ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንዲት በአንድ ክርክር ውስጥ ገባሁ። ክርስቲያን መጠጥ መጠጣት አልተከለከለምና በምግብ ቤት ውስጥ መጠጥ ቢሸጥ ገበያውን እስከሳበ ድረስ ክፋት የለበትም የሚል አቋም የያዘ አንድ ወንድም እና ሌላዋ ደግሞ ለምን ከቶውኑ መጠጥ መጠጣት ታሰበ? እኛ የማንጠጣውን ነገር ለምን መሸጥስ አስፈለገ? የሚል ጥያቄ የያዘች ናት። በጊዜው የተረዳሁትን ካካፈልኩ በኋላ ያንኑ ምሽት ተቀምጬ ይህችን ትንሽ መጣጥፍ አሰናዳሁ።
ለክርስቲያን ወይን መጠጣትና ማጠጣት የተፈቀደ ነውን? በአንድ ጎራ አስካሪ መጠጥን የሚኮንኑ ከቶም ሊጠጣ ይቅርና ሊታሰብም የተገባ አይደለም የሚል አቋም የያዙ አሉ።
በሌላው መጠጥ መጠጣት ይፈቀዳል ስካር ነው የሚከለከለው? የሚል አቋም ያላቸው አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎች የተመሰገኑና የተመሰከረላቸው ሰዎች የወይን ጠጅ ጠጥተዋል፤ ጌታም የወይን ጠጅ ጠጥቶአል፤ ታዲያ ቢጠጣ ምን አለበት? የሚሉ ናቸው። ‘በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ፤ መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ’ ነው ያለው ዘፋኙ የሚሉ ዓይነቶቹ ናቸው (ምንም ዘፋኙን ባይጠቅሱም)። ከነዚህ አንዳንዶቹ ራቅ ያለና እስከ መስከርስ ቢሆን? የሚል እርምጃ ይራመዳሉ።
በሁለቱም መሐል ያሉቱ ደግሞ ይህ የግለሰቡ ኅሊና ጉዳይ ነውና ለግሉ ውሳኔ መተው ነው እንጂ በዚህ ጉዳይ መነጋገር አስፈላጊ አይደለም የሚሉ መሐል ሰፋሪዎች ናቸው። የማይጠጣ ለጌታ ብሎ አይጠጣ፤ የሚጠጣም መንፈስ ከመሰከረለት ይኮምኩም ባዮች ናቸው። ስለዚህ አስካሪ መጠትም ሆነ ሌሎችም ሱስ የሚያስይዙም ሆኑ የማያስይዙ ነገሮች የግለሰቡ ኅሊና ውሳኔ ነው የሚል ኅሊናዊ አቋም ይይዛሉ።
ከነዚህ የማይርቁቱ ሌሎች ደግሞ መጠጣትም ሆነ አለመጠጣት ሰውነታችንን/ነፍሳችንን የማርከስ አቅም ስለሌለውና ደኅንነታችንን ከቶም ሙሉ ወይም ጎዶሎ ስለማያደርገው ይህ ጉዳይ እጥያቄ ውስጥም መግባት የለበትም የሚል ዳኝነት ይዳኛሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው አገባባቸው በመነሣት ወይንና የወይን ጠጅ እንዲሁም የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ የተለያዩ መሆናቸውን ማወቅ እንችላለን። ምክንያቱም እነዚህ ቃላት ተነባብረው የተቀመጡባቸው ስፍራዎች አሉና፤ ለምሳሌ፥ ዘሌ. 10፥9፤ ዘዳ. 29፥6፤ መሳ. 13፥4-14፤ 1ሳሙ. 1፥15፤ ኢሳ. 24፥9፤ ሉቃ. 1፥15። ከነዚህ አጠቃቀሶች በመንደርደር የወይን ጠጅ ሁሉ አስካሪ መጠጥ ነው ብለን እንዳንደመድም ሊያስገድደን የሚችል እውነት መኖሩን እናስተውላለን።
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ጥቂት አሳቦችን በነጥብ አስቀምጣለሁ። ለእያንዳንዱ ነጥብም ጥቂት ናሙና ጥቅሶች አክላለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የወይን ጠጅ በዘመናችንም ያንኑ ቃል ይወክላል። አስካሪ መጠጥም ማናቸውንም አስካሪ መጠጥ ሊወክል ይችላል።
- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወይን ልብን የሚያስደስት መሆኑ ተጽፎአል።
አንድ የኢትዮጵያ የወይን ጠጅ ፋብሪካ፥ አዋሽ የወይን ጠጅ ፋብሪካ ይመስለኛል፥ በመጠጥ ማከፋፈያ የጭነት መኪናዎቹ ላይ የመዝ. 104፥15ን በግዕዝ ወይን ያስተፌስህ ልበ ሰብእ ብለው ጽፈው ይዞሩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በተወገዘበት የደርግ ዘመን እንኳ ሳይቀር ይህ ጥቅስ መነገጃ ሆኖ ነበር። እውን ወይን ያስተፌስህ? የወይን ጠጅ በእርግጥም ልብን ያስደስታል፤
መሳ. 9፥13 ወይኑም፥ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
ዘካ. 10፥7 የኤፍሬምም ሰዎች እንደ ኃያላን ይሆናሉ፥ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ደስ ይለዋል ልጆቻቸውም አይተው ደስ ይላቸዋል፥ ልባቸውም በእግዚአብሔር ሐሤት ያደርጋል።
መክ. 2፥3 የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ።
መዝ. 104፥15 ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።
