ደቀ መዝሙር

ደቀ መዝሙር

  • “ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” ሉቃ 14፡27

    ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የተናገረው ቃል ነው። ይህ ቃል ዛሬም ሊከተሉት ለሚወዱት ሁሉ ተገቢውን ጥያቄ ያነሳል፡ ራስን በመካድ ለእርሱና ለሱ ብቻ ለመኖር ውሳኔን አድርገን እንከተለው ዘንድ ይህ ጥሪ ለእያንዳንዳችን ደርሶናል ምላሻችን ግን ምንድን ነው? በተለይ ባለንበት ዘመን በየቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ በየኮንፈረንሱ የምንሰማቸው ስብከቶች (ትምህርቶች) ምን ላይ ያተኮሩ ናቸው ብላችሁ አስባችሁ ታውቁ ይሆን? ከርዕሶቻቸው እንኳ ብንነሳ “የጥርመሳ ዘመን” “የቅባት ዘመን” “የከፍታ ዘመን” ወዘተ… እያለ ይቀጥላል። ይሄ ማለት ግን ጥቂቶች የሚሆኑ የክርስትና አንኳር ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ የሉም ማለት አይደለም። ነገር ግን አብዛኛው ያደላው የኛ የአማኞች ሕይወት ለምድር የተፈጠረ ብቻ ያህል አድርገን እንድናስብ የሚያደርጉን መብዛታቸው እጅግ ያሳዝናል። ክርስትና ዋጋ ያስከፍላል !! የሚለው የኢየሱስ አስተምህሮ ከብዙዎች አንደበት የራቀ ይመስላል ወጣት የሆነውን ትውልዳችንን እንዲለማመድ እየተደረገ ያለው ነገር ከቀደሙ አባቶች ሕይወት ጋር ሲነጻጸር እጅጉን የራቀ ነው። ይሄ ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል ልል ነው ብቅ ያልኩት። እንደው የአቅም ለማበርከት መቼም ያለንበት ዘመን የሶሻል ሚዲያ መነጋገሪያ የሆነበት ዘመን ላይ ነው፡ ይሄንኑ ቴክኒዮሎጂ በመጠቀም ድምጼን ላሰማ ብዬ ነው። ጠንካራ ደቀ መዝሙርነት ያስፈልገናል አንድ ሰው እንዳለው ነው “ቤተ ክርስቲያንን ደቀ መዛሙርት ያልሆኑ ደቀ መዝሙሮች ሞልተዋታል” አለ።  

    እንግዲህ ደቀ መዝሙርነት ዋናው እና ወሳኙ የክርስቲያን መለያው ነው። መስቀሉ ማንነታችን ነው። የሞቅታና የይሆንልሃል አስተምሕሮዎች የትም እያደረሱን አይደለም ያሉት። እውቁ ጀርመናዊው መጋቢ እና የነገረ መለኮት መምህር ዲትሪክ ቦንሆፈር “ብዙ ሰዎች በትክክለኛ ፍላጎት የምንናገረውን ለመስማት ወደ ማምለኪያ ስፍራችን ይመጣሉ ነገር ግን በብዛት ጥሩ ያልሆነ ስሜት እየተሰማቸው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ምክንያቱም ወደ ኢየሱስ እንዳይመጡ በጣም ውስብስብ (አስቸጋሪ) ስለምናደርግባቸው ነው።” ብሎ ተናገረ የጌታ ኢየሱስ መልዕክት በጣም ግልጽ ነበር ሰዎች እንዲወስኑ ጥያቄ የሚፈጥር ሊከተሉት አለዛ ላይከተሉት ደቀ መዝሙራዊ ጥሪ ያቀርብላቸው ነበር። “ኢየሱስም፦ ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።” ማቴ 8:20 ይሄ እንግዲህ የኢየሱስ ጥሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው በዚህ በማቴዎ 8 ላይ ባለው ታሪክ የምናየው ለዚህ የአይሁድ መምህር “ወደ ምትሄድበት እሄዳለሁ” ብሎ ማለቱ በጣም ቀላል ነበረ ነገር ግን ወደ ዋናው ውሳኔ እንዲመጣ ሲጋበዝ ያን ጊዜ ነው እውነተኛ ውሳኔ መወሰኑም አለመወሰኑም የሚታየው ኢየሱስ አይደለም ልከተልህ የሚሉትን ይቅርና አብረውት ያሉትን “ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ። እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ።” ዮሐ 6፡67  እንደው ዛሬ ጌታ እኛን ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርብልንስ? ለምን እንደተከተልነው ገብቶን ይሆን? እንደ ፈሪሳዊው አብሬህ እሄዳለሁ ማለቱ ላይከብድ ይችላል መወሰኑ ግን በጣም ወሳኝ ነው አብሬው ነኝ፡ ብለን ልናስብ ይሆን ይሆናል ነገር ግን እንደ ደቀ መዛሙርቱ  ሌሎች አማራጭ የሚመስሉ ነገሮች ጋር ስንደርስስ? እንደ ጴጥሮስ “ከአንተ ወዴት እንሄዳልን?”  ለማለት የሚያስችል የሕይወት ውሳኔን አድርገን ይሆን? ራሳችንን ክደን  መስቀሉን ተሸክመን መከተል አማራጭ የሌለው ጥሪ ነው። በይሆንልኛል የሂሳብ ስሌት ሰርተን ሳይሆን “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።” ማቴ 10፡25 የሚለውን ሂሳብ ሰርተን መከተል ነው። እንግዲህ ጎበዝ ወገባችንን ጠብቅ ትንፋሻችንን ሰብሰብ አድርገን የጀመርነውን ጉዞ በሚገባ ለመቀጠል እንበርታ ተስፋችን እኛ ከምናስበው ይበልጣል ጥሪያችን ክቡር ነው፡ መድረሻችን ከፍያለ ነው፡ ሰለዚህ እንበርታ።  ደቀ መዛሙርት በመሆን ሌሎችንም ደቀ መዛሙርት እናድርግ፤

    About the author

    Tebebe Mekonnen

    ወንድም ጥበበ ባለትዳር እና የልጆች አባት ነው፤ ጌታን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ እየተከተለ ያለ፣ ባለበት ሕብረት ጌታን የሚያመልክ እና የሚያገለግል የጌታ ደቀ መዝሙር የሆነ ወንድም ነው፤