ማሕበረሰብ ክርስቲያን ወጣት

ስኬታማ ክርስቲያን መጣት


  • የወጣትነት ዕድሜ በብዙ ዕድሎችና ተግዳሮቶች የተከበበ ነው፡፡
    • ራሳችንንም ሆነ በዙርያችን የሚገኙትን ነገሮች ለመለወጥ በቂ ጊዜ አለን፡፡
    • ማድረግ የምንፈልገውን ሁሉ ለማረግና መሆን የምንፈልገውን ሁሉ ለመሆን በቂ አቅም አለን፡፡
    • የሕይወትን ልምድ ለመቅሰምና ለመማር ትክክለኛው ዕድሜ ነው፡፡
    • ወጣትነታችንን የሚፈልጉ እግዚአብሔራዊ ያልሆኑ ኃይላት መኖራቸው ደግሞ የወጣትነትን ዕድሜ ከባድ ያደርገዋል፡፡
  • ወጣትነት ሕይወታችንን አቅጣጫ ለማስያዝ በጣም ወሳኝ ዕድሜ ነው፡፡
  • ሕይወታችን ሁለንተናችን በመሆኑ ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ ለኑሮአችን የሚያስፈልጉን ነገሮች ተገቢውን ትኩረት ማግኘት ይገባቸዋል፡፡

በወጣትነት ዘመን ስኬታማ ለመሆን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አሉ፡-

1. ጊዜ

ወጣትነትን ተመራጭ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ ጊዜ ነው፡፡

ከወጣትነት የጊዜ ክልል ውጪ የማይገኙ ብዙ ነገሮች አሉ፡- ጉልበት፣ ውበት፣ ንቃት፣ ዕውቀትን የመሰብሰብ አቅም፣ ወዘተ.

ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም

  • ጊዜ በእግዚአብሔር ከተፈጠሩ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ በጊዜ ውስጥ ነው የፈጠረው፡፡
  • ጊዜ አንዴ ከባከነ ተመልሶ አይገኝም፡፡ በጊዜ ውስጥ በደፊትም ወደ ኋላም መሄድ አይቻልም (በሐሳብ ካልሆነ በስተቀር)፡፡ ጊዜ ይመጣል ያልፋል፡፡
  • በምድር ላይ የምንኖረው የእድሜ ዘመን የተለያየ ርዝማኔ ቢኖረውም ነገር ግን ለሁሉም ሰው እኩል የሆነ የ 24 ሰዓት ጊዜ ነው የተሰጠው፡፡
  • ስኬታማ ሰዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም የቻሉ ሰዎች ናቸው፡፡
  • ረጅም ዕድሜ ኖረው ለመታሰብያነት የሚበቃ ምንም ነገር ሳይሠሩ ያለፉ በርካታ ሰዎች አሉ፤ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ዓለምን በበጎ የለወጡ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ ኢየሱስ አንዱ ነው፡፡
  • ጊዜ በጣም ውድ ነገር ነው፤ ነገር ግን የጊዜን ዋጋ በትክክል የምንገነዘበው በጊዜ የመጠቀም ዕድላችን ሲያከትም ነው፡፡
  • ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም መጀመርያ የጊዜን ዋጋ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡
  • በምድር ላይ ያለን ጊዜ በልባችን ውስጥ ያለውን መሻት ሁሉ ከግብ ለማድረስ በቂ አይደለም፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለመዘጋጀት በቂ ነው፡፡
  • በምድር ላይ ያለንን ዘመን በትክክል መኖር አለመኖራችን በዘላለማዊው ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ይናገራል፡-

