ክርስቲያን ወጣት

የድህረ ስልጣኔ ፍልስፍና

በምዕራባውያን የታሪክ ዘመን አከፋፈል መሰረት እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የሚገኘው ዘመን ቅድመ ስልጣኔ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከ1600-1950 የሚገኘው የታሪክ ዘመን የስልጣኔ ዘመን (Modernism) በመባል ይታወቃል፡፡ ከ1950 ወዲህ ያለው ዘመን ደግሞ ድህረ ስልጣኔ (Post modernism) በመባል ይታወቃል፡፡

ድህረ ስልጣኔ ፍፁም የሆነ እውነት የለም በማለት የሚያስተምር ፍልስፍና ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን መኖር የሚክደው ንፅረተ ዓለም አካል ሲሆን ፍልስፍናው በክርስትናም ሆነ በሌሎች ንፅረተ ዓለማት ውስጥ በመግባት  ሊሰርፅ ይችላል፡፡ የድህረ ስልጣኔ አቀንቃኞች ነባር የሆኑ እምነቶችንንና አስተሳሰቦችን እንዲሁም እሴቶችን ይክዳሉ፡፡  ሁሉም አመለካከቶች እኩል በሆነ ሁኔታ ትክክል ናቸው በማለትም ያምናሉ፡፡

የድህረ ስልጣኔ አስተሳሰብ መሰረት የተጣለው ዘመነ አብርሆት ወይም ኢንላይትመንት በመባል በሚታወቀው ዘመን ሲሆን ይህ እንቅስቃሴ እግዚአብሔርና ሃይማኖት አያስፈልጉንም በሚሉ ፈላስፎች የተመራ የፍልስፍና መነቃቃት ዘመን ነበር፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ውጤቶች የሆኑ አስተሳሰቦች የድህረ ስልጣኔ ፍልስፍና መሰረቶች ሲሆኑ ዛሬ ምዕራባውያን ለሚገኙበት የግብረ ገብነት ዝቅጠት ምክንያት እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዘመነ አብርሆት መሰረት የተጣለላቸው የድህረ ስልጣኔ አስተሳሰቦች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ጠቃሚዎች ቢመስሉም ነገር ግን እውነት አንፃራዊ እንደሆነች የሚያናገረው የድህረ ስልጣኔ ፍልስፍና ሲታከልባቸው አደገኛ ውጤት ያስከትላሉ፡፡

