“በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት ያላቸው ግንዛቤ በጣም የተዛባ ከመሆኑ የተነሳ ምንም ግንዛቤ የላቸውም ያሰኛል፡፡”
መንፈስ ቅዱስ ከሥሉስ ቅዱስ አካላት መካከል አንዱ ነው፤ ልናመልከውና ልንታዘዘው ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱ ቢሄድ መንፈስ ቅዱስን ስለሚልክላቸው መሄዱ መልካም እንደሆነ ነግሯቸዋል (ዮሐ. 16፡7)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከእነርሱ ተለይቶ እንደሚሄድ በመናገሩ ምክንያት አዝነውና ፈርተው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ይህ ዜና በእጅጉ አስደሳች ነበር፡፡
ደህንነትን በመቀበያው ቅፅበት መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ሕይወት ውስጥ በማደር መዳኑን ያረጋግጥለታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ መንፈስ በውስጣቸው የማይኖር ሰዎች ክርስቲያኖች አለመሆናቸውን ተናግሯል (ሮሜ 8፡9)፡፡ በአንፃሩ ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ማህተም እንደታተሙ ተናግሯል (ኤፌ. 1፡13)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሎ በጻፈ ጊዜ ተመሳሳይ ሐሳብን አስተጋብቷል፡- “ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን፡፡” (1ዮሐ. 4፡13)
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ደህንነትን በመቀበያችን ቅፅበት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት እንዳለባቸው አጥብቆ ይናገራል፡፡ “በመንፈስ መመላለስ” የሚለው ሐሳብ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሚገኙት መልዕክታት ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እንመለከታለን፡፡ “በእምነት መኖር” “ወደ እግዚአብሔር መቅረብ” እንዲሁም “ለእግዚአብሔር መገዛት” የሚሉት አማራጭ ሐረጎች በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ከሚለው ሐሳብ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “በመንፈስ ቅዱስ መሞላት” የሚለው አባባል አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መታጠቃቸውን፣ ጥበብንና ምሪትን ማግኘታቸውን ለመግለፅ የተነገረ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት መንፈስ ቅዱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመምጣት ምስክሮቹ ይሆኑ ዘንድ ኃይልን እንደሚሰጣቸው ነግሯቸዋል (ሐዋ. 1፡8)፡፡ ይህ የተስፋ ቃል በበዓለ ሃምሳ ዕለት ተፈፅሟል፡፡ ኤፌሶን 5፡18 ላይ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “መንፈስ ይሙላባችሁ …” ይላል፡፡
“መሞላት”
የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ለመረዳት ኤፌሶን 5፡18 ላይ የሚገኘው ውስብስብ የሆነው የግሥ አወቃቀር ሊብራራ ይገባል፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ የሚገኘው ግሥ አራት ውቅሮች አሉት፡፡ የአማርኛው ትርጉም የግሪኩን ፅንሰ ሐሳብ በቂ በሆነ ሁኔታ ስላላስቀመጠ በጥልቀት ማጥናት ይኖርብናል፡፡
ትዕዛዝ፡- መሞላት ትዕዛዝ ነው
ይህ ትዕዛዝ አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ መሞላት ምርጫ ሳይሆን የአማኝ ሕይወት አካል ነው፡፡ ለአማኝ መንፈስ ቅዱስን ሳይሞላ የክርስትናን ሕይወት መኖር መሞከር ጥልቅ ዋናተኛ የአየር መስጫውን ሳይከፍት ውኀ ስር እንደመጥለቅ ነው፡፡
ብዙ ቁጥር፡- ትዕዛዙ አማኞችን ሁሉ ይመለከታል
ኤፌሶን 5፡18 ላይ “ይሙላባችሁ” ብሎ ሲናገር የብዙ ቁጥርን አመላካች ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ትዕዛዙ የተሰጠው ለአንድ ሰው ወይንም ለተወሰነ ቡድን ሳይሆን ለመላው ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ነው፡፡ ይህ ትዕዛዘት ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ወንድ፣ ሴት፣ ጠንካራ፣ ደካማ፣ በሳል፣ ለጋ ሳይል ሁሉንም አማኞች የሚያጠቃልል ነው፡፡
