ክርስቲያናዊ ሕይወት አጭር ሩጫ ሳይሆን ማራቶን ነው፡፡ ማራቶንን ለመሮጥ የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ማዳበር ጊዜን ይፈልጋል፡፡ አንዳንድ አማኞች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን ስለሚያነቡና በቀን ለብዙ ሰዓታት ስለሚጸልዩ ቅዱሳን ሰዎች ታሪክ በማንበብ ወይም በመስማት በነርሱ ተግባር በመነሳሳት ተመሳሳይ ልማድ ለማዳበር ይሞክራሉ፡፡ በቅፅበት ያንን የሚመስል መንፈሳዊ ልምምድ ውስጥ መግባት የሚችሉ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኞቻችን ያንን ማድረግ አንችልም፡፡ ያ ደግሞ ምንም ማለት አይደለም፡፡ በቀጣይነት እንደምንመለከተው እግዚአብሔር ቃሉን እንድናጠናና እንድንጸልይ ይጠብቅብናል፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ በመጀመር ማሳደግ የተሻለ ነው፡፡
አማኝ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚከተልበት መጠን የዕድገት መጠኑን ይወስናል፡፡ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት መከተል ሁሌም ቀላል አይደለም ነገር ግን ውጤቱ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ አማኝ ተከታዮቹን ተግባራት በፈጸመ ቁጥር በመንፈሱ ያድጋል፡-
የእግዚአብሔርን ቃል መረዳትና መተግበር
የእግዚአብሔርን ባሕርያት፣ ዓላማውንና መንገዶቹን ባወቅን ቁጥር እናድጋለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እግዚአብሔር ለኛ ራሱን ለመግለጥ የሚጠቀምበት ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የተሻለ ለማወቅ አማኝ የእግዚአብሔርን ቃል ትርጉም በመስማት፣ በማንበብ፣ በማጥናት፣ በመሸምደድና በማሰላሰል መረዳት ይኖርበታል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛው መልዕክቱ የቃለ እግዚአብሔርን አስፈላጊነት እንዲህ ሲል ገልጿል፡- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡” (2ጢሞ. 3፡16-17)
ቃሉን ማጥናት በራሱ የመጨረሻ ጉዳይ አይደለም፡፡ የማጥናት ዓላማ መማርና ማደግ እንጂ እውቀትን ማከማቸት አይደለም፡፡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ዕውቀት ያላቸውና ሰፊ የሆኑ ንባቦችን የሸመደዱ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር የማያምኑ እንዲሁም እርሱን የመታዘዝ ሐሳብ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ያዕቆብ አማኞች የቃሉ ሰሚዎች ብቻ በመሆን ራሳቸውን እንዳያታልሉ ያስጠነቅቃል (ያዕ. 1፡22)፡፡
መጸለይ
እግዚአብሔር ከአማኞች ጋር የሚገናኝበትን ክፍት መስመር አዘጋጅቷል፡፡ ጸሎት ማለት በቀላሉ እግዚአብሔር ሁሌም እንደሚሰማን በማወቅና ዓላማውን ከግብ ሊያደርስ እንዲሁም እኛን የበለጠ ሊጠቅም በሚችልበት ሁኔታ ምላሽ እንደሚሰጠን በማወቅ ከእግዚአብሔር ጋር ንግግር ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሆኖም ጸሎት ማለት የገዛ አቅማችንን ካሟጠጥን በኋላ የምንጠቀመው ነገር አይደለም፡፡ ይልቁኑ ለገባንባቸው ሁኔታዎች ሁሉ የምንሰጠው ተፈጥሯዊ ምላሽ ሊሆን ይገባል፡፡ ምሪት ለመጠየቅ፣ ፍላጎቶቻችን እንዲሟሉልንም ሆነ ጥበቃ እንዲደረግልን መጀመርያ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ማለት ያስፈልገናል፡፡ ኤፌሶን 6፡18 እንዲህ ይለናል፡- “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፡፡”
ከአማኞች ጋር ሕብረት ማድረግ
ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ላይ ያለንን ግንኙነት ማደስ ወደጎን ከሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር መንገድ ይጠርጋል፡፡ ሆኖም ይህ ግንኙነት በጋራ ጊዜን በማሳለፍና በክርስቶስ ሆነን የምንካፈለውን ሕይወት በጋራ በማጣጣም እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል፡፡
ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጋር መሰባሰባችንን እንዳንተው የሚያስጠነቅቀን (ዕብ. 10፡24-25)፡፡ አንዳችን ለሌላችን እናስፈልጋለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት በግል የምንኖረው ሕይወት ሆኖ አልተሠራም፡፡ ከሌሎች አማኞች ጋር በቋሚነት ሕብረት ማድረግ መፅናናትን፣ ተጠሪነትን፣ ትምህርትን፣ መበረታታትን፣ ድጋፍንና አቅጣጫን ይሰጠናል፡፡ አማኝ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሳትፎ ከሌለው የተዛባ አስተሳሰብ፣ የስሜት ድጋፍ ማጣት፣ የደህንነት ስሜት ማጣትና የተጠሪነት አለመኖር ችግሮች ይገጥሙታል፡፡
ሌሎችን ማገልገል
ከሌሎች አማኞች ጋር ጊዜን ከማሳለፍ ባለፈ አንዳችን ሌላችንን ልናገለግል ይገባል፡፡ አሁንም ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው፡፡ ለመገልገል ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል እንደመጣ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል፡፡ ኋላ ላይም እርሱ ሲያገለግል እንደነበረው ሁሉ እነርሱም ሌሎችን እንዲያገለግሉ ነግሯቸዋል (ማቴ. 20፡28፣ ዮሐ. 13፡15)፡፡
ሌሎችን ማገልገል እግዚአብሔር ባሕርያችንን ለመቅረፅ የሚጠቀምበት መንገድ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑ አገልግሎት ሰጪውንም ሆነ ተቀባዩን የሚጠቅም ነው፡፡ ተቀባዩን የሚጠቅመው ፍላጎቱን በማሟላት ነው፡፡ ሰጪውን ደግሞ የሰዎች ፍላጎት ሲሟላ በመመልከት እንዲደሰት በማድረግና በሌሎች ላይ ተፅዕኖን እንዲያመጣ በመርዳት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሁላችንም በመስጠትና በመቀበል ጫፍ ላይ ስለምንሆን ደስታውን እኩል እንጋራለን፡፡
ለሌሎች የምንሰጠው አብዛኛው አገልግሎት የጀግንነት ተግባርን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በየዕለቱ ፍቅራችንን የምንገልፅባቸው መልካም የማበረታቻ ቃላትን መናገር፣ ሰዎችን ማዳመጥ፣ ምሳ መጋበዝ፣ በጥሩ ዓይን መመልከትና እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እያደረገ ያለውን ማካፈልን የመሳሰሉ ቀለል ያሉ ተግባራት ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት የዘውትር መልካምነትን ያበረታታል፡- “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ፡፡” (ገላ. 6፡10)
(“ደቀ መዛሙርትን ማነጽ” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ ጽሑፍ ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር የተወሰደ)