  1. ምክንያታዊነት (Reasoning) – የዘመነ አብርሆት ፈላስፎች እግዚአብሔርም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንደማያስፈልጉና ሰዎች በምክንያታዊነት ብቻ በመመራት ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ አስተምረዋል፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን መኖር በመካድ የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣን እንዲያቃልሉ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
  2. ተስፈኛነት (Hopefullness) – ከዘመነ አብርሆት ወዲህ ሰዎች ተስፈኞች ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ተስፋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አድጎ የተሻለ የደስታ ህይወት መምራትን በመመኘት የተፈጠረ ተስፋ እንጂ በፈጣሪያቸው ላይ የተመሰረተ ተስፋ አይደለም፡፡
  3. ግላዊነት (Individualism) – ዛሬ በምዕራብ አገራት ውስጥ የተንሰራፋ አስከፊ ባሕል ቢኖር ግላዊነት ነው፡፡ ሰዎች በራሳቸው ላይ የሚያተኩሩ እና ለሌላው ግድ የሌላቸው ሆነዋል፡፡ የመሰላቸውን ማድረግ እና መናገር መብታቸው እንደሆነ በማመን ግብረ ገብነትን አንፃራዊ አድርገዋል፡፡ ይህም የዘመነ አብርሆት አንዱ ውጤት ነው፡፡ ግለኝነት ሰዎችን በየራሳቸው አጥር ውስጥ የሚያስቀምጥ አስተሳሰብ ነው፡፡ አንድ ሰው ስህተት መሆኑን ብታውቁም እንኳ ስህተት መሆኑን ልትነግሩት አትችሉም፡፡ ያንን ማድረግ የሰዎችን መብት ከመጋፋት እና ከትዕቢት ይቆጠራል፡፡
  • ክርስትና የግልም የጋራም የሆኑ ገጽታዎች አሉት፡፡ ውስጣዊው የክርስትና ሕይወታችን በኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ጉዳይ ቢሆንም እግዚአብሔርን የምናመልከው እና የምናገለግለው ግን በጋራ ነው፡፡ “Ecclesia” የሚለው የግሪክ ቃል “ተጠርተው ለአንድ ዓላማ የወጡ” የሚል ትርጉም ለው፡፡ በሕብረት ለአንድ ዓላማ መሰለፍን የሚያመለክት ነው፡፡
  • አንድ ሰው ብቻውን ቤተ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ስብስብ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወም አስተምህሮ ምንጩ ከአጋንንት ነው፡፡
  1. ፍጆታዊነት (Consumerism) – ይህ አስተሳሰብ ሰዎች ባላቸው ነገር ላይ ሌላ ነገር በጨመሩ ቁጥር ደስታና እርካታቸውን ከፍ እንደሚያደርጉ ያስተምራል፡፡ ነገር ግን ፍላጎታችን ገደብ ስለሌለው ባለን ነገር ላይ በጨመርን ቁጥር ባዶነታችን እየሰፋ ይሄዳል እንጂ ደስታና እርካታን ልናገኝ አንችልም፡፡ አላቂ የሆኑ ነገሮችን አንድ ላይ ብንደምር ትልቅ አላቂ የሆነ ነገር እናገኛለን እንጂ አላቂ ያልሆነ ነገር አናገኝም፡፡ እውነተኛ እርካታን ልናገኝ የምንችለው የሁሉ ነገር አልፋና ኦሜጋ በሆነው በአምላካችን ብቻ ነው፡፡
  2. ለዘብተኝነት (Libralism) – ሰዎች ነባር እውነቶችን በማጣጣል እውነታዎችን በዘፈቀደ እንዲተረጉሙ የሚያደርግ አስተሳሰብ ሲሆን ገደቦችን ሁሉ የሚጥስ ፍልስፍና ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በምዕራባውያን አገራት ውስጥ በወንድና በሴት መካከል ያለው ልዩነት ትርጉም እያጣ ይገኛል፡፡ ለዘብተኝነት በክርስቲያናዊ ሥነ መለኮት ላይም የጎላ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ በዚህም ምክንያት የለዘብተኛ ሥነ መለኮት አቀንቃኞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙ ትምህርቶች እና ታሪኮች የራሳቸውን አማራጭ ትንታኔዎች በማዘጋጀት የክርስትናን መሰረቶች ለማናጋት በትጋት ሲሰሩ ኖረዋል፡፡
  3. ቁሳዊነት (Materialism) – ቁሳዊነት ከፍጆታዊነት ጋር የሚመሳሰል ሲሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ በማለት በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ እንድናተኩር የሚያደርግ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ የድህረ ስልጣኔ ውጤት የሆነው አስተሳሰብ ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናትን እየገደለ የሚገኝ አስተሳሰብ ነው፡፡

ዛሬ በብዙ አገራት በቁጥር እየጨመሩ የሚገኙት የብልጽግና ወንጌል በመባል የሚታወቀውን መስመር የሳተ ትምህርት የሚያስተምሩ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባኪዎች ክርስቶስን ሳይሆን ገንዘብን ይሰብካሉ፡፡ ክርስቲያን የመሆን ዓላማ እና ክርስቶስን የመከተል ግቡ በምድር ላይ በብልፅግና መኖር እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን አይልም፡፡ ምድራዊው በረከት በሰማይ የምናገኘው በረከት ምርቃት እንጂ ዋና ስጦታ አይደለም፡፡ “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” 1ቆሮ 15፡19

ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴ 24፡26-34

ቁሳዊነት ዛሬ በምንገነባቸው የአምልኮ ሕንጻዎችም ይንጸባረቃል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው አብተ ክርስቲያናት ለወንጌል ስርጭት የሚመድቡት ዓመታዊ በጀታቸው ከ 1% ያነሰ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ግን “ሂዱና ሕንጻ ስሩ” አላለንም፡፡ ሕንጻ መስራት አስፈላጊ ቢሆንም ሰው መስራት ግን ይቀድማል፡፡

