መንፈሳዊ ውንብድና፤ የሐሰተኞች ነቢያት ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም። ጥንትም ዛሬም ሐሰተኞች ነቢያት እግዚአብሔር ወይም ኢየሱስ ወይም፥ ‘በኢየሱስ ስም’ ሲሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ወይም ኢየሱስ እንደሚሉ ሊመስለንና ልንወናበድ እንችላለን። ብዙዎች ይወናበዳሉ። እነዚህ ሰዎች ሰዎችን እያወናበዱ ስለሆነ መንፈሳዊ ውንብድና እየፈጸሙ መሆናቸውን በእርግጥ እንወቅ። መንፈሳዊ ውንብድና ከፈጸሙ መንፈሳውያን ወንበዴዎች ናቸው። መንፈሳዊ ውንብድና አለ፤ መንፈሳዊ ወንበዴዎችም አሉ።
ይህንን ‘መንፈሳዊ ውንብድና’ የሚለውን ሐረግ፥ ባለፈው ሳምንት እያነበብኩት ከነበረው የጸሎት-የንግድ ቤት?! ከተሰኘው የወንድም ተካልኝ ነጋ መጽሐፍ የወሰድኩት ነው። የጌታ ቤት ከጸሎት ቤትነት ወደ ጨረታና የችርቻሮ ንግድ ቤትነት እንዴት በፈጣንና እኩይ አካሄድ እየተለወጠ መሆኑን የሚናገር፥ ደግሞም ከመፍትሔ አሳቦች ጋር አሰናስሎ ያቀረበ ግሩም መጽሐፍ። ግዙት፤ አንብቡት።
ስለ ወንበዴ ጥቂት ልበል፤ ወንበዴ ወራሪ ጦር ሆኖ ከውጪ የመጣ አገር ወጊ አይደለም። ወንበዴ ቤቱና መንደሩ ኮስኩሶት የወጣ፥ አገዛዝ ያልተመቸው ወይም ለራሱ ጥቅም ሲል ፋንኖ ወጥቶና አፈንግጦ ሌሎችን በዙሪያው እየኮለኮለ፥ የዋሃንን እና ያልተማሩትን እያወናበደና እያታለለ ዋናውን አካል የሚወጋና የሚጎዳ፥ ሕዝብንም የሚያተራምስ ሰው ነው። ወንበዴ ከመደበኛው የኑሮ መስመር ወጥቶ፥ ተለይቶ፥ በስውርና በምስጢር፥ በማታለልና በማጭበርበር፥ ሲልም በማስፈራራትና በማስደንገጥ፥ በማገትና በመጉዳት፥ በአደባባይ ሳይሆን፥ በተጠያቂነት ሳይሆን፥ በሕጋዊነት ሳይሆን የሚንቀሳቀስ ዘራፊና አግበስባሽ ነው። ወንበዴ ሲዘርፍ ኅሊና የለውም፤ ሰዓት ፈትቶ ከመውሰድ ይልቅ ከእጅ ጋር ቆርጦ ይወስዳል፤ ቀለበት ቶሎ አልወልቅ ካለ ከነጣት ቆርጦ ይወስዳል፤ ጉትቻን ከጆሮ ጋር ይገነጥላል።
ከላይ ያልኩት መንፈሳዊ ወንበዴ ከጫካው ወንበዴ ጋር ተመሳሳይ ነገር የሚያደርግ ሆኖ ልዩነቱ ይህኛው ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ይዘት ያለው መሆኑ ነው። በተለምዶ መንገድ ጫካ የገባ ሳይሆን ‘መንፈሳዊ’ ጥሻ ውስጥ የገባ ሰው ነው። የመንግሥትን ሕግ የጣሰ ሳይሆን (ይህም በወጉ ከተፈተሸ የተጣሰ መሆኑ እውን ነው፤ ስሜትና ገንዘብና አካል ከተጎዳ፥ ነፍስ ከጠፋ ሕግ መጣስ አይደል?) ግን ከዚያ በላይ የእግዚአብሔርን ሕግ እየጣሰ፥ እየሰበረ፥ እያጣመመ፥ ለራሱ ስምና ጥቅም፥ ዝናና ካዝና የሚሠራ ጭፍራ ያለው የጎበዝ አለቃ ነው። የሚጎዳውና የሚወጋው፥ የሚያምሰውና የሚዘርፈው አላፊ መንገደኛን ሳይሆን የክርስቶስን አካል ቤተ ክርስቲያንን ነው።
የሐሰተኞች ነቢያት ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ መስሎን አንወናበድ። እነዚህ ሰዎች የክርስትና ቀለም የተቀቡ መንፈሳዊ ወንበዴዎች መሆናቸውን አንርሳ! ተአምራት መደረጋቸውንና ተአምራቱም በኢየሱስ ስም መደረጋቸውን ብቻ አንይ። ምልክቶችና ድንቆች በቅዱሳን በኢየሱስ ስምም፥ በሐሰተኞች በኢየሱስ ስምም፥ ያለ ኢየሱስ ስምም ይደረጋሉ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት በስሙ ታላላቅ ድንቅ ነገሮችን ያደርጋሉ። ይህ ድንቅ አይደለም። ድንቅ የሚያደርገው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ሐሰተኛ ድንቆችም አሉ፤ 2ተሰ. 2፥9-10 ይህንን እንዲህ ሲል ይነግረናል፤ ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም!
