አጭሩና እቅጩ መልስ ፈጽሞ አይቻልም የሚል ነው።
በመጀመሪያ መላእክት ፍጡራን መሆናቸውን እንወቅ። መጠንቀቅ ያለብን አጋንንትም በፍጥረታቸው መላእክት መሆናቸውን ነው። ከመላእክት ሰይጣንን በዓመጽ ተከትለው የወደቁ አጋንንት ናቸው። መልአክ የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን መልእክተኛ የተላከ ማለት ነው። የአዲስ ኪዳኑ መጠሪያቸውም ይህንን የተላኩ መሆንን የሚያሳይ ነው። የሚላኩ ይሁኑ እንጂ ሰዎች የሚልኳቸው ሳይሆኑ እግዚአብሔር የሚልካቸው ፍጡራን ናቸው። ስማቸው የሚያሳየውን ፍጥረታቸውን ሳይሆን ይህንን አገልግሎታቸውን ነው።
መላእክት ሥራቸው ብዙ ዓይነት ነው። በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ የደኅንነትም የቅጣትና የበቀልም ስፊ የሆነ ድርሻ ነበራቸው። ዘጸ. 12፥23፤ ማር. 13፥32፤ 1ቆሮ. 10፥10፤ 2ሳሙ 24፥16። በብሉይ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሱት በአብርሃም ታሪክ ነው። ከአብርሃም በኋላ ብዙ ጊዜ ደጋግመው ሲገለጡና የተለያዩ ሥራዎችን ሲፈጽሙ ይገኛሉ። ለጌዴዎን፥ ለሰምሶን ወላጆች፥ ለነቢያትም ለኤልያስ፥ ለዳንኤል፥ ለሌሎችም ተገልጠዋል። መላእክት በዚህ ዘመን አማኞችን ያገልግላሉ፤ ንስሃ በሚገባ ኃጢአተኛ ይደስታሉ፤ ዕብ. 1፥14፤ መዝ. 34፥7፤ እና 91፥11፤ ማቴ. 18፥10፤ ሐዋ. 5፥19፤ 8፥26፤ 10፥3፤ 12፥7፤ እና 27፥23። በሚመጣውም ዘመን የፍርድ አገልጋዮች ይሆናሉ፤ ማቴ 13፥39-39-49፤ 16፥27 እና 24፥31። በመጽሐፍ ቅዱስ በሱም የተጠቀሱ መላእክት ሁለት ብቻ ናቸው፤ እነርሱም፥ ሚካኤል እና ገብርኤል ናቸው። መላእክት የማይሞቱ ፍጡራን ናቸው። ሉቃ. 20፥36፤ ከሰብዓዊ ችሉታ በላይ የሆነ እውቀትና ኃይልም አላቸው። ማር. 13፥32፤ 2ተሰ 1፥7፤ መዝ. 103፥20። ሆኖም ሁሉን የሚያውቁ ሁሉን የሚችሉና በሁሉ ቦታ የሚገኙም ሳይሆኑ ውስኖች ናቸው። ሊመለኩም ከቶ አይገባም፤ ቆላ. 2፥18፤ ራእ. 19፥10።
መላእክት ከሰዎች ጋር ኖሮአቸው በሚያውቀው በመጽሐፍ ቅዱስ በተጻፉልን ታሪኮች ውስጥ ሰዎች መላእክትን ሲያነጋግሩ፥ መልእክትን ሲቀበሉ፥ መላእክት የታዘዙትን ሲፈጽሙ ሲመለከቱ ወይም የተነገራቸውን ሲያደርጉ እንጂ ሲያዝዙና ተግባር ሲያስፈጽሙ ከቶም አልተጻፈም። መላእክትን እግዚአብሔር ቅዱሳንን እንዲያገለግሉ እንዲልካቸው በቃሉ ተጽፎአል፤ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ መዝ. 91፥11። ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን? ዕብ. 1፥14። ቅዱሳንን ያገልግሉ እንጂ ቅዱሳንን ያገለግሉ ዘንድ የታዘዙት ከእግዚአብሔር ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ስፍራ ሰዎች መላእክትን በራሳቸው ወይም በእግዚአብሔር ስም ሲልኳቸው፥ ሥራ ሲያሰሯቸው፥ ሲያዝዟቸው አልተጻፈም። እግዚአብሔር በዘመናት ውስጥ ያላደረገውን አዲስ ነገር በኛ ዘመን ያደርጋል የሚሉ ሰዎች ሲነሡ እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስቲያኖች ማስተዋል አለብን። መላእክት ተገልጠው ያደረጉትን ባደረጉባቸው ቦታዎች ሁሉ እግዚአብሔር ልኳቸው እንጂ ሰዎች ጠርተዋቸው አልመጡም።