ደቀ መዝሙር

ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ማድረግ

በክርስቶስ በማመን ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ሕይወት የተሻገረ ሰው ብዙ በረከቶችንና መብቶችን ያገኛል፤ ከነዚህ መካከል አንዱ ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ በሙሉ መታረቅና አዲስ ሕብረት መጀመር ነው፡፡ ይህ ሕብረት አእምሯችን ሊያስበው ከሚችለው ከየትኛውም ነገር የጠለቀ፣ የተሟላና የሰፋ ሕብረት ነው፡፡ በኛና በእግዚአብሔር መካከል ባለው ሕብረት ላይ ትልቅ ተፅዕኖን የሚያሳድረው በኛና በእግዚአብሔር መካከል የሰፋ ልዩነት መኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፦

    • እኛ ውሱኖች ስንሆን እግዚአብሔር ግን ያልተወሰነ ነው፡፡
    • ስለምንኖርበት ዓለምና በእርከናችን ስላሉት ሰዎች ያለን መረዳት በጣም ውሱን ሲሆን እርሱ ግን ሁሉን አዋቂ ነው፡፡
    • እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው፤ እኛ ፍጡራን ነን፡፡
    • እርሱ የማይታይ ነው፤ እኛ ግን እንታያለን፡፡
    • እርሱ የማይለዋወጥ ነው፤ እኛ ግን እንለዋወጣለን፡፡
    • እግዚአብሔር ፍፁም ነው፤ እኛ ግን ፍፁማን አለመሆናችን ግልፅ ነው፡፡

ሆኖም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት በሕይወታችን ውስጥ ከምናውቃቸው ሕብረቶች ጋር የሚመሳሰልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ይህም እንደማንኛውም ሕብረት ጊዜን፣ መነጋገርን፣ መፈላለግን፣ መቀራረብን፣ ወዘተ. የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ ከሕብረቶች መካከል ምርጡ ረጅም ጊዜን በመውሰድ በጥልቀት ሐሳባችንን የምናካፍልበት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረትም ተመሳሳይ መንገድ ይከተላል፡፡ እንደ ማንኛውም ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት ሁለትዮሽያዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕብረትን ለመመሥረት የሚያደርጋቸው የተወሰኑ ነገሮች አሉ፤ ሕብረቱ እንዲጠብቅና እንዲያድግ ደግሞ ከኛም የሚጠበቁ ነገሮች አሉ፡፡ ይህንን የሁለትዮሽ መንገድና በሕብረት ላይ ያለውን ተፅዕኖ መረዳት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት መንከባከብ የምንችለው ይህንን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዴት መንከባከብ እንደምንችል በመረዳት ነው፡፡

እግዚአብሔር ከኛ ጋር ላለው ሕብረት የመጀመርያውን እርምጃ ይወስዳል

በጥልቀት ያውቀናል (መዝ. 139፡1-4)፡-

እግዚአብሔር ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ያውቃል፤ ተግባራታችንን፣ እንቅስቃሴዎቻችንን፣ ሐሳባችንን፣ ቃላችንን ያውቃል፡፡ እርሱ ሁሉን አዋቂ ስለሆነና ከጊዜና ከቦታ ውጪ ስለሚኖር እነዚህ ነገሮች ከመሆናቸው በፊት አስቀድሞ ያውቃቸዋል፡፡ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል፡፡

ዕውቀት በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ አስፈሪ ነገር ነው፡፡ ለሌሎች የምንነግረው ችግር እንደማያስከትል ያመንንበትን ብቻ ነው፡፡ ሌሎች እንዳያውቁ የምንፈልጋቸውን መረጃዎች ደግሞ እንሰውራለን፡፡ እግዚአብሔር ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቅ ምንም ነገር ልንደብቀው አንችልም፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ስለ እኛ የማይወደዱ ብዙ ነገሮችን ቢያውቅም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይወደናል!!!