- ወይን/ወይን ጠጅ በብሉይም ሆነ በአዲሱ ኪዳናት ዘመን የተለመደ ባህላዊና ማኅበራዊ መጠጥ ነው።
ለመስተንግዶ፥ ለሠርግ፥ ለበዓላት፥ ለድግስ፥ ለነገሥትና ለመኳንንት፥ ለስጦታ፥ ለክፍያም ይውል ነበር። ንጉሦች ወይንና የወይን ጠጅ የሚያከማቹባቸው ማከማቻዎችና በተለይ ለዚህ የተሾሙ ሹሞችም ነበሩአቸው።
ዘፍ. 14፥15 የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ።
1ሳሙ. 16፥20 እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዋት እጅ ወደ ሳኦል ላከ።
1ሳሙ. 25፥11 እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው።
1ሳሙ. 25፥18 አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች።
2ሳሙ. 16፥1-2 ዳዊትም ከተራራው ራስ ጥቂት ፈቀቅ ባለ ጊዜ የሜምፊቦስቴ ባሪያ ሲባ ሁለት መቶ እንጀራ፥ አንድ መቶም ዘለላ ዘቢብ፥ አንድ መቶም በለስ፥ አንድ አቁማዳም ወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ተገናኘው። ንጉሡም ሲባን፦ ይህ ምንድር ነው? አለው። ሲባም። አህዮቹ የንጉሥ ቤተ ሰቦች ይቀመጡባቸው ዘንድ፥ እንጀራውና በለሱ ብላቴኖቹ ይበሉት ዘንድ፥ የወይን ጠጁም በበረሀ የሚደክሙት ይጠጡት ዘንድ ነው አለ።
1ዜና 12፥40 ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢበ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።
2ዜና 2፥10 እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባሪያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።
1ዜና 27፥27 በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚሆነው በወይኑ ሰብል ላይ ሸፋማዊው ዘብዲ ሹም ነበረ።
ነህ. 2፥1 በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር።
ነህ. 5፥18 ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ በአሥር በአሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልሻም ነበር።
ጌታ በመጀመሪያ ያደረገው ተአምሩ ውኃን ወደ ወይን መለወጡ ነበር። ይህንን ተአምር አስካሪ መጠጥ የመጠጫ ዋነኛ መከራከሪያ የሚያደርጉ ጠጪዎች አሉ። ይህ ወይን ጠጅ የሚጠጣበት ባህላዊ ድግስ ነው። ሠርግ ነው። ወይን ጠጁም ከመናኛ ወይም ከቀጠነው እስከ መልካሙ ወይም ኃይለኛውና አስካሪው የሚለያይ ነው። ጌታ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠው ወደ መናኛው ሳይሆን ወደ መልካሙ ነው። ይህ በሰው እጅና ጊዜ የተጠመቀው ስላልሆነ ከመልካሙም የተሻለው መሆን አለበት።
ዮሐ. 2፥ 3 እና 9-10 የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።
ይህ ሠርግ ጌታ ተጋብዞ ወይም ታድሞ የሄደበት ሠርግ ነው። እናቱ ማርያም ውስጠኛና የቅርብ ሰው ሳትሆን አትቀርም። ባይሆን የጓዳውን ምስጢር፥ የወይን ጠጁን ማለቅ፥ ለጌታ አትናገርም ነበር። ይህ የወይን ጠጅ መጠጥ የሚጠጣበት ድግስ ስፍራ ነው፤ ወይን ጠጅ ደግሞ አለቀ። ጌታ በጉዳዩ ተሳታፊ ካልሆነ የሚያሳፍር ነገር ሊከሰት ነው። ጌታ ተአምራትን ያደርግ የነበረው ሁኔታዎችን ለመለወጥና ተአምራትን ማድረጉ አስፈላጊ ሲሆን ነው። ጌታ ተአምራትን እንዲያው እንደ በታኝ ዘሪ ሲበትን አይታይም። እዚህ አስፈልጎ ነበር። ደግሞም የመጀመሪያ ተአምሩ ነው። ጌታ በአካል በተገኘበት ሠርግ ጎዶሎነት አይኖርምና በመልካሙ ወይን ተአምር ሠርጉን ከጎዶሎነትና ከእፍረት ጠበቀ። ሠርጉን የታደገው ወይን ጠጁ ሳይሆን የጌታ መገኘት ነው። የጌታን የራሱን ምሳሌነት በሌላ ነጥብ እንመለከታለን።
- ለመቅደስ አገልግሎትና ለመስዋእት ይቀርብ ነበር።
የወይን ጠጅ እንደ መጠጥ ቁርባን እና የሚፈስስ መስዋእት በመሆን ይቀርብ ነበር። የወይን ጠጅ እንደ አስራትም ሆኖ ለሌዋውያን ይሰጥ ነበር። ሕዝቡ በዓመታዊ በዓላቸውን ደስ እንዲላቸው ወይን ጠጅና ብርቱ መጠጥ ሊጠጡ ተፈቅዶላቸዋል።