  • የእዚአብሔር ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ተናገረ፡- “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና።” መዝሙር 90፡10፡፡ እድሜያችን በገፋ ቁጥር ያለፉት ጊዜያት ትዝታዎች ብቻ ይሆናሉ፡፡ አንድ ቀን ደግሞ የተወሰነልንን ዘመን ጨርሰን ወደ ዘላለም መኖርያችን እንሰበሰባለን፡፡
  • ጊዜ በጣም ወሳኝ በመሆኑ ምክንያት በትክክል ልንጠቀመው እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይናገረናል፡፡
  • ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች እንዲህ በማለት ጻፈ፡- ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።” ኤፌሶን 5፡16
  • ጥበበኛው ሰለሞን በመክብብ 3፡1-8 ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል፡- ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፡፡ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፡፡ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፡፡ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፡፡ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፡፡ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፡፡ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፡፡ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፡፡ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፡፡ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፡፡ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፡፡ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፡፡ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፡፡ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው።”
  • ያለ ጊዜ የሚሆን ነገር የለም፤ ነገሮችንም በጊዜያቸው ማድረግ ያስፈልጋል፤ በአብዛኛው ሁኔታ ሰዎች በምርጫቸው በጊዜያቸው ላይ እንዲወስኑ እግዚአብሔር አቅምና ፈቃድን ሰጥቷቸዋልና፡፡
  • ንጉስ ዳዊት የተወለደው በጣም ኋላ ቀር በነበረችው የቤተልሔም ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን እስራኤልን ከውድቀት ዘመን ወደ ብልፅግና ዘመን ማምጣት የቻለ ታላቅ ንጉሥ ሆነ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ 900 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ በብዛት በመጠቀስ ከ1000 ጊዜ በላይ ከተጠቀሰው የኢየሱስ ሥም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የስኬቱ ምስጢር የዕድሜ ዘመኑ አጭር መሆኑን በመገንዘብ የተሰጠውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀሙ ነበር፡፡ “አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ።” መዝሙር 39፡4
    • ዳዊት ክልጅነቱ ጀምሮ ነገሮችን በትክክለኛ ጊዜያቸው ያደርግ የነበረ ሰው ነበር፡፡
    • እረኛ መሆን በሚገባ ዘመን ጥሩ እረኛ ነበር፡፡ ከእረኛ መሣርያዎች መካከል አንዱ ወንጭፍ ስለነበር ድንጋይን በማወናጨፍ የተካነ እረኛ ነበር፡፡
    • የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ በሳሙኤል ቢቀባም “ተቀብቻለሁ ንጉሥ ልሁን” ብሎ ከመጣደፍ ይልቅ ወደ እረኝነት ቦታው ተመልሶ በጎቹን መጠበቅ ቀጠለ፡፡
    • ጎልያድ ሕዝቡን ሲገዳደር በትክክለኛው ሰዓት ደረሰ፡፡ የእረኝነት ዘመኑን ተጠቅሞ ከጥሩ እረኛ እንደሚጠበቀው ጥሩ ወንድጭፈኛ ባይሆን ኖሮ ጎልያድን መጣል ባልቻለም ነበር፡፡
    • ጎልያድን ከጣለ በኋላም ቢሆን የእስራኤል ልብ እርሱን ቢከተልም አሁንም ንግሥናውን ከማወጅ ይልቅ ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ፡፡
    • የሳዖል የጦር ጀነራል መሆን በሚገባው ዘመን ለሳዖል በመታዘዝ አገለገለ፣ መሰደድ በሚገባው ዘመን ተሰደደ፣ ትክክለኛ ጊዜውን ጠብቆ ነገሠ፣ እስራኤልን ሃያል አገር አደረጋት፡፡
    • ዳዊት በዘመኑ ከባባድ ስህተቶችን የሠራው ሁለት ጊዜ ነው፤ አንዱ ሕዝቡን ማስቆጠሩ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከቤርሳቤህ ጋር በምንዝርና መውደቁ ነው፡፡
      • እንዲህም ሆነ፤ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ሰደደ። የአሞንም ልጆች አገር አጠፉ፥ ረባትንም ከበቡ፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። (2ሳሙ. 11፡1)
    • በሰልፍ ሰዓት ለመዝናናት በከተማ በመቅረቱ ሳብያ ራሱን ለፈተና አጋለጠ፡፡
    • ዳዊት በተሰጠው ዘመን እግዚአብሔርን እንዳገለገለ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ” ሐዋ. 13፡36
    • ጊዜን ማወቅ፣ በጊዜው መሆን የሚገባንን መሆንና ማድረግ የሚገባንን ማድረግ፣ ጊዜያችንን ሳናባክን በትክክል መጠቀም ኋላ ከመፀፀትና ያለፈው ዘመናችንን ዕዳ ከማወራረድ ይታደገናል፡፡