በመንፈስ ቅዱስ መሞላት በክርስትና ከመብሰል ጋር አንድ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፤ ነገር ግን የብስለት ሒደቱ ቁልፍ አካል ነው፡፡ አንድ ሰው በሳል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ሊሞላ ይችላል ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ በሕይወቱ ውስጥ ሳይሠራ በክርስቶስ ወዳለው ብስለት ሊደርስ የሚችል ማንም የለም፡፡
ተግባር ተቀባይ፡- መሞላቱ በኛ ሊፈፀም አይችልም
“ይሙላባችሁ” የሚለው ተግባር ተቀባይ መሆንን በሚያሳይ ሁኔታ ሲተረጎም “መንፈሱ ራሱ እናንተን ይሙላችሁ” የሚል አንድምታ ነው ያለው፡፡ በሌላ አባባል እግዚአብሔር ራሱ ሊያደርግልን የሚሻው ነገር ነው፡፡ መጀመርያ እኛ እንድናሟላው የሚጠበቅብን አስቸጋሪ መስፈርት የለም፡፡ ምጡቅ የሆነ ደረጃ ላይ መድረስ አይጠበቅብንም፤ የሆነ ዓይነት ዕውቀት ማግኘት አይጠበቅብንም፤ የሆኑ ቴክኒኮችን መማር አያስፈልገንም፤ እግዚአብሔር በመንፈሱ ሊሞላን ብቻ ነው የሚገባው፡፡
የአሁን፡- ሙላቱ ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል
ግሡ የአሁን ጊዜን ገላጭ ነው፡፡ አባባሉ በግሪክ ቋንቋ ድርጊቱ አሁንም አሁንም ሳያቋርጥ መደጋገሙን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ ሳይቋረጥ ሊከናወን ይገባል፡፡
“ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” (ዮሐ. 3፡8)። በደህንነት ውስጥ ምስጢራዊ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር እንዳለ ሁሉ በየዕለቱ በሚደረገው የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ረገድም ሙሉ በሙሉ ሊብራራ የማይችል ምስጢር አለ፡፡ ሆኖም ሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ መርሆችን በመረዳት አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደሚሞላ መረዳት እንችላለን፡፡ እነዚህም ወደ እግዚአብሔር መቅረብና ለእግዚአብሔር መገዛት ናቸው፡፡
ወደ እግዚአብሔር መቅረብ
ክርስትና በባሕርዩ ከክርስቶስ ጋር ሕብረት ማድረግ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ እንደ አዲስ በመወለድ ከእርሱ ጋር ሕብረት እንጀምራለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ያንን ሕብረት ማጥበቅ፣ ማጥለቅና ማስፋት ነው፡፡ ሁሉም ክርስቲያናዊ ዕድገት መሠረቱ ይህ ሕብረት ነው፡፡ ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከኢየሱስ ጋር ካለን ሕብረት ይመነጫል፡፡
ዮሐንስ 7፡37-39 በመንፈስ ቅዱስ ሙላትና ከክርስቶስ ጋር ባለን ሕብረት መካከል ስለሚገኘው ግንኙነት አፅንዖት ሰጥቶ ይናገራል፡፡
“ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ፡፡ ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና፡፡”
ኢየሱስ አማኞች ከእርሱ ጋር ሕብረት በማድረግ በመንፈስ ቅዱስ እንደሞሉ ጥሪ አቅርቦላቸዋል፡፡ ይህ ጥሪ በዮሐንስ 7፡37-39 ላይ በሚገኙት ሦስት ንግግሮች ተገልጧል፡፡ እነዚህንም እንደሚከተለው እናያለን፡-
“ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ”
ጥማት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ አካላዊ ጥማት ሰውነታችን እርካታ እንደሚያስፈልገው እንደሚያመለክተው ሁሉ መንፈሳዊ ጥማትም የሚያስፈልገንን ነገር አመላካች ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥማታችንን ማወቅ ወደ ክርስቶስ እንድንመጣ ያደርገናል፡፡
ይህንን ጥልቅ የነፍስ ጥማታችንን ለማርካት ወደ ኢየሱስ መምጣት ግድ ይለናል፡፡ ማንም ሰው ወይንም የትኛውም ነገር ይህንን ጥማታችንን ሊያረካልን አይችልም፡፡ “ይምጣ” የሚለው ቃል የማያቋርጥ ድርጊትን አመላካች ሲሆን ወደ ኢየሱስ ደጋግመን መምጣት እንዳለብን ያሳያል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጥማት እንደ ሥጋዊ ጥማት ሁሉ ደጋግሞ መርካት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ እውነታ መንፈሳዊ ጥማት ከደህንነት በፊትም ሆነ በኋላ እንዳለ እንደሚቀጥል ያሳየናል፡፡ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጣጥሙ ቢሆኑም ይህ ግንኙነት ግን በኛ ኃጢአትና በወደቀው ዓለም ውስጥ በመኖራችን ምክንያት ጥቃት ይደርስበታል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ወደ እርሱ እንድንመጣ ከመጋበዝ ውጪ እንደማያስገድደን ልብ በሉ፡፡ በእርሱ መንገድ እንድንሄድ አያስገድደንም ነገር ግን ወደ እርሱ በመምጣት ከእርሱ ጋር እንድንኖርና የዘላለምን ሕይወት እንድንቋደስ ዕድልን ይሰጠናል፡፡ ይህ አቋም ከባሕርዩ ጋርና ግብረ ገባዊ ፍጥረታት አድርጎ እኛን ከመፍጠሩ ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ ከልቡ ይፈልገናል ደግሞም ወደ እርሱ እንድንመጣ ይጓጓል፡፡ የእግዚአብሔር “የግብዣ” ባሕርይ በመጽሐፍ ቅዱስ የደህንነት አስተምህሮ ውስጥ ድርና ማግ ሆኖ እንመለከታለን፡፡