ይጠብቀናል ይጋርደናል፡፡ እርሱ ጠባቂያችን ነው (መዝ. 139፡5-6)፡-

መዝሙረኛው “አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ፤ አንተ ፈጠርኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ፡፡” ይላል፡፡ እግዚአብሔር እጁን በኛ ላይ ማድረጉ ሁለንተናችንን የመጠበቁ ተምሳሌታዊ ንግግር ነው፡፡ በሌላ መዝሙር ላይ ዳዊት እግዚአብሔር ለእርሱ መጠንቀቁን በተለያዩ ምሳሌዎች ይገልፃል፡፡ ጋሻ፣ ምሽግ፣ መሸሸጊያ ቦታ እና መጠጊያ እያለ ይገልፃል፡፡

መዝሙር 91፡1-2 ላይ እንዲህ ይላል፡- “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል፡፡ እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፡፡”

ያለንበት ሁኔታ ምንም ቢሆን ሁል ጊዜ ትኩረቱ በኛ ላይ ነው (መዝ. 139፡7-12)፡-

መዝሙረኛው “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?” በማለት በመደነቅ ይናገራል፡፡ በማስከተልም የትም ቢሄድ ከእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ ሊወጣ እንደማይችል ይናገራል፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነትና ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት መካከል የሚገኝ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ አንድ ሰው ምንም ያህል ቢመኝ ሁል ጊዜ የሥጋችንንና የስሜታችንን ፍላጎቶች ለመሙላት ሊገኝልን አይችልም፡፡ በሆነ ጊዜ ላይ ርቀትና ሌሎች ጉዳዮች ሊያግዱት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከኛ ጋር ወደማይሆንበት ቦታ መሄድ አንችልም፡፡ እርሱ የሌለበት ቦታ የለምና፡፡

የሕልውናችን መሠረትና አስቀጣይ እርሱ ነው፡ ውጪያዊ (ሥጋችን) እና ዘላለማዊ (ስሜታዊ፣ መንፈሳዊ) (መዝ. 139፡13-16)፦

ስለሚቀርቡን ሰዎች በጣም ዋጋ ከምንሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዱ አንዳችን ሌላችንን መረዳት መቻላችንን ነው፡፡ እነዚያ ምርጥ ወዳጆቻችን ምን እንደምንወድና እንደምንጠላ ያውቃሉ፡፡ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ስለሆነ ከማንም በላይ ውስጣችንን ያውቀዋል፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ሕብረት ውስጥ ኃላፊነት አለብን፦

  1. እርሱን ለመፈለግ (ኤር. 29፡10-14)

“እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ”  (ኤር 29፡10-14)፡፡ ልብ የአንድን ሰው የማንነቱን ማዕከል፣ ማለትም ስሜቱንና ፈቃዱን ያመለክታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከልብ ጋር የተያያዙ ብዙ ትዕዛዛት አሉት፤ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን እንድንወደው (ዘዳ. 6፡5)፣ በፍጹም ልባችን እንድንታመነው (ምሳ. 3፡5)፣ በፍጹም ልባችን ንስሐ እንድንገባ ተነግሮናል (ኢዩ. 2፡12)፡፡ በግማሽ ልባችን ልንፈልገው አይገባንም፡፡

ወደ ተለያዩ ቦታዎች ለጉዞ የወጡ ሁለት ሰዎችን እስኪ አስቡ፡፡ የመጀመርያው ሰው በሳምንቱ አጋማሽ የጥፍር መቁረጫውን መጣሉን አስተዋለ፡፡ ብዙም ውድ ባይሆንም ጥሩ የጥፍር መቁረጫ ነው፡፡ ምናልባት ድንገት እንደ አጋጣሚ አገኘው ይሆናል በሚል ሲሄድ አልፎ አልፎ በዓይኖቹ ያማትራል፡፡

ሁለተኛው ሰው ከቤት በወጣበት ምሽት የመኪናው ቁልፉ ጠፋበት፡፡ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ባለቤቱ ልጃቸው የመኪና አደጋ ደርሶበት ሆስፒታል መግባቱን ደውላ ትነግረዋለች፡፡ በእጁና በጉልበቱ እየዳኸ ቁልፉን ፈለገው፡፡ የሸከፈውን እቃ ሁሉ በታትኖ ፈለገ፡፡ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ቁልፉን ፈለገው፡፡ የመጀመርያው ሰው ሴንጢውን ይፈልግ የነበረው በግማሽ ልቡ ነበር፡፡ ሁለተኛው ሰው ቁልፉን ይፈልግ የነበረው በፍጹም ልቡ ነበር፡፡

