ልምድ ያላቸው ተዋጊዎች በውጊያ ውስጥ የመጀመርያው መርህ ጠላትን ማወቅ ነው ይላሉ፡፡ ክርስቲያኖች ጠላቶች አሏቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ጠላቶች ዓለም፣ ሥጋና ሰይጣን እንደሆኑ ይናገራል፡፡ እነዚህ ጠላቶች ሳያቋርጡ አማኙን ስለሚገዳደሩት መንፈሳዊ ዕድገትን አስቸጋሪ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ጠላቶች የሚያመጡብንን ፈተናዎች ከተጋፈጥን እኛን በማጠንከርና እግዚአብሔርን የሚመስል ባሕርይን እንድናዳብር በመርዳት የዕድገት ምክንያት ሊሆኑን ይችላሉ (ያዕ. 1፡2-4)፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሦስቱ ጠላቶቻችን እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
ዓለም
አማኝ የሚጋፈጠው የመጀመርያው ጠላት ዓለም ነው፡፡ ዓለም ስንል በዙርያችን ያለውን ቁሳዊ ከባቢ ማለታችን አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለም” የሚለው ቃል ቁሳዊውን ከባቢ ብቻ ሳይሆን ክፉ ግዛትንም ጭምር ነው፡፡ እርሱም በሰይጣን የሚመራው ግዛት (ኤፌ. 2፡2) እንዲሁም ከእግዚአብሔር በተለየውና እግዚአብሔርን በሚጠላው ሕዝብ የተያዘው ሥርዓት ነው (ቆላ. 1፡21)፡፡ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥቱን በሙላት ለመመሥረት ወደ ምድር ሲመለስ ይህ ክፉ ግዛት ይጠፋል፡፡
አንድ ሰው ክርስቶስን እንደ አዳኙ ሲታመን ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማው መንግሥት ወደ ብርሃን ይሸጋገራል፡፡ አማኞች የዚህ ዓለም ግዛት አካል አይደሉም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ናቸው (ቆላ. 1፡13-14፣ 21-22)፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንግዶችና መጻተኞች መሆናችንን ያሳስበናል (1ጴጥ. 2፡11)፡፡
አማኞች የእግዚአብሔር መንግሥት አባላት ቢሆኑም በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ተፅዕኖ ያሳድርብናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ይህ ክፉ ዓለም በሥጋዊ እርካታ ምኞት፣ በዓይን አምሮትና ስለ ገንዘብ በመመካት የተያዘ ነው (1ዮሐ. 2፡15-17)፡፡ ወይንም ደግሞ ቻርለስ ዝዊንዶል የተሰኘ ደራሲ እንዳስቀመጠው “የዓለም ሥርዓት በአራት ቃላት ልንገልፃቸው በምችላቸው አራት ነገሮች የተያዘ ነው፤ እነርሱም ገንዘብ፣ ዝና፣ ሥልጣንና ደስታ ናቸው፡፡”
ሕይወታቸውን በእነዚህ አራቱ ነገሮች በሚመሩ አላማኞች ተከበናል፤ ነገር ግን እንደ ሰማይ ዜጎች ማዕበሉ ወደሚነጉድበት አቅጣጫ እንዳንወሰድ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡ በውጤቱም ከአቋማችን የተነሳ ልንሰደድና ጉዳት ሊደርስብን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሆነ ብለው ሊያሳድዱን ይችላሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሥርዓቱ ጋር ባለመስማማታችን ምክንያት ልንጎዳ እንችላለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ ተቃውሞ በማላገጥ ሊገለጥ ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ግልጽ የሆነ ጥቃት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከብቸኝነት ስሜት ጋር መታገል ያስፈልገናል፡፡ ጤናማ ባልሆኑ ግንኙነቶች፣ ጎጂ ጸባዮችና ሌሎች የኃጢአት ውጤቶች በሚታይበት ዓለም ውስጥ መኖሩ በራሱ ትልቅ የህመም ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡
1ዮሐንስ 2፡15-17 ላይ አማኞች ዓለምን ባለመውደድ ከእርሱ ራሳችንን እንድነጠብቅ ተነግሮናል፡፡ አንዳንድ አማኞች የምንኖርበትን ምድራዊ መንግሥት በተመለከተ አቋማችን ምን መሆን እንዳለበት ግራ ይገባቸዋል፡፡ ለእግዚአብሔር የተሻለው መንገድ ከዚህች ምድር መነጠል እንደሆነ ያስባሉ፡፡ አማኝ ካልሆኑት ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይገባ የሚያምኑ ሲሆን ከዓለም ጋር እንደሚያመቻምቹ የሚያስቧቸውን አማኞች ይነቅፋሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ኢየሱስም በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ተመሳሳይ ትችት ደርሶበት ነበር፡፡ እንደ እግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ዜጎች በማያምኑት ሕዝቦች መካከል ተፅዕኖን ልናሳርፍ ይገባናል፡፡ ዓለም ክፋትን እንድናደርግ ተፅዕኖ ሊያሳርፍብን አይገባም ነገር ግን የእግዚአብሔር አምባሳደሮች በመሆን በዚህ ዓለም ላይ ተፅዕኖን ልናመጣ ይገባናል፡፡
