የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ አሳየኸኝ ለገሰ ነው፤ ጽሁፉ የተገኘው ከፌስቡክ ገጹ ነው፤
አንዳንድ የዘመናችን “ቤተ ክርስቲያናት” በአምልኮ ሰዓት (በልዩ ልዩ ክዋኔዎች) ለታዳሚው “አስደሳች ድባብ” ለመፍጠር የሚኼዱበት ርቀት አስደንጋጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ የመድረክ አገልግሎቶች የገበያ ፍልስፍና (marketing philosophy) የሚከተሉ ይመስላሉ፡፡ የደንበኞችን ፍላጎት በማጥናት ተፈላጊውን ምርት እንደሚያቀርብ አምራች፣ ጆሮን የሚያሳክክ ትምህርትና ስሜትን የሚኮረኩር ሸቀጥ ሁሉ መድረኩ ላይ መሰጣት ከጀመረ ቆየ፡፡
ስብከቱ በአዎንታዊ ሐሳቦች የተሞላ፣ ለአድማጩ ጊዜያዊ ስሜት የሚጨነቅ፣ ቀላልና ዘና የሚያደርግ ሲሆን፤ የሚያስተምር፣ የሚወቅስ፣ የሚገስጽና የሚያቀና ጠንካራ ትምህርት ከብዙ ምስባኮች ተሰድዷል፡፡ ስለ ኀጢአት፣ ስለ ፍርድ፣ ስለ ሕይወት ንጽሕና፣ ስለ ንስሐ፣ ስለ ወንድማማች መዋደድ፣ ስለ ጌታ ምጽአት አይነሳም፡፡ ትምህርቶች፣ ለአድማጭ እንዳይጎረብጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘታቸው ሳስቶ ሥነ ልቡናዊና አነቃቂ ይደረጋሉ፡፡
አምልኮ እየተባለ የሚከወነውም ድርጊት እንዲሁ ነው፡፡ መዝሙሮች ከመልዕክት አዘልነት ይልቅ ምዕመናንን ለማውረግረግ የሚጨነቁ፣ በተራ ቀረርቶና በባዶ ተስፋ ታዳሚን ማስፈንጠዝን ግባቸው ያደረጉ ሆነዋል፡፡ የጥሩ ‹‹አስመላኪ›› መለኪያው ‘ሕዝቡን ምን ያህል አንቀሳቀሰ? ድምጹና ደንሶ የማስደነስ ችሎታው ምን ይመስላል?’ የሚል የሆነ ይመስላል፡፡ መልዕክት አልባውን ጩኸት የሚያጅበው ሙዚቃ፣ የሚብረቀረቁ የመድረክ መብራቶችና ከጀርባ የሚለቀቀው ባዕድ ጭስ፣ ተመልካችን በስሜት የሚያጦዝ ድባብ ይፈጥራሉ፡፡ ከሁሉ የከፋው ነገር፣ ይህ ሰው ሰራሽ ድባብ “የእግዚአብሔር ሕልውና” እየተባለ መጠራቱ ነው፡፡ (ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ሐገረ አሜሪካ ተጉዞ የተመለሰ አገልጋይ፣ በዚያ ስላያቸው አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ሲናገር፣ “የመንፈስ ቅዱስ ደመና ጠፍቶባቸው፣ አርቴፊሻል ደመና ፈጥረው ከመድረክ ያቦንናሉ” ብሎ የተናገረው ትዝ ይለኛል፡፡)
በኮምፒዩተር ቴክኖሉጂ “user friendly” የሚባል የተለመደ ቃል አለ፡፡ ለተጠቃሚ የሚቀርቡ ሶፍተዌሮችና ፕሮግራሞች ለተጠቃሚው የማይከብዱና ያልተወሳሰቡ እንዲሆኑ አደርጎ ማቅረብ ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲሁ user friendly እየሆነ መጥቷል፡፡ አይደን ቆዘር የተባሉ መጋቢ (ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት) በአሜሪካ ቤተ ክርስቲያናት ላይ የተመለከቱትን ለውጥ አስመልክቶ፣ “ተዝናኖት (ወይም