  1. በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ሐሳባችን ልንወደው ይገባል (ማቴ 22፡36-39)

“መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡” (ማቴ 22፡37)

እግዚአብሔር መኖሩን ወይም ፈጣሪ መሆኑን ዕውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችንና ሐሳባችን ልንወደው ይገባል፡፡ በሌላ አባባል በሁለንተናችን ልንወደው ይገባል፡፡

  1. እርሱን መታዘዝ (ዮሐ 14፡21)

የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የመታዘዝ ኃላፊነትም አለብን፡፡ ይህ ፍቅር በተግባር የሚገለጥበት መንገድ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እንደተናገረው መታዘዝ ለእግአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት መንገድ ነው (ዮሐ. 14፡21)፡፡ ይህንን ቃል የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ኋላ ላይ የኢየሱስን ንግግር በመድገም ጽፏል፡- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” (1ዮሐ. 5፡3)። እግዚአብሔርን አውቀናል (ከእርሱ ጋር ሕብረትን መሥርተናል) የምንል ከሆነና ትዕዛዛቱን ባንጠብቅ ውሸተኞች መሆናችንን ዮሐንስ ተናግሯል (1ዮሐ. 2፡4)፡፡

  1. ወደ እርሱ መቅረብ (ኤር. 4፡8)

የጌታ ኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ጻፈ፡- “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል፡፡ እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ” (ያዕ 4፡8)። ይህ ጥቅስ ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ሕብረት ያለብንን ሌላ ኃላፊነት የሚገልፅ ነው፡፡ ስለ ውጫዊ ተግባራችን (እጆቻችሁን አንጹ) እና ስለ ውስጣዊው ሐሳባችንም ጭምር (ልባችሁን አጥሩ) ይናገራል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ ሁለቱም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡

እኛ ኃጢአተኛ ፍጥረታት በመሆናችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ሕብረት ከእርሱ የሚያርቁንን ተግባራት እንፈፅማለን፡፡ ስለዚህ መራቃችንን ባወቅን ቁጥር ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ያስፈልገናል፤ ኃጢአታችንንም በመናዘዝ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልገናል፡፡ እኛ እርሱን በመፈለግ ወደ እርሱ እንቀርባለን፤ እርሱ ደግሞ በሙላት ወደ እኛ ይቀርባል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ኃላፊነቶች ከተስፋ ጋር እንደተያያዙ ልብ በሉ፡፡ ኃላፊነታችንን ስንወጣ አዎንታዊ ምላሽን እናገኛለን፡፡ ይህ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የሁለትዮሽ መንገድ ግንኙነት የሚገልጥ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ስንፈልግ ይገኝልናል፤ ለኛ ያለውን ግሩም የሆነውን ዕቅዱንም ይገልጥልናል፡፡ እግዚአብሔርን በመታዘዝ ፍቅራችንን ስንገልጥ ፍቅሩን ይገልጥልናል፤ ራሱንም ይገልጥልናል፡፡ ወደ እርሱ ስንቀርብ እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት ከእርሱ ጋር በመጣበቅ ይለመልማል 