“ይጠጣ”
ወደ ክርስቶስ ከመጣን በኋላ ከእርሱ መጠጣት ያስፈልገናል፡፡ የምንጠጣውም በሚከተሉት መንገዶች ነው፡-
- ከእርሱ ጋር መተባበር – ይህ ማለት በመገኘቱ ውስጥ መኖርና ጊዜን ከእርሱ ጋር ማሳለፍ ነው፡፡
- እርሱን ማምለክ።
- እርሱን መስማት – ቃሉን ማንበብ፣ በፊቱ በጥሞና መሆን፣ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት በመከተል፡፡
- ሸክማችንን በእርሱ ላይ መጣል – ስለ ፍላጎታችን፣ ስለ ጉዳታችንና ስለልባችን መሻት በእግዚአብሔር ፊት ቅኖችና ግልፅ በመሆን ነፍሳችንን ለእርሱ መስጠት፤ ያስጨነቀንን ነገር ሁሉ ለእርሱ መንገር፡፡
- እንዲያገለግለን ለእርሱ መፍቀድ – መንፈሱ ለመንፈሳችን እንዲያገለግል መፍቀድ፣ ፍርሃታችንን እንዲያረግብ፣ ቁስላችንን እንዲያክምና ልባችንን እንዲያበረታ መፍቀድ፡፡
በነዚህ መንገዶች ከክርስቶስ ጋር ጊዜን ስናሳልፍና ከእርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ደስ ስንሰኝ መንፈሳዊ ጥማታችንን ሲያረካ እናየዋለን፡፡
“በእኔ የሚያምን”
ማመንን የሚያሳየው ቃል በተደጋጋሚ የሚፈፀምን ተግባር የሚያመለክት ነው፡፡ መጀመርያ ላይ ኢየሱስ ከኃጢአታችን እንዲያድነንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲያድስ ወደ እርሱ እንመጣለን፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስፈልገን ትልቁ ነገር ነው፡፡ በየዕለቱ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ስናጣጥም ኢየሱስ ለሚያስፈልገን ነገር ሁሉ እርሱን እንድንደገፍና እንድንታመን ይነግረናል፡፡
ወደ ኢየሱስ መምጣት፣ ከእርሱ መጠጣትና እርሱን መታመን አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲትረፈረፍ ያደርገዋል (ቁ. 38)፡፡
ለእግዚአብሔር መገዛት
ለእግዚአብሔር መገዛትና ፈቃዱን ማድረግ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ሌላው ገፅታ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ በፈቃዳችን ለእግዚአብሔር በመገዛትና እንዲያበረታንና እንዲመራን ወደ እርሱ በመቅረብ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ አለመታዘዛችንን ለመግለፅ ሁለት ቃላትን ይጠቀማል፡፡ ኤፌሶን 4፡30 ላይ መንፈስ ቅዱስን “እንዳናሳዝን” ተነግሮናል፡፡ በዚያ አውድ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ አማኞች ሌሎች ሰዎችን በትክክል እንዲንከባከቡ ይመክራቸዋል፡፡ ስለዚህ የተሳሳቱ መንገዶችን መከተል፣ የድፍረት ኃጢአት ማድረግ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለንን ሕብረት ያበላሻሉ፡፡ 1ተሰሎንቄ 5፡19 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “መንፈስን አታጥፉ” ይላል፡፡ መንፈስን የምናጠፋው እርሱን ከመከተል በማቋረጥና በራሳችን ኃይል የሆነ ነገር ለማድረግ በመሞከር ነው፡፡ እነዚህ ኃጢአቶች አንዳንዴ መንፈስ ቅዱስን የመግፋት ኃጢአቶች ተብለው ይታወቃሉ፡፡
እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ በራሳችን መንገድ ስንሄድ በመንፈስ ቅዱስ እንደገና በመሞላት ወደ መንገዱ መመለስ ግድ ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ወደ መንገዱ መመለስን አስቸጋሪ ሥራ አላደረገብንም፡፡ መጀመርያ ያደረግነውን በመናዘዝ ንስሐ መግባት ያስፈልገናል፡፡ መናዘዝ ማለት ያደረግነው ነገር የተሳሳተ መሆኑን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መስማማት ነው (1ዮሐ. 1፡9)፡፡ ንስሐ ማለት ስለ ኃጢአታችን የልብ ለውጥ በማድረግ መንገዳችንን በመተው ወደ እግዚአብሔር መንገድ መመለስ ማለት ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ በፈቃደኝነት ለእርሱ በመገዛት በመንፈሱ ደግሞ እንዲሞላን በእርሱ መታመን ይኖርብናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ የእርሱ ፈቃድ በመሆኑ ደግሞ ይሞላናል፡፡
(“ደቀ መዛሙርትን ማነጽ” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ ጽሑፍ ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር የተወሰደ)