ሥጋ
ሁለተኛው የክርስቲያን ጠላት ሥጋ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ፍጥረት ለመበከልና በቆሻሻ ለመሙላት ብዙ እንደሠራን ሁሉ በውስጣችን የሚገኘውን የእግዚአብሔርን አዲስ ፍጥረት ለመበከልና ለማበላሸት የሚሞክር ኃጢአተኛ ባሕርይ በውስጣችን አለ፡፡ ጠላታችን በውስጣችን ይኖራል፡፡
ሁሉም የሰው ልጆች ከኃጢአት ባሕርይ ጋር ነው የሚወለዱት፡፡ ይህ የኃጢአት ባሕርይ ከተሳሳተ አስተሳሰብና ከመጥፎ ልማድ ያለፈ ነው፡፡ እግዚአብሔርንና ጽድቁን እንድንቃወም የሚያደርገን ውስጣዊ ጥመትና ፍላጎት ነው፡፡ ታዋቂ ክርስቲያን ጸሐፊ የሆነው ጄ. ኦስዋልድ ሳንደርስ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “ሥጋ በሰው ተፈጥሮ ውስጥ የሚገኝ ክፉ መሻት፣ ከአጥቂዎቻችን ጋር የሚተባበር ክፉ ከዳተኛ ነው፡፡ ሥጋ የዲያብሎስ ፈተና የሚቀመጥበትን ጎጆ ይሰጠዋል፡፡” የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ በራሳችን ምኞች ተስበን ኃጢአትን እንደምናደርግ በመናገር የሥጋችንን ተፅዕኖ ገልጿል (ያዕ. 1፡4)፡፡
የማያምን ሰው በዚህ የኃጢአት ባሕርይ ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ክርስቲያን ኃጢአተኛ ባሕርይ አለው ስለዚህ ይህ ባሕርይ በሞት ጊዜ ግብዓተ መሬቱ እስኪፈፀም ድረስ ሊታገለው ይገባል፡፡ ክርስቲያን ከዚህ ኃጢአተኛ ባሕርይ ጋር መታገል ቢኖርበትም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብሏል፡፡ በውስጡ በሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካይነት ኃጢአተኛ ባሕርይን በየትኛውም ጊዜ ልናሸንፍ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስና ኃጢአተኛ ባሕርይ ተቃራኒ ስለሆኑ አንዱን እያስተናገድን በሌላው መኖር አንችልም፡፡ “በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፡፡” (ገላ. 5፡16)
አማኞች ከዓለም ራሳቸውን የሚጠብቁባቸውን መንገዶች እንደተሰጡት ሁሉ ከኃጢአተኛ ባሕርይም የሚጠበቁባቸውን መንገዶች ተሰጥተዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አማኝ በየትኛውም ሰዓት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካይነት ኃጢአተኛ ባሕርዩን ማሸነፍ ይችላል (ገላ. 5፡16፣ ሮሜ 8፡13)፡፡ ኃጢአተኛ ባሕርይ አማኝ በሥጋው እስኪሞት ድረስ በውስጡ የሚኖር በመሆኑ ከኃጢአተኛ ባሕርይ ጋር የሚደረግ ፍልሚያ እስከ ዕድሜ ልካችን ድረስ ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ አማኝ (አዲስም ይሁን በሳል አማኝ) ንቁ መሆኑና በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ዲያብሎስ
ሦስተኛው ጠላታችን ዲያብሎስ ነው፡፡ ቀንድ ያለው መንሽ የያዘ የካርቱን ምስል ከመሆን በተለየ ሁኔታ ዲያብሎስ ትክክለኛ ጠላት ነው፣ አደገኛ ጠላት ነው፣ እኛን ለመጉዳትም ይፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስ ከመስመር የወጡ ክርስቲያኖችን ይዞ ለማጥፋት እንደሚያደባ ይናገራል፡፡ ዲያብሎስና በማይታየው ዓለም ውስጥ የሚገኙ በእርሱ ትዕዛዝ ስር ያሉ እርኩሳን መናፍስት ክርስቲያኖችን አምርረው ይጠላሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የእርሱ ጠላት ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ስለወገንን ነው፡፡ ዲያብሎስ በአንድ ወቅት ትልቅ ሥልጣን ያለው መልአክ የነበረ ቢሆንም በእግዚአብሔር ላይ አመፀ፡፡ አሁን የክፋት ሁሉ ቋት በመሆን እግዚአብሔርንና ሥራውን ሁሉ የሚቃወም ሆኗል፡፡
ፍፁም የሆነውን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ እግዚአብሔር ዲያብሎ ለተወሰነ ዘመን የተወሰነ ሥልጣን እንዲኖረው ፈቅዷል፡፡ ዲያብሎስና ተባባሪዎቹ አንድ ቀን አቅማቸውን ሁሉ በመገፈፍ ለዘላለም ወደሚሠቃዩበት የእሳት ባሕር ውስጥ ይጣላሉ፡፡ የታሪኩ የመጨረሻ ምዕራፍ አስቀድሞ ተጽፎ ስለተጠናቀቀ ክርስቲያኖች ማን ያሸንፋል ብለው መጨነቅ የለባቸውም፡፡