ዘሌ. 23፥13 የእህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ይሁን የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን።
ዘኁ. 15፥4-7 ቍርባኑን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ያዘጋጃል። ለአንዱም አውራ በግ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታዘጋጃለህ የኢን መስፈሪያ ሢሶም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለህ።
ዘዳ. 12፥17 የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም አሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኩራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህም ያቀረብኸውን፥ በእጅህም ያነሣኸውን ቍርባን በደጆችህ ውስጥ መብላት አትችልም።
ዘዳ. 14፥23 እና 26 ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን የወይን ጠጅህንም የዘይትህንም አሥራት የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ። በዚያም በገንዘቡ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ ወይም የወይን ጠጅ ወይም ብርቱ መጠጥ ሰውነትህም የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፥ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል።
ዘዳ. 18፥4 የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም በኵራት፥ አስቀድሞም የተሸለተውን የበግህን ጠጕር ለእርሱ ትሰጣለህ።
ይህን መስዋእት ባርኮ የሰጣቸው ራሱ እግዚአብሔር ነው።
ሆሴ. 2፥10-11 እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ፥ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ።
- በአገልግሎት ወቅት/ዘመን ግን እንዳይጠጡ ተደንግጎአል።
የወይን ጠጅ ለመስዋእትና ለስጦታ ይቅረብ እንጂ ሌዋውያን በአገልግሎታቸው ወቅት መጠጣት አልተፈቀደላቸውም።
ዘሌ. 10፥9 እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል
ሕዝ. 44፥21 ካህናቱም ሁሉ በውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ የወይን ጠጅ አይጠጡ።
ለምን ተከለከሉ? አገልጋዮች ናቸው። አገልግሎታቸው አምልኮ ነው። በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡ ሰዎች ናቸውና አእምሮአቸው መበረዝ የለበትም። በአንቂም በአደንዛዥም ንጥረ ነገር መመረዝ የለባቸውም። ይህ በተለይ ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች ትልቅ ትምህርት ነው። የአዲስ ኪዳን አማኞች በሙሉ አገልጋዮች ናቸው፤ የንጉሥ ካህናት ናቸው፤ እግዚአብሔርም እንደብሉይ ዘመን ጊዜና የመቅደስ ቦታ የሚወሰንለት ሳይሆን በመንፈስና በእውነት ሁሌና የትም የሚመለክ አምላክ ነውና አምላኪዎቹና አገልጋዮቹ ሁሌም ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ እንደተባለው ሊሆኑ የተገባ ነው።
ናዝራውያን የዚህ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ናዝራውያን በናዝራዊነት ዘመናቸው ወይንና የወይን ጠጅ፥ የወይኑን ፍሬና ዘቢቡንም አይቀምሱም።
ዘኁ. 6፥3-4 ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ ከወይን ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ። ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ።
ዘኁ. 6፥20 ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል።
ሶምሶን ከመጸነሱ ጀምሮ ናዝራዊ ነበርና ሳይወለድ ጀምሮም እናቱ እንድትጠነቀቅ ተነገራት።
መሳ. 13፥4 እና 7 አሁንም ተጠንቀቂ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ። . . . እርሱም፦ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች።
