ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያን ወጣት ደቀ መዝሙር

ዝነኝነት ወይንስ ታማኝነት?

ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴ 25፥21

“አንተ ታማኝ ባሪያ” መባል ከምንም በላይ ሊያሳስበን የሚገባበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፤ በጌታ ፊት ዋጋ የሚሰጠው ታማኝ ባሪያ መሆን እንጂ ዝነኛ አገልጋል ሆኖ መገኘት አለመሆኑን ልናስተውል ይገባል፤ ታማኝ ሆኖ መገኝትን በተለያየ መልኩ የሚያሳንሱብን፣ ይሄንን ዋና የሆነውን ጥሪ እንዳናይ የሚጋርዱን ብዙ አይነት ነገሮች በዙሪያችን ከበውናል፤ በተለይ ዘመን አመጣሹ የሶሻል ሚዲያውም ሆነ እንደ ዝነኛ (Celebrity) ወይንም ፌመስ ዘማሪ፣ ፌመስ ሰባኪ የመደነቅ ነገር ለብዙዎች እንቅፋት እየሆነ ያለንበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፤

ወደ ዝነኝነት የመጡ ሰዎች ብዙ አይነት የሕይወት መንገድ ተጉዘው ወደ ዝነኝነት ማማ ላይ መውጣት የቻሉ ናቸው፤ ይሄ ዋጋ ያስከፈላቸው ጉዞ እና አሁን ያሉበት ክብር (STATUS) በቀላሉ ሊለቁት የማይችሉት ማንነት ሆኖ ያገኙታል፤ ይሄን አይነቱ ዝነኝነት ወደ ቤተ እምነት የገባ አደገኛ የሆነ አካሄድን እየተፈጠረ እንዳለ ማየት ይቻላል፤ እነዚህ በጌታ ቤት በዝነኝነት መንፈስ ራሳቸውን ከፍ ያደረጉ፣ ከመደዴው ምእመን በላይ እንደሆኑ የሚያስቡ፤ ጌታ የሰጣቸው ጸጋ፣ ታማኝ ሊሆኑ የተጠሩለትን ጥሪ ያጎደሉ፣ ቅባታቸው ከተራው አማኝ ተርታ እንዳይመደቡ ከዛም ባለፈ መልኩ የሚቀመጡበት ወንበር የተለየ፣ የሚለብሱት ልብስ በዋጋ የተወደደ አንዳንዶቹም የሚነዱት መኪና ለኔ ቢጤው ደሃ ሲታይ የሚያስደነግጥ እየሆነ ከመጣ ሰንበትበትብሏል፤

በታዋቂነት ማንነት ማገልገል እና ለቃሉ እውነት ታማኝ ሆነን በማገልገል መካከል ያለው መስመር በጣም ስስ ነው፤ በጳውሎስ እና ባርናባስ (ሐሥ 14፥8-19) ያለውን ታሪክ ስንመለከት የሚያስተምረን ነገር አለ፤ ጳውሎስ እና ባርናባስ በበልስጥራን በእነሱ የተደረገው ተአምር ምክንያት “ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤” (ሐሥ 14:11) ይሄ የሚያሳየን ቀጣዩ ነገር እነ ጳውሎስን ለየት ያለ ስፍራ መስጠት ከዛ ባለፈ መልኩ ልዩ በሆነ መልኩ እነሱን ትንንሽ አማልክት ማድርገ ማምለክ ነበር የዚያ ከተማነዋሪዎች ፍላጎት። የጳውሎስ እና ባርናባስ ምላሽ ግን ““እናንት ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን” የሚል ነበር፤ ምክንያቱም ታማኝ ሊሆኑለት የሚገባ ጥሪ የነበራችው ሰዎች ስለነበሩ፤

ይሄን መስመር በምን ያክል እንዳለፍን አንዳንዴ በማይገባን መልኩ አልፈነው ልንገኝ እንችላለን፤ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በሰዎች ዘንድ የተለየ ዝነኝነት ያተረፉ ሰዎች እንዲያገለግሉም ሆነ በመድረኮቻቸው እንዲገኙ ሲሽቀዳድሙ መመልከት ለዚህ አይነቱ ችግር የበለጠ መባባስ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፤ “ከልካችን ያለፈ ጉርሻ መዋጥ ትንታ ያተርፋል። እግዚአብሔር በሰጠን ልክ ለክብሩ በመኖር ፈንታ የየራሳችን ትንንሽ ጣዖታት ለመሆን ባንጋጠጥን ጊዜ በድንገት መፈንገልን እናተርፋለን።” (የዱባ ጥጋብ ገጽ 118 በሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን)