አሁን ግን አማኝ ይህንን ጠላት መጋፈጥ ይኖርበታል፡፡ ንቁ በመሆን ሰይጣን ጥቃት ሲፈፅም ማወቅ ይኖርበታል፡፡ አሁንም አማኝ አቅመ ቢስ ሳይሆን የዲያብሎስን ጥቃት የሚቋቋምበት ኃይል ተሰጥቶታል፡፡ ጴጥሮስ ጸንተን ዲያብሎስን ልንቃወመው እንደሚገባ ጽፏል (1ጴጥ. 5፡8-9)፡፡ ያዕቆብም ለመጀመርያዎቹ አማኞች “ዲያብሎስን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል” በማለት ጽፏል (ያዕ. 4፡7)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው መልዕክት ውስጥ ዲያብሎስን ለመቋቋም ስለተሰጡን መሣርያዎች በጥልቀት ይናገራል (ኤፌ. 6፡13-18)፡፡ የእውነት መታጠቂያ፣ የፅድቅ ጥሩር፣ የእምነት ጋሻ፣ የመንፈስ ሰይፍና የመሳሰሉት ትጥቆች የተሰጡን “የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም እንችል ዘንድ” እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዲያብሎስ የተወደደ አንዱ ስልት በክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ ሰይጣን የሐሰት አባት በመባል ነው የሚታወቀው (ዮሐ. 8፡44)፡፡ እውነትን በማጣመም ደግሞ የተካነ ነው፡፡ ይህ ከመጀመርያው ጀምሮ ሲጠቀምበት የነበረ አካሄድ ነው፡፡ ሔዋንን ያሳሳታት እውነትን በማጣመም የእግዚአብሔርን መልካምነት እንድትጠራጠር በማድረግ ነበር፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ የሆነ ዘዴን በአማኞች ላይ ይጠቀማል፡፡ የዲያብሎስን ሐሰት በመስማት መጥፎ የሆኑ ሁኔታዎች ሐሳባችንን እንዲወስዱት ከፈቀድን የእግዚአብሔርን መልካምነት ወይም ኃይል ልንጠራጠር እንችላለን፡፡ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በመሰወርና ራሳችንን በእውነት በማስታጠቅ እንዲሁም በመጸለይ የእግዚአብሔርን እውነት ከጠላት ውሸት ልንለይ ይገባናል፡፡
በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተሓድሶ ሰው በማርቲን ሉተር የተጻፈው አምላካችን ፅኑ ምሽጋችን የሚለው ዝማሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ የሚገኙትን አማኞች ማፅናናቱን ቀጥሏል፡፡ ከግጥሙ ላይ የጠወሰዱት የተወሰብኑ ስንኞች እንዲህ ይላሉ፡- “ያ ጥንታዊው ጠላታችን፣ ይፈልጋል ዛሬም ሊያጠፋን፣ ክፋቱና ኃይሉ ትልቅ፣ ጥላቻም የእርሱ ትጥቅ፣ በምድር የለም ከእርሱ የሚልቅ፡፡ ይህ ዓለም በዲያብሎስ ቢሞላም፣ ሊያስፈራራን ቢሞክርም፣ እግዚአብሔር እውነት ድል እንዲነሳ ስለወደደ እኛ አንፈራም፡፡ የጨለማው ንጉሥ ያጓራል፣ ልባችን መች እርሱን ይፈራል፣ ቁጣው አይችልም ሊያጠፋን፡፡ መጥፊያው እርግጥ ነው፣ ዓለም ሊደፋበት ነው፡፡” በዚህ ግጥም ውስጥ ስለ ጠላት ኃይል ማሳሰብያ ተሰጥቶናል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የምናገኘው ድል ተነግሮናል፡፡
ማጠቃለያ – ከአሸናፊዎች በላይ
ጠላቶቻችንን በዚህ ምድር ላይ እንዴት ድል እንደምንነሳ መማር ወሳኝ የሆነ የመንፈሳዊ ዕድገት አካል ነው፡፡ አማኝ ስለ ጠላቶቹ ማወቅና በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን መሣርያዎች መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ውጊያው ውስጥ ስንገባ በቃለ እግዚአብሔር የሰጠንን ተስፋ አጥብቀን ልንይዝ ይገባናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ ስምንተኛው ምዕራፍ ላይ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፡- “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?” ሊያሸንፉን የሚችሉ ብዙ ነገሮችን ከዘረዘረ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” በማለት ይደመድማል (ሮሜ 8፡37)፡፡ ከዚያም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ዓይነት ፍጥረት እንደሌለ በማረጋገጥ ይደመድማል (ሮሜ 8፡39)፡፡
(“ደቀ መዛሙርትን ማነጽ” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ ጽሑፍ ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር የተወሰደ)