መሳ. 13፥14 ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፥ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፥ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ አለው።
ሬካባውያን ሌላ ምሳሌዎች ናቸው፤ ታሪካቸው በኤር. 35 ይገኛል።
ኤር. 35፥2 ወደ ሬካባውያን ቤት ሄደህ ተናገራቸው፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዲቱ አግባቸው የወይን ጠጅም አጠጣቸው።
ኤር. 35፥5-9 በሬካባውያንም ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አኑሬ፥ የወይኑን ጠጅ ጠጡ አልኋቸው። እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፥ የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና። እናንተና ልጆቻችሁ ለዘላለም የወይን ጠጅ አትጠጡ። በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንም አትትከሉ፥ አንዳችም አይሁንላችሁ። እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል እኛም ሚስቶቻችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም። የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም።
የአዲስ ኪዳን አማኞች/አገልጋዮች እንደ ናዝራውያንና እንደ ሬካባውያን ስለምን ራሳቸውን አይቋጥሩም? ስለምን ራሳቸውን የተለዩ አያደርጉም?
እስራኤል በምድረ በዳው ጉዞአቸው ዘመንም ወይንና የሚያሰክር አልጠጡም። ያ ጉዞ የግንኙነትና የአምልኮ ጉዞ ነበረ፤ ወልመጥማጣ ትውልድ ሆኑና በምድረ በዳ ቀሩ እንጂ የወጡትስ የካህናት መንግሥት ሆነው ሊያገለግሉት፥ ሊያመልኩት ነበረ።
ዘዳ. 29፥6 እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ እንጀራ አልበላችሁም፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክረውን መጠጥ አልጠጣችሁም።
መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱ ከወይን ጠጅና አስካሪ መጠጥ የጸዳ ነበረ።
ሉቃ. 1፥15 በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤
ናዝራውያን በናዝራዊነታቸው ዘመን፥ ሌዋውያን በአገልግሎት ዘመናቸው፥ ሬካባውያን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ፥ እስራኤል በነጻነት ጉዞአቸው ወቅት፥ መጥምቁ በዘመኑ ሁሉ መጠጥ አልጠጡም ነበር። ለእግዚአብሔር መለየት ማለት እግዚአብሔርን ማምለክና እርሱን ማገልገል ነው፤ ከእርሱ ጋር አብሮ የመሆንና የኅብረት ጊዜ ነውና አእምሮ በምንም ሌላ ገዢና ተቆጣጣሪ ስር መሆን የለበትም።
እነዚህ ያልጠጡቱ ወይም እንዳይጠጡ የተከለከሉቱ ለምን እንደተከለከሉ ስናጤን ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 14፥17 የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና ያለውን በውል መረዳት አይከብደንም።
- ወይን ጠጅ አስከፊ መልክ አለው። በርካታ ምሳሌዎችም ተዘርዝረውልናል።
ጥንት ግሪካውያን አስተማሪዎች ለተማሪዎቻቸው የአስካሪ መጠጥን አስቀያሚነት ለማሳየት ወደ ማስተማሪያ ክፍላቸው ሰክሮ የጠነበዘ ሰው አምጥተው ያሳዩአቸው ነበር። ስካር በቀላሉ አታልሎ የሚወስድ ስለመሆኑ ደግሞ እንዲህ የሚል ምሳሌም ነበራቸው፤ በመጀመሪያ ለራስህ አንድ ዋንጫ ወይን ትጋብዛለህ፤ ቀጥሎ የጠጣኸው ወይን ሌላ ዋንጫ ይጋብዝሃል፤ ከዚያም የጠጣኻቸው ዋንጫዎች አንተን ይጠጡሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ የወይን ጠጅን አስቀያሚ መልክም በግልጽ አስፍሮልናል። በበዓለ ኀምሳ ዕለት ደቀ መዛሙርት በሌሎች ቋንቋዎች ሲናገሩ ሲያደምጡአቸው፥
ሐዋ. 2፥13 ሌሎች ግን እያፌዙባቸው፥ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።
እነዚህ ሰዎች ያልሰከሩ ቢሆኑም እንኳ እያፌዙባቸው የሚለው ቃል የወይን ጠጅ የጠገቡ ሰዎች የሚፌዝባቸው የፌዝ ጊጤዎች ናቸው ማለት ነው።
1ሳሙ. 1፥14 ዔሊም፥ ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት።