ዝነኛ ሰዎች በተለየ መልኩ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ እንዲታወቅ የተለየ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ብዬ አላምንም፤ ነገር ግን በእነዚሁ ሰዎች አማካኝነት ጌታ አይሠራም ማለቴም እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፤ በጣም ጌታን የሚፈሩ በታማኝነት እርሱንና እርሱን ብቻ የሚያገለግሉ፣ በሚያገለግሉት ጌታም ሆነ የአገልግሎታቸውን በረከት ተካፋይ በሆነ አማኝ መካከል ስፍራ ያላቸው ወገኖችም እንዳሉ ማሰብ ተገቢ እንደ ሆነ አምናለሁ፤ “በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ።” (ቆላ 4፥17) ብሎ ጳውሎስ ለአክሪጳ እንዳስጠነቀቀው በዙሪያቸው የሚታየው ግርግር እና ጭብጨባ ሳይሆን ለተቀበለው አገልግሎት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያስጠነቅቀዋል፤

‘ከዚህም የተነሣ ዝናው በመላዋ ሶርያ ተሰማ፤ ‘ማቴዎስ 4:24

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት እየሆነ ከነበረው ነገር የተነሳ ለየት ያለ እውቅናን አግኝቶ ነበር፣ ከመታወቅም አልፎ እንደውም ስላበላቸው ስላጠጣቸው፤ “’ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ።” (ዮሐንስ 6:15) በዚህ የዮሐንስ ወንጌል ታሪክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው ነገር ዝናን አትርፎ ነበር ነገር ግን ከዝነኝነት የተነሳ የሚመጣ ክብር ከሚያስገኝልን ምስጋና ይልቅ ይዞብን የሚመጣው ጣጣ ብዙ መሆኑን ሊያስተምረን ስለፈለገ ራሱን ገለል አደረገ እንጂ ለማሱ (ለብዙሃኑ) ግርግር ራሱን አልሰጠም፤

ራስን እንደ ማወቅ እና ራስን እንደ መሆን ትልቅ ነገር የለም፤ ይሄ በሕይወታችን መሆን ሲችል ያን ጊዜ ለታማኝነት የቀረበ ልቦናን እናገኛለን፤ ራሳችንን መሆን የሚያስችለን ብቸኛው ነገር ለእግዚአብሔር ቃል የተጠጋ ማንነት ሲኖረን ነው፤ የቃሉ መስታወት ማንነታችንን ለራሳችን በማጋለጥ ልካችንን እንድናይ ያደርገናል እግዚአብሔርን የትኛውንም ያክል ብናውቀው ልንላመደው አንችልም ለዚህ ነው ራስን ማወቅ ልክን ማወቅ ነው። ጌታ ጌታ  ነው እኛ እኛ ነን፤ ጴጥሮስ ከጌታ ኢየሱስ ትንሳኤ በኋላ ስለ ራሱ ያለው እይታ ለየት ያለ መሆን ችሎ ነበር፤ በፊት ፈጠን ፈጠን ይል የነበረው አሁን ግን “…..ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድድህም ታውቃለህ” አለው።” ወደሚለው ራስን ወደማወቅ መጣ፤ (ዮሐ 21፥17)

የተቀበልነው አደራ ተጠያቂነት ያለበት ስለሆነ ታማኝነት ግድ ይላል፤ ልባም ባሪያ ሆነን ስንገኝ የተሰጠንን አደራ ለተደራሹ እንደሚገባ ተጠንቅቀን እናደርሳለን፤ ለዚህ አይነቱ ባሪያ ትልቁ ትኩረት ተደራሹ አይደለም አደራ የሰጠው ነው ትልቅ ስፍራ ያለው!! “’ጌታም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማነው? ‘ሉቃስ 12:42

የተቀበልነው አደራ ራሳችንን ልናሳይበት ሳይሆን ልንጠነቀቅለት፣ ራሳችንን እኛነታችንን ዝቅ ልናደርግለት፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በምድረበዳ የምንጮህ ድምጽ የምንሆንለት እንጂ የምንታይ ዝነኞች እንዳልሆንን ሊገባን በዚህ መልኩ ራሳችንን ልናውቅ ይገባል፤

‘እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል። ‘ዮሐንስ 3:30

 

About the author

Tebebe Mekonnen

ወንድም ጥበበ ባለትዳር እና የልጆች አባት ነው፤ ጌታን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ እየተከተለ ያለ፣ ባለበት ሕብረት ጌታን የሚያመልክ እና የሚያገለግል የጌታ ደቀ መዝሙር የሆነ ወንድም ነው፤