  1. ዓለማዊነት (Secularism) – ይህ አስተሳሰብ እግዚአብሔር እና መንፈሳዊ የሆኑ አስተሳሰቦች ከሕዝብ አደባባዮች መወገድ አለባቸው የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በምዕራባውያን አገራት የሚገኙ መንግሥታት የክርስትናን እሴቶች የሚገልፁ ነገሮችን ከመንግሥት መስርያ ቤቶች እና ከትምህርት መጽሐፍት ውስጥ እያስወገዱ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ከትምህርት በፊት የሚደረጉ ፀሎቶች እና የአሥርቱ ትዕዛዛት ትምህርቶች እንዲቀሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአገራችን አውድ ስንመለከት በእርግጥ እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ኃይማኖት ወደ መንግስት መስሪያቤቶች እና ወደ ሕዝባዊ አደባባዮች ላምጣ ቢል ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ነገር ግን ገላቲያ 5፡22 ላይ የሚገኙትን መልካም ባህርያት የሚከለክል የመንግሥት ህግ የለም፡፡ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።” ስለዚህ በባሕርያችን እና በኑሯችን ክርስቶስን “Secular” ወደ ሆኑ ወደነዚህ ቦታዎች ልናመጣው እንችላለን፡፡ በየመስሪያቤቱ ተለጥፈው የምናያቸው የመልካም ስነ ምግባር መርሆች አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው፡፡ “ታማኝነት፣ ሃቀኝነት፣ ቅንነት…”

  1. ዓለማዊ ሰብዓዊነት (Secular Humanism) – ይህ ፍልስፍና ሰው በዩኒቨርስ ውስጥ ትልቁ ማንነት እንደሆነ ያስተምራል፡፡ በሌላ አባባል ከሰው በላይ የሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ የእግዚአብሔርን መኖር በመካድ ሰውን አምላክ የሚያደርግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ በዓለማዊ ሰውነት መሰረት፡-
  • ኃጢኣ የሚባል ነገር የለም፡፡
  • እውነት አንጻራዊ ናት፡፡
  • ሰው በተፈጥሮው ጥሩ ነው፡፡
  • ኢየሱስ ሰው ብቻ ነው፡፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም፡፡ የሰው ፈጠራ ነው፡፡ ለግብረ ገብነት የመመርያ ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ግን ከሁሉ በላይ የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ እና የሕይወት ምንጭ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪያችን ስለሆነ ሊመለክ ይገባዋል፡፡

  • ሰይጣን አዳምና ሔዋን ከገነት እንዲባረሩ ያደረገው እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ የሚል የሐሰት ተስፋ በመስጠት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው እንደ አምላክ መሆን ይችላል የሚለው የ Secular Humanism አስተሳሰብ ምንጩ ከሰይጣን ነው፡፡
  • እግዚአብሔር ሰውን መልካም አድርጎ በራሱ አምሳል የፈጠረው ቢሆንም ሰው ግን ነጻ ፍቃዱን ተጠቅሞ በኃጢኣት ወድቋል፡፡ ስለዚህ እንዳንዱ ሰው ኃጢኣትን ከማድረግ ዝንባሌ ጋር ይወለዳል፡፡
  • ፍጹም የሆነ እውነት አለ፡፡
  • ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡
  • መጽፍ ቅዱስ በሰው ታሪክ ቋንቋ እና ባሕል ውስጥ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ለሕይወታችን ትክክለኛ መመርያ ነው፡፡ ትዕዛዛቱ ፍጹምና ቅዱስ ናቸው፡፡
  1. ሉላዊነት (Globalization) – Globalization (ሉላዊነት) የእግዚአብሔር የመጀመርያም የመጨረሻም ሐሳብ ነው፡፡ “በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” ኤፌ 1፡10
  • ነገር ግን ሰዋዊ Globalization እግዚአብሔርን የሚቃወም አስተሳሰብ ነው፡፡
  • ሰዋዊ Globalization በድሕረ ስልጣኔ አስተሳሰብ የሚመራ እግዚአብሔርን ከሰው ታሪክ ውጪ የማድረግ ሩጫ ነው፡፡
  • የሰዋዊ Globalization ሐሳብ አሁን የተጀመረ አይደለም

“ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች። ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ በዚያም ተቀመጡ። እርስ በርሳቸውም፦ ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው የምድርም ዝፋት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው። እንዲህም፦ ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ። እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው ይህንም ለማድረግ ጀመሩ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም። ኑ፥ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው። እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው ከተማይቱንም መሥራት ተዉ። ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል።” ዘፍ 11፡1-9