2. ትክክለኛ ጓደኛ መምረጥ

  • መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ጓደኛ ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራል፡- ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም።” መክብብ4፡9-12
  • አብሮን የሚውልና የልባችንን ምስጢር የምናዋየው ሰው በሕይወታችን ላይ በጎ ወይንም መጥፎ ተፅዕኖ የማሳረፍ አቅም አለው፡፡ “ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።” ምሳሌ 27፡17
  • “ከማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚለው አባባል ትክክል ነው፡፡ መጥፎ ጓደኝነት ስብዕናችንን ያጎድፋል፡፡ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” 1ቆሮንቶስ 15፡33 ይህንን አባባል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ታይስ” በሚል ርዕስ “ሜናንደር” በተባለ ግሪካዊ ባለቅኔ ከተጻፈ ተውኔት ላይ ነው የወሰደው፡፡ የቆሮንቶስ ሰዎች የሚያውቁትንና የባሕላቸው አካል የሆነውን ዘይቤ ቢጠቀም ይበልጥ ሊገባቸው ስለሚችል ነው ይህንን ያደረገው፡፡
  • ከመጥፎ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደሚያጠፋን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋት አትሂድ፥ መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ።” ምሳሌ 22፡24-25
  • የዳዊት ልጅ አምኖን የገዛ እህቱን ትዕማርን በወደደ ጊዜ ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ምክርን ፍለጋ የሄደው ኢዮናዳብ ወደተባለ መጥፎ ወዳጁ ነበር፡፡ ከማን ምክርን መስማት እንደሚገባው ባለማወቁ የተነሳ ፍጻሜው ሞት ሆነ፡፡ 2ሳሙኤል 13
  • ንጉሡ ሮብአም ሕዝቡን ማስተዳደር ይችል ዘንድ ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ባለመስማቱ የተነሳ የእስራኤልን ሕዝብ ለሁለት ከፈለ፡- እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። እርሱም፦ አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።” 1ነገሥት 12፡8-11
  • መጽሐፍ ቅዱስ ጓደኛ ማብዛት ጉዳት እንዳለው እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።” ምሳሌ 18፡24
  • አንድን ሰው ልንለውጠው እንደምንችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ካልሆንን ወደጅነታችንን በልክ ማድረግ አለብን፡፡

3. ያለንን ነገር ማወቅና በትክክል መጠቀም

  • ያለንን ነገር ለይተን ማወቅና በትክክል መጠቀም ለስኬታማ ሕይወት ወሳኝ ነው፡፡ (የጸጋ ስጦታዎች፣ የተፈጥሮ ተሰጥዖ፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁሶች፣ ወዘተ.)፡፡
  • የተሰጠንን መክሊት ዋጋ ተረድተን ካልነገድንበትና ካላተረፍንበት የመክሊቱ ባለቤት ሲመጣ ተጠያቂዎች እንሆናለን ፡፡
    • ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፦ ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። (ማቴ. 25፡15-29)

3. በሁኔታዎች ተስፋ አለመቁረጥ፡፡

  • በወጣትነት ዘመን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች ድል ለመንሳት ተስፋ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
  • ተስፋ የሕይወት መብራት ነው፡፡ በጨለመብን ቀን ማዶ ያለውን ነገር አሻግረን የምናየው በተስፋ ነው፡፡
  • ክርስቲያን ተስፋ ቢስ አይደለም፡፡ ከሁሉ በላይ የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ አለን፡፡ በምድርም ላይም በምንም ሁኔታ ውስጥ ጌታ ከኛ ጋር ሊሆን ተስፋን ሰጥቶናል፡፡

