እግዚአብሔር ሁል ጊዜ የሚገኝና ከኛ ጋር ሕብረት ማድረግ የሚፈልግ አምላክ ነው፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እጅግ ወሳኝ መንገድ ነው (ያዕ. 4፡8)፤ ለፈቃዱ ይበልጥ ጥማት እንዲኖረን ያደርጋል (ማቴ. 6፡10)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ አስደናቂ የጸሎት ሕይወት ነበረው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሌሊቱን ሙሉ በጸሎት ሲያሳልፍ አይተውታል፡፡ ኢየሱስ የተካነ “የጸሎት ወታደር” ነበር፡፡ እንዴት መጸለይ እንዳለብንም አስተምሮናል፡፡ ስለዚህ እስኪ ከባለሙያው እንማር፡፡
የኢየሱስ የጸሎት ሞዴል
ኢየሱስ የጸሎት መመርያ የሚሆነንን “የጌታ ጸሎት” ብለን የምንጠራውን ጸሎት አስተምሮናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህንን ጸሎት ስንጸልይ በጋራ ለማምለክ ብቻ አይደለም፡፡ ለግል የጸሎት ሕይወታችን እንደ ንድፍ ልንጠቀመው እንችላለን፡፡
ማቴዎስ 6፡9-13 ላይ የሚገኘውን የጌታን ጸሎት ስንመለከት ተቀዳሚው ተግባራችን እግዚአብሔርን ማመስገንና ማምለክ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ወደ ሰማዩ አባታችን እንጸልያለን፤ እናመልከዋለን፡፡
ፈቃዱን በምድር ላይ እንዲፈፅም እንጸልያለን፡፡
አባታችን በየዕለቱ የሚያስፈልገንን እንጀራ እንዲሰጠንና እንዲመግበንም እንጸልያለን፡፡ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን እንጸልያለን፤ የበደሉንንም ይቅር እንድንል እንደሚጠብቅብንም እናስተውላለን፡፡ ከፈተና እንዲያድነንና ከክፉ እንዲጠብቀን እንጠይቀዋለን፡፡
እግዚአብሔር በቃሉና በጸሎት ከኛ ጋር ሕብረት ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ቃሉን እንድንረዳና በጸሎት ከእርሱ ጋር እንድንገናኝ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል፡፡