እግዚአብሔር ሰዋዊ ሉላዊነትን ይቃወማል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ስርኣት ለመፍጠር የሚደረጉ የሰው ልጆች ሩጫዎችንም ሲያከሽፍ እንመለከታለን፡፡ ታላላቅ ኢምፓየሮችን በመፍጠር ዓለምን ሁሉ እንገዛለን በማለት የተነሱት ግዛተ መንግሥታት በእግዚአብሔር በራሱ ጣልቃ ገብነት እንደፈራረሱ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታሪክ ምስክር ናቸው፡፡ ለምሳሌ ናምሩድ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ፋርስ፣ ሮም፣ አረቦች፣ ኮሚኒዝም፣ ወዘተ.

  1. መቻቻል (Tolerance) – መቻቻል መልካም ቢሆንም ነገር ግን “እውነት አንጻራዊ ናት” የሚለው አስተሳሰብ ከታከለበት አደገኛ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡ ዛሬ በመቻቻል ስም ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ የሚቃወማቸውን ልምምዶች እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነትን አጥብቆ ይቃወማል፡፡

ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ጸያፍ ነገር ነውና። ዘሌ 18፡22

ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል ፈጽመው ይገደሉ ደማቸው በላያቸው ነው። ዘሌ 20፡13

ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 1ቆሮ 6፡9-10 እንዲሁም ሮሜ 1፡26-28

በምዕራባውያን አገራት ውስጥ አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊነትን ከተቃወመ “Homophobe” የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ በመቻቻል የማያምን ሰው እንደሆነም ይቆጠራል፣ ይገለላል፡፡

እኛ የምናመልከው አምላክ ሙስሊሞች፣ ሂንዱዎች፣ ቡዲህስቶች፣ ወዘተ. ከሚያመልኩት አምላክ የተለየ ነው፡፡ ስለዚህ ከሙስሊሞች ጋር አንድ ላይ መጸለይ አንችልም፡፡ ብዙ ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት ግን ከሙስሊሞች ጋር የጋራ የጸሎት ጊዜያትን በማዘጋጀት በሙስሊም ኢማሞች እየተመሩ ይጸልያሉ፡፡ ሙስሊም ሰባኪያንን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመጋበዝ እንዲ ሰብኩ ያደርጋሉ፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ስም ወደ እግዚአብሔር አብ እንድንጸልይ ነው የታዘዝነው፡፡ መሰባሰባችን እንኳ በኢየሱስ ስም እንዲደረግ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ የታዘዝነው፡፡ ሙስሊሞች ግን በኢየሱስ ስም አይጸልዩም፣ የእግዚአብሔንም አባትነት አይቀበሉም፡፡ እነዚህን የሚያለያዩንን ነገሮች በመተው አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ብቻ በመስማማት ከእነርሱ ጋር የምንጸልይ ከሆነ የእነርሱን እምነት ተቀበልን ማለት ነው፡፡ ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በእጅጉ ይጣረሳል፡፡ ሙስሊሞችን መውደድ እና ከእነርሱ ጋር በመቻቻል መኖር እና ከክርስትና መስመር ወጥቶ የእነርሱን ኃይማኖት ማስተናገድ ለየቅል ናቸው፡፡ ብዙ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ግን በመቻቻል ስም ይህንን የተሳሳተ መንገድ እየተከተሉ ይገኛሉ፡፡ አንድ ሰው ይህንን የሚቃወም ከሆነ Islamophobe የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡

የድሕረ ስልጣኔ አስተሳሰብ ምን ዓይነት ችግሮችን ያስከትላል?

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የድሕረ ስልጣኔ ፍልስፍና እውነት አንጻራዊ ናት የሚል ነው፡፡ ትክክልና ትክክል ያልሆነውን ግለሰቦች በግላቸው የሚወስኑት እንጂ ፍጹም የሆነ ደረጃ ያለው እውነት የለም ይላል፡፡