ይህ ስለ ሐሰተኛው ክርስቶስ እንዲሁም በዓመጸኛው መንፈስ ስለሚሠራው የሐሰት አሠራር የሚናገር ክፍል ነው። በኢየሱስ ስም የተደረገ ነገር ሁሉ በኢየሱስ የተደረገ ነው ማለት አይደለም። አይምሰለን። በማቴ. 7፥22-23 በስሙ ስለተደረጉ ድንቅ ነገሮች ይናገራል። ድንቆቹን ያደረጉት ሰዎች ግን አስደናቂ ሰዎች እንጂ የዳኑ ሰዎች አልነበሩም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። በስሙ ድንቅ አድርገዋል፤ ግን አልታወቁም።
የነቢያቱ ኢየሱስ ነቢያቱን የሚያዝዝ ሳይሆን ለነቢያቱ ትእዛዛት ደፋ ቀና እያለ የሚሠራላቸው ከሆነ፥ ብር አባዛ ሲሉት የሚያባዛላቸው ከሆነ፥ የብልጽግና አዋጅ አንባቢና አነብናቢ ከሆነ፥ ስልክ ቁጥር ተናግሮ ንስሐ የሚያስፈልገውን ኃጢአታቸውን የሚደብቅ ከሆነ፥ እንደተፈወሱ ነግሮአቸው ፈውሳቸውን ከስፍራው የሚያጠፋው ከሆነ፥ ሁሌ ምድራዊ፥ ቁሳቁሳዊና ሥጋዊ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለቸርቻሪዎች መደብር እንደሚያቀርብ አይሱዙ እየተጫነ መጥቶ የሚያራግፍ ብቻ ከሆነ፥ ስለ ምድራዊው ድሎት ብቻ እንጂ ስለ ሰማያዊው ሕይወትና ይልቁንም ስለ ዘላለማዊው ቅጣት የማይናገር ከሆነ፥ የመስቀሉ ዋጋ የኃጢአት ክፍያ መሆኑን ጨርሶ የማያስታውስና የማያሳስብ ከሆነ፥ እርሱን በማመናቸው፥ እርሱን በመከተላቸው ምክንያት ስደትና መከራ ጨርሶውኑ የማያገኛቸው መሆኑን የሚያውጅ ከሆነ፥ ገንዘብ የሚያገኙበትን አዳዲስ ቴክኒክ እየፈጠረ የሚያቀርብላቸው ከሆነ፥ ቤቱ የሸቀጥ መሸጫና የገንዘብ መለወጫ ሲሆን የማይቀናና ጅራፍ የማያነሣ ከሆነ፥ ይህ ኢየሱስ የተፈጠረ፥ ሰው-ሠራሽ ኢየሱስ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም። ይህ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ሳይሆን፥ ጳውሎስ በ2ቆሮ. 11፥4 የጻፈው ሌላ ኢየሱስ ነው። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። ሌላ ኢየሱስ ከተሰበከ ሌላ መንፈስ አለ። ሌላ ኢየሱስ ከተሰበከ ያ ወንጌል ልዩ ወንጌል ነው። የሚመስል ግን ያልሆነ ልዩ ወንጌል ነው። ስለዚህ እንጠንቀቅ፤ እናስጠንቅቅ።