ሐና አልሰከረችም ሆኖም በመምሰሏ ይህም ቃል የወይን ጠጅን ውጉዝነት ያሳያል።
ሆሴ. 4፥11 ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል።
አሞ. 12፥2 እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው ነቢያቱንም። ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ አዘዛችኋቸው።
ኢሳ. 28፥7 እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ በራእይ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ።
የእግዚአብሔር አገልጋዮች የወይን ጠጅ ሰለባ ሲሆኑ ይስታሉ፥ ያስታሉ፥ ያጠፋሉ፤ ይጠፋሉ። በአዲስ ኪዳን አገልጋይና ተገልጋይ የሚባል መደብ አለመኖሩን ማስተዋል አለብን። ሁላችንም ካህናት፥ ሁላችንም ጸጋ የተቀበልን አገልጋዮች ነን። ስለዚህ ራሳችንን ከነዚያ የብሉይ ኪዳን ሁነኛ አገልጋዮች እንደ አንዱ ብናደርግ ትክክል ነን።
ጠጥተው የሳቱና ከመስመር የወጣ ነገር ያደረጉ ወይም የተደረገባቸው በርካታ ምሳሌዎች ተሰጥተውናል። ኖኅ ጠጣ፥ ሰከረ፥ እርቃኑ ታየ። አንድ የልጅ ልጁን ለእርግማን አሳልፎ ሰጠው።
ዘፍ. 9፥ 20-21 እና 24 ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ። ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ። ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።
ሎጥ ሰከረ፤ ከሁለት ሴቶች ልጆቹ ጋር ተኛ፤ ሲተኛና ሲነሣ ወይም በመካከል የሆነውን ነገር አላወቀም።
ዘፍ. 19፥32-35 ነዪ አባታቻንንም የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር። በዚያችም ሌሊት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት ታላቂቱም ገባች፥ ከአባትዋም ጋር ተኛች እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። በነጋውም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት፦ እነሆ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ ዛሬ ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ እናጠጣው አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር። አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ አጠጡት ታናሺቱም ገብታ ከእርሱ ጋር ተኛች እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም።
አርጤክስስ ከመጠጡ በኋላ የሚስቱን ውበት ወደ አደባባይ ጠራ። ይህ ያልተለመደ ባህል ነበረ።
አስ. 1፥10-11 በሰባተኛውም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ ባለው ጊዜ፥ ንግሥቲቱ አስጢን መልከ መልካም ነበረችና ውበትዋ ለአሕዛብና ለአለቆች እንዲታይ የመንግሥቱን ዘውድ ጭነው ወደ ንጉሡ ፊት ያመጡአት ዘንድ በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርን፥ ከርከስን አዘዛቸው።
ብልጣሶር የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ሊያረክስ ደፈረ።
ዳን. 5፥ 1-2፥4 እና 23 ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቶቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ። አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ ብሎ አዘዘ። የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ። የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም።
እነዚህን ሰዎች ስናይ በአስካሪ መጠጥ ግፊት ደፋሮች ሆነው ከመስመር የወጣ ነገር ሲያደርጉና ሲሆኑ እናገኛለን። መጠጥ ድፍረት ይሰጣል። ድፍረቱ ደግሞ ለመጥፎ ግብና ዓላማ ነው። በመጠጥ ዓይን አፋሩ ዓይን አውጣ ይሆናል። ጭምቱም ፎካሪ ይሆናል፤ ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ።
ይቀጥላል