  • ፍጹም የሆነ እውነት የለም የሚለው ትምህርት እውነትን ከመጥላት የመነጨ ትምህርት ነው፡፡ እውነትን መጥላት ደግሞ የክርስቶስ ተቃዋሚ ባሕርይ ነው፡- ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው።” 2ተሰ 2፡10
  • እውነት ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ንግግር እውነት ነው የምንለው ከተጨባጩ ዓለም እውነታ (Reality) ጋር የሚገጥም ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድን አገልጋይ እሁድ 3 ሰዓት ላይ በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ስለ ድህረ ስልጣኔ ትምህት ትሰጣለህ በማለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች ፕሮግራም ቢያሲዙት “ድህረ ስልጣኔ” በሚለው ርዕስ ላይ ተዘጋጅቶ እሁድ 3 ሰዓት ላይ በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን መገኘት ይጠበቅበታል፡፡ እርሱ ግን ሐሙስ 6 ሰዓት ላይ ቢመጣና “በተነጋገርነው መሰረት ስለ ጋብቻ ላስተምር መጥቻለሁ” ቢላቸው ትክክል ይሆናልን?
    • ወደ አዲስ አበባ መሄድ ብንፈልግ የሞያሌ ትኬት አንቆርጥም፡፡
    • ከሳምባ በሽታ ለመዳን የወባ መድሃኒት አንወስድም፡፡
    • ውሃ ቢጠማን ሽጉጥ አንጠጣም፡፡

ስለዚህ ፍፁም የሆነ እውነት አለ፡፡ ይህ ማለት ግን በግል ስሜት ላይ የተመሰረቱ እውነቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡

  • ሁለት ዓይነት እውነቶች አሉ፡- ግላዊ እውነት እና ፍጹማዊ እውነት (subjective and objective).
  • Subjective truth is about the subject, which means about the person who makes that claim. Objective truth is about the object, which means it depends on the object, not the subject.
  • ግላዊ እውነት ንግግሩን የሚናገረውን ሰው ስሜት እንጂ የንግግሩን ርዕሰ ጉዳይ የሚገልፅ አይደለም፡፡
    • ቡና በጨው መጠጣት ያስደስታል፡፡
    • አረንጓዴ ልብስ ያምራል፡፡
    • የሒሳብ ትምህርት ደስ ያሰኛል፡፡
    • አዲስ አበባ የምታምር ከተማ ናት፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉት ንግግሮች ግላዊ እውነቶች ናቸው፡፡

  • አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፡፡
  • ጸሐይ ከመሬት ትበልጣለች፡፡
  • ወተት ነጭ ነው፡፡
  • አንድ ሜትር መቶ ሴንቲሜትር ነው፡፡
  • ውሃ የሁለት ሃይድሮጂን እና የአንድ ኦክስጂን አተሞች ትስስር ነው፡፡

እነዚህ ደግሞ ፍፁማዊ እውነት ናቸው፡፡ ይህም ማለት ማንም ሰው ከእነዚህ አባባሎች ጋር ባይስማማ እውነት መሆናቸው ሊቀር አይችልም ማለት ነው፡፡

  • አዋሳ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፡፡
  • ኢትዮጵያ የምትገኘው በአውሮፓ ውስጥ ነው፡፡
  • ጨረቃ ከመሬት ትበልጣለች

ከላይ የተጠቀሱት ደግሞ ውሸት የሆኑ የፍፁማዊ እውነቶች ንግግሮች ናቸው፡፡ ውሸት የሆኑበት ምክንያት ከነባራዊው እውነታ ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን፦

  • ንጹሕ ሰው መግደል ትክክል አይደለም፡፡
  • ውርጃ መጥፎ ድርጊት ነው፡፡
  • ስርቆት መጥፎ ድርጊት ነው፡፡

እነዚህ አባባሎች ደግሞ የግብረገብነት (Morality) ንግግሮች ናቸው፡፡ “ፍጹም የሆነ እውነት የለም” የሚለው አባባል “ፍጹም የሆነ የግብረ ገብነት ሕግ የለም” ወደሚለው አደገኛ ድምዳሜ ስለሚመራ እነዚህ ድርጊቶች ጥሩም መጥፎም ሊባሉ አይችሉም፡፡

የድህረ ስልጣኔ አስተሳሰብ አራማጆች ግብረ ገብነት ግላዊ ነው በማለት ያስተምራሉ፡፡ “Morality is subjective.” Morals, values and ethics are determined by each person for him or herself. Therefore to tell someone else that their behavior is “wrong” or “sinful” is considered to be intolerant.