እያንዳንዱ ግንኙነት የሚያድገው ልምዶችን በመለዋወጥና እርስ በርስ በሚገባ በመተዋወቅ ነው፡፡ ክርስትና በባሕርዩ በሕያው እግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል የሚደረግ ግንኙነት ነው፡፡ ራሱን ለኛ በመግለጥና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እኛን ከራሱ ጋር በማስታረቅ እግዚአብሔር እኛን በመፈለግ ይህንን ሕብረት ጀምሯል፡፡ በምላሹም እግዚአብሔርን በንቃት መፈለግና ከእርሱ ጋር ያለንን ሕብረት ልንንከባከብ ይገባናል፡፡ ይህንንም ከእርሱ ጋር ጊዜን በማሳለፍ ነው መፈፀም የምንችለው፡ ነገር ግን ሰዎች ብዙ ጊዜ “እግዚአብሔርን ሳታየው እንዴት ነው አብረኸው ጊዜን ልታሳለፍ የምትችለው?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ እንደ መታደል ሆኖ እግዚአብሔር መንገዱን አሳይቶናል፡፡ የእርሱ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል፡፡ በጸሎት ሥፍራችን ደግሞ ያገኘናል፡፡ ቃሉን ሳናቋርጥ ስናነብና ስንጸልይ ወደ እርሱ ይበልጥ እንቀርባለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር እንዴት ሕብረት ያደርግ እንደነበር ስንመለከት የእርሱን ባሕርይ፣ እሴቶች እና ማንነቱን እናውቃለን፡፡ ከቃሉ ጋርና በጸሎት ጊዜን ባሳለፍን ቁጥር እግዚአብሔር እኛን በመቀበል ሕይወታችንን ይለውጣል፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር በቃሉ አማካይነት እንገናኛለን

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና በተግባር መኖር ግሩም ልምምድ ነው፡፡ ከሌሎቹ መጻሕፍት በተለየ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና መንፈሳዊ ነው፣ በተግባር የሚቀየርና ጥልቅ ነው፡፡ የዕብራውያን መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ እንደሆነ ይናገራል (ዕብ. 4፡12)፡፡ በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር ሁለንተናችንን፣ ማለትም ነፍሳችንን፣ መንፈሳችንን፣ አካላችንን፣ አእምሯችንንና ልባችንን ይነካል፡፡ ቃሉን ባነበብንና በታዘዝን ቁጥር በሕይወታችን ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ይሆናል፡፡ መዝሙር 19፡7-14 የእግዚአብሔር ቃል ነፍሳችንን እንደሚያድስ፣ ጠቢባን እንደሚያደርገን፣ እንደሚያበረታንና እንደሚመራን ይናገራል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከመልካም ምክር ያለፈና እግዚአብሔር ከኛ ጋር በቀጥታ የሚነጋገርበት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜን ማሳለፍ ከንጉሥ ጋር እንደ መነጋገር ነው፡፡ ይህም ማለት ቃሉን መቅረብ ያለብን ልክ እግዚአብሔርን እንደምንቀርበው ነው፤ በትህትናና በመታዘዝ፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡- “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ፡፡” (ዮሐ. 14፡21)

ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜን ማሳለፍ ከምሑራዊ ልምምድ ወይም ራስን ከማሻሻል ያለፈ ነው፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ያለንን አክብሮትና ፍቅር የምንገልጥበት መንገድ ነው፡፡ ለመማር ምቹ በሆነ አቀራረብና ለመለወጥ በመፈለግ በቃሉ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንጠጋለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ባሕርዩን በሙላት ያንፀባርቃል እንዲሁም ዳርቻ የሌለውን ሉኣላዊ ኃይሉን የተሞላ ነው፡፡ በመዝሙር 37 ላይ ዳዊት እግዚአብሔር የገባውን ቃል እንደሚፈፅም ይነግረናል፡፡ ደግሞም ይመክረናል፡- “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” (ቁ. 4)። ስለዚህ እግዚአብሔር እውነቱን እንዲገልጥልንና ፈቃዱን በመካከላችን እንዲፈፅም በሚጠማ ልብ ልንጠባበቀው ይገባል፡፡

በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር እንነጋገራለን

እንደ ምድራዊው ጓደኝነታችን ሁሉ ከሰማዩ አባታችን ከእግዚአብሔር ጋርም ያለን ሕብረት መቋረጥ የለበትም፡፡ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር የማያልቅ ንግግር የምናደርግበት ሊሆንልን ይችላል፡፡ ጸሎት ቃሉን በማንበብ ባሳለፍነው ጊዜ ላይ ተጨምሮ ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገውን ንግግር እንድንቀጥል ያስችለናል፡፡ ነገር ግን ጸሎት ምንድነው? ጸሎት ሐዋርያው ዮሐንስ እንደጻፈው እግዚአብሔር እኛን ለመድረስ ለወሰደው እርምጃ የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡ ጌታችን እንዲህ አለ፡- “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፡፡” (ራዕይ 3፡20)

