ከጥያቄዎች፤ በአዲስ ኪዳን አሥራት መስጠት ግዴታ ነው?
የጌታ ፀጋ ይብዛልህ! በአዲስ ኪዳን አስራት መክፈል ግዴታ ነው ወይ! Some teacher saying that it is the law given to old covenant era! what is your understanding regarding to this idea? Thank you for kind response? your brother in Christ Jesus muluneh!
ሙሉነህ፥ አሥራት መክፈል . . . ብለው የሚጠይቁ ሰዎችን ስሰማ ግፊታቸውን ማወቅ እፈልጋለሁ። ብዙ ጊዜ ይህን ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ለመስጠት የሚጓጉ ሳይሆኑ ከመስጠት የሚሸሹ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሲጠይቁ ለመስጠት ነው ወይስ ላለመስጠት? እቅጩን አሥራት ላይ ለማቆም ነው ወይስ ከዚያ ያነሰ ወይም ያለፈ ለመስጠት? አንዳንዶች ግን እውነቱን ማወቅ የሚሹ ናቸው። ይህኛውን እንደዚህኛው እወስዳለሁ። ግፊታችንን ማወቁ ይጠቅመናል።
ሁለት ጉልህ ቃላት ላይ ላተኩር። የመጀመሪያው ክፍያ የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ግዴታ የሚለው ነው። አስራት ክፍያ አይደለም። መክፈል ለተደረገ አገልግሎት የሚደረግ ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም የሌላ ነገር እኩያ ልዋጭ ነገር ነው። ገበያ ሄደህ የበግ ግልገል ወስደህ 500 ብር ብትከፍል ወይም በወሩ መጨረሻ ለተጠቀምክበት ውኃ ወይም ስልክ 2ሺህ ብር ብትከፍል ለተቀበልከው ነገር የሰጠኸው ልዋጭ ነው። አሥራት በአዲስ ኪዳን ይቅርና በብሉይ ኪዳንም የኪዳኑ ሰዎች የመሆን አንድ መግለጫ እንጂ የተቀበሉት በጎነት ክፍያ አይደለም። ለምሳሌ ለምንሞቀው ፀሐይ ወይም ለምንተነፍሰው አየር አሥራት በምንም መልኩ ተመጣጣኝ ዋጋ አይደለም።
ሁለተኛ ግዴታ ላልከው ከላይ እንዳልኩት በብሉይ ኪዳንም የኪዳን ትስስር ምልክት እንጂ ግዴታ አይደለም። ለዚህ ነው አሥራቱን ይከለክሉ፥ ይሰርቁ የነበረው። በአዲሱ ኪዳን ደግሞ ምንም ነገር በግዴታ አይደረግም። ግዴታ ከሆነ ፈቃድ የለበትም። እግዚአብሔር ደግሞ በፈቃዳችን ላይ የሚጫን ጨቋኝ አምላክ አይደለም።
ይህን ካልኩ በኋላ አሥራት ምን መሆኑን እንይ። አሥራት በብሉይ እና አዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፈ ቃል ነው። አሥራት (מַעֲשֵׂר ማዓሤር ወይም מַעַשׂרָה ማዓሥራህ፤ עָשַׂר ዓሣር፤ δεκάτη ዴካቴ፤ ἀποδεκατόω አፖዴካተኦ) ከአሥር አንድ፤ ከአሥር አንድ እጅ፥ አንድ አሥረኛ ማለት ነው፤ ዘፍ. 14፥20፤ ዕብ. 7፥1-9። አይሁድ የኪዳኑ ሰዎች እንደመሆናቸው ከእጃቸው ፍሬ ሁሉ አሥራትን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ በሕጉ ታዝዘዋል፤ ዘሌ. 27፥30፤ ዘዳ. 14፥22-28፤ 2ዜና. 31፥5-6፤ ነህ. 10፥37-38፤ 13፥5-12፤ አይሁድ የሚሰጡት አሥራት ለሌዋውያን እንደ ርስት ሆኖ የሚቀርብ ነው፤ ዘኁ. 18፥21-24። ሌዋውያን ራሳቸውም ከሚቀበሉት አሥራት፥ የአሥራት አሥራት የማንሣት ቁርባን አድርገው ያቀርባሉ፤ ዘኁ. 18፥26-28። ለሌዋውያን ከሚሰጠው በተጨማሪ በሦስት ዓመት አንዴ ከሌዋዊው ጋር ለመጻተኛ፥ ለድሀ አደግና ለመበለት ይሰጣሉ፤ ዘዳ. 26፥12። ነገሥታትም አሥራት ይወስዳሉ፤ 1ሳሙ. 8፥15-17። አሥራትን ለእግዚአብሔር ቤት አለመስጠት እግዚአብሔርን መስረቅ ነው፤ ሚል. 3፥8-10።