  • ግብረ ገብነት ግላዊ ከሆነ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ቢገድለው ትክክል አለመሆኑን ልንናገር የምንችለው እንዴት ነው?
  • ግብረ ገብነት ግላዊ ከሆነ አስገድዶ መድፈር ትክክል አለመሆኑን ልንናገር የምንችለው እንዴት ነው?
  • ግብረ ገብነት ግላዊ ከሆነ አልቃኢዳና አልሸባብን የመሳሰሉ ሽብርተኛ ቡድኖች እያደረጉ የሚገኙት ነገር ትክክል አለመሆኑን ልንናገር የምንችለው እንዴት ነው?
  • ግብረ ገብነት ግላዊ ከሆነ ሂትለር 5 ሚሊዮን አይሁዶችን መጨፍጨፉ ትክክል እንዳልሆነ ልንናገር የምንችለው እንዴት ነው?

በክርስትና መሰረት ግብረገብነት፣ እሴት እና ስነ ምግባር በእግዚአብሔር ተወስነው በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ደግሞ በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ የህሊና ህግ አለው፡- ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።”ሮሜ 2፡14-15

  • እግዚአብሔር ለሰው የራሱን የግብረ ገባዊነት ባሕርይ ስላካፈለው እያንዳንዱ ሰው ትክክል የሆነውን ትክክል ካልሆነው የመለየት ተፈጥሯዊ ችሎታ አለው፡፡
  • የድህረ ስልጣኔ አስተሳሰብ አራማጆች ግብረ ገብነት ግላዊ እንዳልሆነ ህሊናቸው ይመሰክርላቸዋል፡፡ ነገር ግን የድህረ ስልጣኔ አስተሳሰብ በመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ላይ የማመጽ ፍልስፍና ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 2 ላይ እንዲህ ይላል፡-

አሕዛብ ለምን ያጕረመርማሉ? ወገኖችስ ለምን ከንቱን ይናገራሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል። በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቍጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል። እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ። ትእዛዙን እናገራለሁ እግዚአብሔር አለኝ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ። ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ። አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።

  • በዚህ ዘመን ከድህረ ስልጣኔ አስተሳሰብ የተነሳ በምዕረቡ ዓለም ውስጥ ክርስቲያናዊ እሴቶች በዓለማዊ እሴቶች እየተተኩ ይገኛሉ፡፡
  • ስለ ፍጥረት ጅማሬ የሚናገረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት በዝግመተ ለውጥ መላ ምት ተተክቷል፡፡
  • ወጣቱ ትውልድ የግብረ ገብነትን አንጻራዊነት በሙሉ ልብ ስለተቀበለ ጸያፍ የሆኑ ነገሮችን ያለ ምንም መሸማቀቅ እና ያለ ከልካይ እያደረገ ይገኛል፡፡
  • የዓለም መሪዎችም ግሎባላይዜሽን የሚለውን ፍልስፍና በማራመድ ለአዲሱ ዓለም ስርኣት (New World Order) መንገድ እየጠረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ዓላማና ግብ ነው፡፡

ሦስት የማይለወጡ ነገሮች አሉ፡-

  1. እግዚአብሔር – የእግዚአብሔር ባሕርይ ስለማይለወጥ የእግዚአብሔር ቃልም ሆነ በውስጡ የሚገኙት የግብረ ገብነት ትዕዛዛት አይለወጡም፡፡
  2. የሰው ተፈጥሮ – ሰው በተፈጥሮው ክፉ እና ኃጢኣትን የመስራት ዝንባሌ ያለው ነው፡፡ ይህ ባሕሪው አይለወጥም፡፡ ምንም ያህል በቴክኖሎጂና በእውቀት ቢመጥቅም የክፋት ባህሪውን ሊለውጥ አይችልም፡፡
  3. ሰይጣን – ሰይጣን ክፉ እና የክፋት ምንጭ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ባሕሪው መቼም ቢሆን አይለወጥም፡፡

የዓለም ክፋት እየባሰ ይሄዳል፡፡ ክርስቲያኖች ግን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመኖር ዘመኑን ዋጅተው ለክርስቶስ ምጽኣት ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል!

“እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።”ኤፌ 5፡15-16

About the author

Dan

ወንድም ዳንኤል በነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሲሆን የበርካታ መጻሕፍት ተርጓሚ፣ አርታዒና ደራሲ ነው።