ጸሎት የእግዚአብሔርን እርዳታ የምንጠይቅበትና የእርሱን አብሮነት የምንቀበልበት ነው፡፡ እንኳን በደህና መጣህ የማለት ወይንም ለእርዳታ የመጣራት ያህል ነው፡፡በጸሎት ለእግዚአብሔር ትኩረትን የምንሰጥበት ሕይወት በቀላሉ የሚመጣ አይደለም፡፡ የጸሎት ልምምድ ውስጥ መግባት ትግል አለው ነገር ግን ደስታን ያጎናፅፈናል፡፡እግዚአብሔር በጸጋው ጸሎትን ያለማምደናል፤ በቃሉም ውስጥ ብዙ ምሳሌዎችን ሰጥቶናል፡፡ ኤልያስ፣ ዳንኤል፣ አስቴር፣ ነህምያ፣ ራሱ ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ይጠቀሳሉ፡፡

መጽሐፍ ቅደስ ስለ ጸሎት አጥብቆ ይናገራል፡፡ አንድ ክርስቲያን መፀለይ ካልቻለ ጤናማ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረው አይችል፡፡

  • “እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።” 1ዜና 16፡11
  • “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።” መዝ 145፡18
  • “እግዚአብሔር ከኅጥኣን ይርቃል የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።” ምሳ 15፡29
  • “ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።” ፊልጲስዩስ 4፡6
  • “ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ።” ቆላ 4፡2
  • “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” 1ተሰ 5፡17
  • “እንዲህም አላቸው፦ ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ። ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? ያም ከውስጥ መልሶ፦ አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” ሉቃ 5፡11-13
  • “በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ።” ሉቃ 6፡12
  • “ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ እንዲህ ሲል፦ በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች። ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ። ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ። ጌታም አለ። ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” ሉቃ 18፡1-8
    • ጸሎት ነገሮችን ይለውጣል፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ እኛን ይለውጠናል፡፡
    • ጸሎት የእግዚአብሔርን ልብ ለልባችን ይገልጣል፡፡
    • ጸሎት የእግዚአብሔር ክብር በሕይወታችን እንዲገለጥ ያደርጋል፡፡
    • ጸሎት ከማይታዩ የክፋት ሰራዊቶች ጋር የሚደረግ ተጋድሎ ሲሆን ድል የማግኛ መንገድ ነው፡፡
    • ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የመገኘቱ ሕልውና ያመጣናል፡፡
    • የሚጸልይ ሰው የእግዚአብሔርን ድምፅ ይለማመዳል፤ የእግዚአብሔርን አጠቃላይ ፈቃድ ከማወቅ አልፎ ለአስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የመመራት ልምምድ ውስጥ ይገባል፡፡
    • የሚጸልይ ሰው በእግዚአብሔር በረከት ውስጥ ይኖራል፤ ከፈተና የመውጫ መንገዶችንም ያገኛል፡፡
    • የሚጸልይ ሰው ለምድር ለውጥን ያመጣል፤ የእግዚአብሔርም ሞገስ ይሆንለታል፡፡

ማጠቃለያ

የግል የፅሞና ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ለመመሥረት በጣም ወሳኝ ነው፡፡

    • ትክክለኛ ጊዜ መምረጥ (ማለዳና አመሻሽ አካባቢ)
    • የሚያስፈልጉንን መሣርያዎች መያዝ (መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማስታወሻ፣ የምናዳምጠው ለስላሳ መዝሙር)
    • ገለልተኛና ፀጥተኛ ቦታ ማግኘት፡፡
    • ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተወሰነ ክፍል ማንበብ፡፡
    • በምስጋና መጀመር፣ በንስሐ ራስን ማየት፡፡
    • በፀጥታ የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰል፤ ጌታን ማድመጥ፡፡
    • ይህንን የየዕለት ልማድ ማድረግ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንንም ይርዳን!

About the author

Dan

ወንድም ዳንኤል በነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሲሆን የበርካታ መጻሕፍት ተርጓሚ፣ አርታዒና ደራሲ ነው።