አሥራት የሕጉ ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን ከሕግም ይቀድማል፤ ዘፍ. 14፥20፤ ዕብ. 7፥1-9። በቀረቤታ ስናየው በብሉይ ኪዳን አይሁድ አሥራት ወይም አንድ አሥረኛ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በጣም ያለፈ ነበር የሚሰጡት። ሕጉ አስሰጪ ነው፤ መስጠትን ያበረታታል። ኪዳኑ ደግሞ ሰጪ ነው። ቢታዘዙ በረከት ተቋጥሮበታልና። ያ በሕግ ዘመን ነው።
በአዲስ ኪዳን ሰዎች አሥራትንም ይሰጡ ነበር፤ ማቴ. 23፥23፤ ሉቃ. 11፥42፤ 18፥12። ሰዎች አሥራትን መስጠታቸውን ጌታ አላወገዘም። ይልቅስ ያወገዘው ከጥቃቅኑም አሥራት መስጠትን እየሰጡ ትልልቁን ነገር፥ ፍርድን፥ ምሕረትን፥ ታማኝነትን፥ እግዚአብሔርን መውደድን ስለሚተዉና በዚህ ስለሚተላለፉ ያንን ነው የወቀሰው። ሕጉ የተሰጣቸው አሥራት ከሰጡ ልጁ የተሰጠን ደግሞ ምንኛ ከዚያ በላይ መስጠት አይኖርብንም? ይሁን እንጂ፥ የአዲስ ኪዳን ስጦታ መሥዋዕት ሆኖ በደስታ፥ በፈቃድ፥ እና በልግሥና የሚሰጡት ስጦታ ነው፤ ሮሜ. 12፥8፤ 2ቆሮ. 9፥6-7፤ ፊል. 4፥18፥19። ግዴታ ከኖረ ሕግ ነው፤ እኛ ደግሞ ከሕግ በታች አይደለንም። ግዴታ ከኖረ ቅሬታም ይኖራል። ግዴታ ከሆነ እንደተጠየቀው ክፍያም ይመስላል፤ ከሆነ ደግሞ እጅ በጅ ልንል ነው፤ ዱቤ አይፈቀድም ውስጥ ልንገባ ነው።
በአዲስ ኪዳን እንደ መሥዋዕት አድርገን እንድናቀርብ የተነገሩን ነገሮች አሉ፤ 1ጴጥ. 2፥5 እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። ይላል። እኛ የአዲስ ኪዳን አማኞች ሁላችንም ካህናት ነንና መሥዋዕት አቅራቢዎች ነን። የምናቀርባቸው መሥዋዕቶች እነዚህ ናቸው፤
- ሰውነታችን፤ እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። ሮሜ. 12፥1፤ 15፥15-16።
- ምስጋናችን፤ እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት። ዕብ. 13፥15።
- መልካምማድረግና ለሌሎች ማካፈላችን፤ ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና። ዕብ. 13፥16።
- ለወንጌል ሥራ የምንሰጠው ስጦታችን፥ ገንዘባችን፤ ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። ፊል. 4፥18።
- ነፍሳችንም፤ ከላይ የተዘረዘሩት ሁላችንንም የሚመለከቱ ሲሆኑ ይህ ለሁሉም አይደለም፤ ሲጠየቅ ግን ለመሠዋት ማፈግፈግ የሌለብን መሥዋዕት ነው። በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። 2ጢሞ. 4፥6። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ ፊል. 2፥17።
ከላይ ካየናቸው መሥዋዕቶች አንጻር ሲታይ አሥራት ለጌታና ለቤቱ ሥራ የምንሰጠው ትንሹ ስጦታችን ነው። የመቄዶንያ ሰዎች ከብልጽግናቸው ሳይሆን ከድህነታቸው የሰጡት የመስጠትን በረከት ስለተለማመዱ ነው፤ 2ቆሮ. 8 እና 9። መስጠት ደግሞ በረከት ብቻ ሳይሆን ብጽዕናም ነው፤ እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ፦ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ። ሐዋ. 20፥35። በአዲስ ኪዳን አሥራት በግዴታ አይከፈልም፤ በፍቅር ግን ይሰጣል።
ዘላለም።