ደቀ መዝሙር

በቃሉ ማደግ

የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለአማኞች ከሚናገርባቸው መንገዶች መካከል ዋነኛውና መሠረታዊው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከእግዚአብሔር ለመስማት በሌሎች መንገዶች ላይ ይደገፋሉ፡፡ አንዳንዶች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመለየት የውስጥ ሰላማቸውን ያዳምጣሉ ወይም ሁኔታዎችን ብቻ ይመለከታሉ፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ዋነኛ የመናገርያ መንገዱ ቃሉ ነው፡፡ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡” (1ጢሞ. 3፡16-17) የእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚነግሩንን ሌሎች መንገዶች የምንመረምርበት ቋሚ መለኪያ ነው፡፡

ለክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ፣ አሠራሩንና የመንግሥቱን መርሆች በማሳወቅ ሕይወታችንንና ውሳኔዎቻችንን ይመራል፡፡ እርሱ ማን እንደሆነ፣ ፈቃዱ ምን እንደሆነና ከእርሱ ጋር እንዴት መገናኘት እንደምንችል የሚያሳውቀንን እጅግ የበለጸገ ዕውቀት ሰጥቶናል (መዝ. 19፡7-11)፡፡ ይህንን በረከት የምንካፈልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ፡-

  1. መስማት፡- የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብና ሲብራራ እንሰማለን፡፡
  2. ማንበብ፡- አማኝ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ ሲወስድ ከእግዚአብሔር የሚሰማበትን ተጨማሪ ዕድል ያገኛል፡፡
  3. ማጥናት፡- የእግዚአብሔርን ቃል ጠለቅ ባለ ሁኔታ ማጥናት ጊዜና ትዕግስትን ይጠይቃል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛዎችን ወይንም ሌሎች የድጋፍ መሣርያዎችን መጠቀም ጥናታችንን ከፍ ያደርጋል፡፡
  4. ማሰላሰል፡- የንባብ ፍጥነታችንን በመቀነስ ቃሉን ማሰላሰልም በጣም ወሳኝ ነው፡፡
  5. መሸምደድ፡- የእግዚአብሔርን ቃል “በልባችን ውስጥ እንድንሰውር” ተነግሮናል፦ “አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” (መዝሙር 119:11)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” ሲል ይህንኑ ከማሳሰብ አንጻር ነው (ቆላስይስ 3:16)። የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎች በትውስታ መያዝ ለክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል ያሳውቀዋል፡፡ ቃሉን ከሌሎች ጋር እንዲካፈል፣ ከክፉው ፈተና፣ ከሰይጣን ውሸትና ጥቃት ራሱን እንዲከላከል ያግዘዋል፡፡
  6. ቃለ እግዚአብሔርን መተርጎም፡- የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ መንፈሱ እውነትን ማወቅ እንድንችል ልባችንን ይከፍታል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ቃሉን የመተርጎም አቅማችን ማደግ ይኖርበታል፡፡ የተለያዩ ክርስቲያኖች አንዱን ቃል በተለያዩ መንገዶች ከመተርጎማቸው የተነሳ ቃሉን የመተርጎም አስፈላጊነትን የሚያጣጥሉ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ ቃሉን በትክክል መተርጎም በግል ስሜት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስሜታቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመተርጎም ሥልጣን ያለው ይመስል ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የግል ስሜታቸውን ተንተርሰው ሲናገሩ እንሰማቸዋለን፡፡ እንደርሱ ግን አይደለም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ባለሥልጣን በመሆኑ እኛ እራሳችንን በእርሱ ላይ ባለሥልጣናት አድርገን መሾም አይገባንም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሁሉም ንባብ አንድ ትርጉም ብቻ ነው ያለው፡፡ እርሱም የመጀመርያው ጸሐፊ እንዲያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ነው፡፡ አንዳንድ ጠቃሚ ምንጮች የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ባሕረ ዕውቀት (ኢንሳይክሎፒድያ) እና ገላጭ የሆኑ ሐታቾች (ኮሜንተሪዎች) ናቸው፡፡ እነዚህ በክርስቲያናዊ መጻሕፍት መደብር ወይንም በኢንተርኔት ላይ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ለቃሉ ተገቢውን ክብር በመስጠት እንድናነበውና እንድንማረው ዘንድ እግዚአብሔር ማስተዋልን ይስጠን። አሜን።

(“ደቀ መዛሙርትን ማነጽ” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ ጽሑፍ ከተወሰነ ማሻሻያ ጋር የተወሰደ)

About the author

Dan

ወንድም ዳንኤል በነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሲሆን የበርካታ መጻሕፍት ተርጓሚ፣ አርታዒና ደራሲ ነው።