4. በእግዚአብሔር ዓላማ የተፈጠርንና የምንኖር መሆናችንን ማወቅ

  • የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን መጠን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ የምንኖር እንጂ በእድልና አጋጣሚ የምኖር ሰዎች አይደለንም፡፡ ስለዚህ በምናልፍበት የሕይወት ጎዳና ሁሉ እግዚአብሔር ዓላማ እንዳለው በማመን መኖር የስፈልገናል፡፡
  • ዮሴፍ ወደ ግብፅ ለሸጡት ወንድሞቹ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡- “ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው፦ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና። ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ።” ዘፍጥረት 45፡1-8
  • የተወለድንበትን አገር፣ ከተማ፣ ቤተሰብና ዘር የመረጠልን ራሱ እግዚአብሔር በመሆኑ ለእርሱ ክብር ልንኖርና በእርሱ ልንታመን ይገባናል፡፡

5. በሁሉም ቦታና ሁኔታ የእግዚአብሔር ሰዎች ሆነን መገኘት

  • ናቡከደነፆር ዳንኤልና ጓደኞቹን ወደ ባቢሎን ምድር ከወሰዳቸው በኋላ ለ3 ዓመታት ያህል የከለዳውያንን ትምሕርት ይማሩ ዘንድ ወደ ማሰልጠኛ ካምፕ አገባቸው፡፡
  • ባቢሎናውያን እነዚህ ወጣቶች የድሮ ማንነታቸው ይዘው ከቀጠሉ በትክክል እንደማያገለግሏቸው ስላሰቡ በተለያዩ ስልቶች የቀድሞ ማንነታቸውን ሊያስጥሏቸው ብዙ ጥረት አደረጉ፡፡
  • ቋንቋቸው፣ አስተሳሰባቸው፣ ባሕላቸው፣ ሃይማኖታቸውና ኑሯቸው ሁሉ ባቢሎናዊ ይሆን ዘንድ የወሰዱት የመጀመርያው እርምጃ አገራቸውንና አምላካቸውን የሚያስታውሷቸውን ስሞቻቸውን መቀየር ነበር፡፡
  • እነዚህ ወጣቶች በባዕድ ምድር የሚኖሩ ሆነው ሳሉ በብዙ ተፅዕኖ ውስጥ እያለፉ ዳሩ ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን የሚያስከብር የውሳኔ ሕይወት ኖረው አለፉ፡፡
  • ለጣዖት ተሠውቶ የሚመጣውን ሥጋ ከመብላትና የወይንጠጅ ከመጠጣት ይልቅ ጥራጥሬን መብላት መረጡ፡፡
  • የዘበኞቹ ዓለቃ 10 ቀን ፈተናቸው፤ በመልክና በጤንነት ከሌሎች 10 እጥፍ በልጠው ተገኙ፡፡
  • ዳንኤል ቀናተኞች በተነሱበት ጊዜ የጸሎት ስፍራውን ላለመልቀቅ ወሰነ፤ ወደ አናብስት ጉድጓድ ቢጣልም አምላኩ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ የአናብስቱን አፍ ዘጋ፤ ዳንኤልም ወደ ተሻለ ክብር ተሸጋገረ፡፡
  • ሐናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ለጣዖት ይሰግዱ ዘንድ አስገዳጅ ትዕዛዝ በተሰጣቸው ጊዜ ላለመስገድ ወሰኑ፤ በእሳት ውስጥ ቢጣሉም ያለ ምንም ጉዳት ከእሳቱ ተረፉ፡፡

እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ለክብሩ የሚኖሩ፣ ከዓለም ክፋት ራሳቸውን የለዩ፣ እርሱን የሚፈሩ፣ ቆራጥ ወጣቶችን ይሻል፡፡

About the author

Dan

ወንድም ዳንኤል በነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሲሆን የበርካታ መጻሕፍት ተርጓሚ፣ አርታዒና ደራሲ ነው።