሎስ የተጻፈ ነው፤ በጸሃፊው ፈቃድ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል፤
ክፍል 4
ባለፉት ክፍሎች እንዲሁ በግርድፉ የዘመናችንን ቤተ ክርሰቲያን የዝማሬ አምልኮ ሥርዓት ግድፈቶች እና መሰናክሎች በማንሳት ለመነጋገር ሞክረናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ባሉ ክፍሎች የአምልኮ ትርጉም፣ መርህ እና አላማ በአጭር በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ “አምልኮ” የሚለው ቃል ውስጥ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን እናስተውላለን፤ አምላክ፣ መስዋዕት እና አምላኪው፡፡ ሶስቱ ጉዳዮች በአግባቡ ተሳልጠው ልከኛ ቦታቸውን ካልያዙ አምልኮ የሚባለው ነገር ክሳቴ አይኖረውም፡፡ አምላክ (Object of Worship) ሲሆን አምልኮን ተቀባይ ወይም የድርጊቱ መንስኤ፣ ዋና ምክንያት ነው፡፡
“አምላክ ስላለ ነው አምልኮ የኖረው!”
በማንኛውም ሀይማኖት እና እምነት (ቃልቻ፣ ቦረንትቻ፣ ሌላም ቻ..) የአምልኮ ነገሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እኛ የምንነጋገረው ስለ ዓለማቱ ፈጣሪ ታላቁ አምላክ ዘለዘለማዊው እግዚአብሔር ነው፡፡ መስዋዕት ለአምላክ የሚሰጥ ስጦታ ወይም ምላሽ ሆኖ የሚቀርብ ጥልቅ ፍቅር፣ እምነት፣ ከፍተኛ አድናቆት (ውዳሴ)፣ ፍርሃት (እየወደድነው እንፈራዋለን)፣ መንቀጥቀጥ (የአክብሮት ጥግ)፣ መንዘፍዘፍ፣ ድንጋጤ (ሰቦማይ ይላል ግሪኩ)፣ ራስን እስከ መሳት ያለ ከፍተኛ አድናቆት (ራዕይ 1፡17)፣ መገዛት ሲሆን፥ ይህ ደግሞ በሶስት ምልዓተ ደርዝ ይገለጣል፡፡
- የሀሳብ አምልኮ (Worship in Thinking)
- የአንደበት አምልኮ (Worship in singing or speech)
- የሥራ አምልኮ (Worship in action)
- የሀሳብ አምልኮ ምንድነው?
ስለ አምላካችን እግዚአብሔር በልባችን ያለው ፍቅር፣ አክብሮት፣ ፍርሃት፣ አድናቆት እና እምነት ነው፡፡ ሀሳብ በጣም የሚገርም ፍጥረት፣ የማንነታችን ክፍል ሲሆን ለሰዎች ሊታይ ፈጽሞ የማይችል የአዕምሮ ቀመር ነው፡፡ በዓለም ያሉ ጠቢባን ሳይነቲስቶች የሰውን የተለያዩ የአካል ክፍሎች በዝርዝር የሚያሳዩ፣ የመጠቁ መሳሪያዎችን ሰርተዋል፡፡ የጭንቅላት ዕጢ፣ የደም መፍሰስ፣ የነርቭ ችግሮችን፣ የተሰበረ አጥንት… ወዘተ ለማየት ችለዋል፡፡ CT SCAN, MRI, X-RAY, ULTRASOUND… ብዙ ነገሮችን ማሳየት የቻሉ የሰው ልጅ ረቂቅ የጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢራቀቁ የሰውን ሀሳብ ለማየትና ለመገንዘብ አልቻሉም፡፡ ሃሳባችን በማንም አይታይም ለዚህም ነው እንደ ፈለግን የምናስበው፡፡ ከሰዎች ጋር አብረን ስንኖር እርስ በርስ ሀሳባችንን መተያየት የምንችል ቢሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ስለ ባልንጀራችን የምናስበውን ሁሉ የሚያውቅ መሳሪያ ቢኖር በእውነት በምድር እንኖር ነበር ወይ?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሀሳብ ምን እንደሚል ጥቂት ብቻ እንመልከት፡፡
ኢያሱ 1፡8 የዚህ ህግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ…በቀንም በሌሊትም አስብ፤ ያን ጊዜ መንገድህ ይቀናልሃል፡፡
