ትኩረት ነገረ መለኮት

የዘመናችን ‘ሐዋሪያዎች’ ኢየሱስ ክፍል አንድ

መግቢያ እና ክፍል አንድ

በApril 2016 መጀመሪያ አንድ ማታ ከጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነን በExodus TV Show (ቤተልሔም ታፈሰ) የተዘጋጀ የሐዋርያ ዘላለም (ፓዝ) ጌታቸው ተከስተን (ከዚህ በኋላ ሐዋርያ ፖዝ ወይም ፖዝ) ቃለ መጠይቅ ተመለከትን። ይህን ካየሁ በኋላ ተቀምጬ አስተያየታዊ ምላሽ ብቻ እንጂ ጥልቅ ምርመራ ያልተደረገበት የምካቴ እምነት ሥራ ያልሆነ አጭር መጣጥፍ መጻፍ ