ቤተ ክርስቲያን

ወሳኝ ጦርነት

አንዳንድ ጦርነቶች ውጊያዎች ብቻ ናቸው። እልቂቶችና ፍጅቶች ናቸው። ውጤታቸው ጥቅምና ስም እንጂ ዘላቂ ታሪካዊ እሴትና ሕዝባዊ ውጤት የላቸውም። አንዳንድ ጦርነቶች ግን እንዲህ አይደሉም። እነዚህ ጦርነቶች ባይደረጉና ድሉም ባይጨበጥ ኖሮ የዓለማችን ወይም የአገራችን መልኮች ሌላ ይሆን ነበር። እንዲህ ያሉ በጣም ብዙ ጦርነቶች አሉ። ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ ልጥቀስ።

አንድ፤ በ718 (እ ኤ አ) የፍራንኮች ንጉሥ ሆኖ ቻርልስ ማርቴል ሲነግሥ ዋናው ወራሪ ጦር ከሰሜን አፍሪቃ ተነሥቶ አውሮጳን እየመደመደ የነበረው የዓረብ ፈረሰኛ ወራሪ ሠራዊት ነበር። በጊዜው ኢስላም ገና 100 ዓመትም ባይሞላውም ከሃይማኖት ይልቅ ወራሪነት ያየለበት አካሄዱ ወደ ምሥራቅ እስከ ኢራን፥ ወደ ሰሜን እስከ ቱርክ እና ቢዛንቲን ግዛት፥ ወደ ምዕራብ እስከ ሰሜን አፍሪቃና ተሻግሮም እስጳኝና ፖርቱጋል ደርሷል። በዘመኑ ገዳማት የደለቡ ግምጃ ቤቶች ነበሩና እነዚያን መዝረፍ ትልቁ የዘመቻው ዒላማም ነበር። ቻርልስ በ732 በዛሬው ፈረንሳይ ቱር እና ፖይቲዬ (Tours and Poitiers) አካባቢ በአብደል ራህማን የተመራውን ጦር ገትቶ እንዲያፈገፍግ አደረገው። ከዚያ በኋላ ነው ቻርልስ በስሙ ላይ ‘ማርቴል’ የሚለው ቅጥያ የተጨመረለት። መርቴሎ ወይም መዶሻ ማለት ነው። ልክ በአይሁድ መቃባውያን ጦርነት ዘመናት የደፈጣ ውጊያዎቹ መሪ የነበረው ይሁዳ ‘መቃቢስ’ ተብሎ እንደተሰየመው ማለት ነው። መቃቢስም መዶሻ ማለት ነው። ቻርልስ ማርቴል ወራሪዎቹን ዓረቦች በቱር ውጊያ ባያቆማቸው ኖሮ የዓለማችን መልክ፥ በተለይም ክርስትና አሁን በምናውቀው መልኩ ሊገኝ ባልቻለም ነበር።

ሁለት፤ እ ኤ አ 1896፤ በኛ አቆጣጠር በ1888 የካቲት 23 በአድዋ ተራሮች ላይ የተፈጸመው ጦርነት ወራሪውን የኢጣልያ ጦር ክፉኛ ያዋረደ፥ የደቆሰና ጭራውን ቆልፎ እንዲያፈገፍግ ያደረገ ጦርነት ነበረ። ምንም እንኳ የአውሮጳውያንን ተስፋፊነት ባይገታም ያስደነገጠ፥ ለአፍሪቃውያንና ለጥቁሮች ደግሞ ትምክህት የሆነ ጦርነትና ድል ነበረ። ‘ምንሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ፤ ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ’ ተብሎ የተገጠመው እውነት ይሆን ነበር። የደጃዝማች ከበደ ተሰማን የታሪክ ማስታወሻ በዚህ ሳምንት ነው አንብቤ የጨረስኩት። እና ኢጣልያ እውነትም በበቀል ነበር በሕዝባችን ላይ የወረደችው። ጣሊያን ምንም በበቀል ከአርባ ዓመታት በኋላ ተመልሳ ብትመጣም የቀድሞው ድል ለዚህኛውም ዋልታና ማገር ሆኖ ነበር። የአድዋው ጦርነት በአውሮጳ ጋዜጦች፥ ‘ታሪክ ተገለበጠ’ ተብሎ የተጻፈለት ነበረ። ያ ድል ባይፈጸም የአገራችን መልክም የአሁኑ አይሆንም ነበር።

እንዲህ ያሉ ብዙ ወሳኝ ጦርነቶች መዘርዘር ይቻላል። ታሪክን ተንተርሼ ሌላውን ትልቁንና ታላቁን ወሳኝ ጦርነትና ድል ልናገር እወድዳለሁ። የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን የተሸነፈበት አንድ ወሳኝ ጦርነት ተደርጎ በጦርነቱም ሰይጣን ጉድ ሆኖ ተሸንፎአል። ጦርነቱ ተለምዶአዊ ጦርነት ሳይሆን ምጸት የሚመስል፥ አሸናፊው በመስቀል የሞተበት ጦርነት ነው። ስፍራው ጎልጎታ ቀራንዮ ነው። የጦርነቱ ድል የታወቀውና የተረጋገጠው በሦስተኛው ቀን የሞተው ሞትን ረትቶ፥ ድል ነሥቶ፥ በትንሣኤ አካል በፈሪና ተስፋ የቆረጡ ‘ሠራዊቱ’ መካከል የተገኘ ጊዜ ነው። ከዚያ ወዲህ ያ ሠራዊት ተስፋቢስ ሠራዊት አልሆነም። ሞትን የናቀ፥ ለነፍሱ ያልሳሳ፥ ድልን ያወጀ፥ ድል የነሣ ሠራዊት ነበረ፤ ነውም።

ሆኖም ጦርነቱ በድል ቢደመደምም ውጊያው ግን እየቀጠለ ይገኛል፤ ይቀጥላልም። ልክ እንደ ጣሊያን ቂምና በቀል ይመስላል። ሰይጣን ወሳኙ ጦርነት እንደተጠናቀቀ አውቆአል። ጥቂት ጊዜ እንደቀረውም ያውቃል። በዚህ አጭር ጊዜው የሚያደርገው ጦርነት ጦርነት ሳይሆን ውጊያ ነው። ስልታዊ ውጊያ ነው። አንዳንዱ እንዲያውም ውጊያ ሳይሆን ድግስ ነው የሚመስለው። ፈጽሞ መንፈሳዊ መልክና ቅርጽ የያዘ ነው። በዘመናት በካበተ ልምዱ ከአሳዳጅነት ይልቅ መመሳሰልና ማስመሰል የሚያዋጣ መሆኑን ሰይጣን ያውቀዋል። ስለዚህ ሃይማኖታዊ፥ መንፈሳዊ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊም መስሎ መቅረብና መታየትን ከመቼውም ይልቅ እየተጠቀመበት ይገኛል።

በዘመናችን ሰይጣን ሰዎችን ለሌላው የወደፊቱ የራሱ ወሳኝ ጦርነቱ እያዘጋጀ ያለው ሰዎች ምልክቶችና ድንቆችን እየተከተሉ ኋላ ሐሰተኛው ክርስቶስ እና ሐሰተኛው ነቢይ ሲመጣና ምልክቶችን ሲያደርግ ያለ ምንም ጥርጥር ግር ብለው እንዲቀበሉት ክትባት እየወጋ ነው። ዛሬ ሰዎች በመስቀል ላይ ወሳኙን ጦርነት ድል ካደረገው ጌታ ከክርስቶስ ጋር ምንም ቁርኝት ሳይኖራቸው ምልክቶችና ድንቆች እያዩ እንደ ጀሌ እንዲግተለተሉ ሲደረጉ ይታያል። ሕይወታቸውን ጠጋ ብለን ስናይ ከዚህ ጌታ ጋር ግንኙነትና ቁርኝት የላቸውም። የነበራቸውም እንኳ እነዚህን ሐሰተኛ ነቢያት መከተል ሲጀምሩ ከዚህ ሕያው ግንኙነት የተላቀቁ ይሆናሉ። ቃሉን አያነብቡም፤ ቅድስና የራቃቸው ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያናቸውንና አገልግሎታቸውን ለምናምንቴ ነገር ለውጠው የሚኮበልሉ ናቸው። አዚም የተደረገባቸው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለው ነው። አንድ ቀን እንዲባንኑ ጦርነቱ ይቀጥል።

መጽሐፍ ቅዱስ ኋላ ሰዎች አውሬውን ወይም ዘንዶውን እንዴት እንደሚከተሉት ሲናገር፥ ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፦ አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ይላል፤ ራእ. 13፥3-4። እየተከተለ ተደነቀ። ድንቅ መፈለግና መደነቅ ለኋለኛው መደነቅ ጥርጊያ መሆኑን አንርሳ።

ወሳኙ ጦርነት በቀራንዮ በድል ተፈጽሞአል፤ መንፈሳዊው ውጊያ ግን ይቀጥላል።