መዝ. 1፡2-3…በእግዚአብሔር ህግ ደስ ይለዋል፣ ህጉንም በቀን እና በሌሊት ያስባል እርሱ በውሃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፣ የሚሰራውም ሁሉ ከናወንለታል።
ፊል. 4፡8 በቀረውስ ወንድሞች ሆይ…አስቡ
ቆላ 3፡1 በላይ ያለውን አስቡ እያለ ምን ያህል ሀሳባችን ከፍ ያለ ንጹህ እና ቅን ሊሆን እንደሚገባው ቃሉ በአጽንኦት ይናገራል፡፡
አምልኮ ስለ እግዚአብሔር በልባችን ከምናስበው በጎ ነገር ካልጀመረ ይፈርሳል!! ‹‹በሀሳብህ ያላከበርከው ጌታ መድረክህ ላይ አይከብርልህም››!! በልብህ ያላነገስከው ጌታ ድንገት በደመቀ ተቀጣጣይ ዝማሬ አይነግስልህም! የጊታርህ ክር፣ ድምጽህም ቢቃኝ ሀሳብህ ካልተቃኘ ፈርሷል! ዛሬ ሀሳባችንን የሞላው ነገር ምን ይሆን? ሀሳባችን እና መዝሙራችን ይተዋወቃሉ?፣ ይቀራረባሉ? ወይስ በየፊናቸው እየተመሙ ነው? በቀን እና በሌሊት የምናስበው ጉዳይ በመድረክ እና በጉባኤ ከምንዘምራቸው ዝማሬዎች ጋር በእውነት ዝምድና አለው ወይ? ካልሆነ ድርሰተ ተውኔት እየተወንን ብቻ እንጂ እያመለክን አይደለም፣ አፍርሰናል፡፡ በዋልድባ የዘፈነ ዲያቆን አፍርሷል እንደሚባለው እንዲሁ ልንዘፍን አይገባም፡፡ የሀሳብ ጥራት በሌለበት የአንደበታችን ስል ንግግር ሆነ ዜማ እግዚአብሔርን ሊያስደስተው አይችልም፡፡
ምስጋናችን ጥልቅ እንጂ ግልብ ሊሆን አይገባም፡፡ “ግልብ” ምስጋና ቆሌ የሌለው እንዲሁ የሙዚቃ ምት እየተከተሉ የሚሉትንም ሳያውቁ መደሳሰት መፈንጠዝ አይነት ሲሆን:- “ጥልቅ” ምስጋና ግን ከጥልቅ ልባችን የሚፈልቅ፣ በቂ ምክንያት ያለው፣ የጌታ ምህረት ብዛቱ በባለውለተኝነት ስሜት እያናወጠን፣ እንባ እንባ እያለን ወይም የሚፈነቅል ደስታ ሲያስጮኸን ነው፡፡ ደስታም እኮ ጥልቅ እና ግልብ ልዩነቱ ያስታውቃል፡፡ ማንም በማያየው የሀሳባችን ስፍራ እኔ ልንገስ እያለ ነው ጌታ፡!!
አንደበታችን ለሰው ነው፣ ተግባራችንም ለሰው የሚታይ ነው፣ ፍርድ ቤት ዳኛ በንግግርህ አልያም በስራህ እንጂ በሃሳብህ ሊፈርድብህ አይችልም፡፡ እንደዚህ እያሰብክ ነው ስለዚህ ጥፋተኛ ነህ ቢል ዳኛ እንዴት እንግዳ ነገር ይሆን? ለእግዚአብሔር ብቻ በተለየችው የሀሳባችን መሰዊያ አምልኮን ብንጀምር አትጠራጠሩ ሁሉ ይሰምራል፡፡ ልባችን ልክ አይደለም!! ከዚህም የተነሳ በእውነተኛ አምልኮ ልንባረክበት ከሚገባን በረከት በብዙ ጎድለናል፡፡ ፊል 4፡8 ቃሉ “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ እውነተኛ የሆነውን…ንጹህ የሆነውን፣ ፍቅር ያለበትን፣ መልካም ወሬ ያለበትን…ወዘተ አስቡ” ሲለን እኛ ሁሉን በተቃራኒው እያሰብን ቢሆንስ? ማር 12፡28 በፍጹም ልብህ፣ ሃሳብህ፣ ነፍስህ እና ሐይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ ሲል እኛ በፍጹም ሪትም፣ ፒች፣ ቅኝት፣ ጩኸት፣ ላይት፣ ጪስ፣ መድረክ፣ ልብስ ብቻ ልንወደው ሞክረን ይሆን? ልብም፣ ነፍስም፣ ሀሳብም፣ ሀይልም የውስጥ ናቸው በመሰረታዊ ደረጃ፡፡ ስለዚህ ጊታራችን ኪቦርዳችን ላይን አሬያችን ምርጥ እንደሆነ ሁሉ ሀሳባችን ምርጥ ይሁን!! ስለ ጌታ፣ ስለ ባልንጀራ፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ህዝብ ያለን ሀሳብ በጎ ይሁን፡፡ አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ!! መዝ 19፡14 የአፌ ቃል እና የልቤ ሀሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን፡፡ ሀሳብ ሲያምር አንደበት ያምራል፣ ተግባርም ያምራል፡፡