Entertainment) የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናትን እያጠቃ ያለ እጅግ የከፋ ኑፋቄ ነው! ተዝናኖት ራሱ እውነተኛውን አምልኮ የተካ ‘ሌላ አምልኮ’ ሆኗል” ብለው ነበር፡፡ የዘመናችንን ቤተ ክርስቲያን በትኩረት የታዘቡት ፌሚ አደለይ የተባሉ ጸሐፊም እንዲሁ፣ “ፈንጠዚያ ከመውደዳችን የተነሳ የእኛ ዘመን ቤተክርስቲያን ከ”ታላቁ ተልዕኮ ወደ ታላቁ ተዝናኖት” (from Great Commission to Great Entertainment) እየተሸጋገረች ይመስለኛል” ብለዋል፡፡
የገበያ ሕጉ፣ `ሰዎች ምን ያስፈልጋቸዋል` ከሚለው ይልቅ `ሰዎች ምን ይፈልጋሉ` የሚለው ላይ አተኩሩዋል፡፡ የታዳሚ ስሜት ላይ የቆመ “ተጠቃሚ ተኮር (consumer-oriented)” አገልግሎትም ተፈጥሯል፡፡ እግዚአብሔር ራሱም፣ “ዓላማችን የደንበኞች እርካታ ነው” የሚል ጥቅስ ለጥፎ፣ ‹‹ተደሰቱልኝ፣ ተዝናኑልኝ›› እያለ እንደሚያስተናግድ አስተናጋጅ የፍላጎታችን አገልጋይ ተደርጎ ተስሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ ብዙ ምስባኮች የወደቀውን ሰው የልዕልና መሻት እና ‹ኤጎ› እያከኩ አዳምን በሚቀልቡ ተናጋሪዎች ተሞልተዋል፡፡ ኮምጨጭ ያለው የቃል እውነት የሚነገርባቸው አዳራሾች ባዶ እየሆኑ፣ ጊዜው በጠየቀው የገበያ ስልት የሚመሩት ደግሞ ጠጠር መጣያ እያጡ ነው፡፡
አንዳንዶች ይህን አስነዋሪ ድርጊታቸውን፣ “ወጣቱንና አማኝ ያልሆነውን ማኅበረሰብ በአውዱ ለማግኘት የሚደረግ ነው” በማለት ለማመናፈስ ይጥራሉ፤ “በሁሉ እነርሱን መሰልኩ” የሚለውን የጳውሎስን ቃል ዋቢ አድርገውም ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ጳውሎስንም ሆነ ቃሉን ጠንቅቆ አለማወቅ ነው፡፡ ጳውሎስ ሰውን ለማስደሰት መልዕክቱን የሚያቀጥን የመድረክ አጫዋች አልነበረም፡፡ ዓለምን ለማዳን እንደ ዓለም መሆንን አልሰበከም፡፡ የዘመናችን ቤተ ክርስቲያን፣ ዓለም የራሷ የሆኑትን ለመሳብ የምትጠቀማቸውን ዘዴዎች ኮርጃ መጠቀሟ የክፍለ ዘመናችን ታላቅ መንፈሳዊ ቅሌት ይመስለኛል፡፡
ትውልዱ የሚያስፈልገው ይህ አልነበረም፤ ስጋዊ አፒታይቱን የሚያረካ ኀይማኖታዊ ተዝናኖት ወደ ክርስቶስ አያቀርበውም! በዳንኪራ የዳነ፣ የኮሜዲ ምሽት በመሰሉ ስብከቶች የተለወጠና በአነቃቂ ዲስኩሮች ያደገ ክርስቲያን አላየንም፡፡ የሚያስፈልገን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ቃሉ የሚመልሰን ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትና ክርስቶስንና ወንጌሉን የሚያልቅ አምልኮና አገልግሎት ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አጥሯ ፈርሶ የዓለም ኮተት ሁሉ ማራገፊያ እንዳትሆን መከላከል ይገባናል፡፡ ከተያያዝነው አደገኛ ቁልቁለት የሚመልሱንን እውነተኛ እረኞች እግዚአብሔር ይስጠን፡፡ መልካም ቀን!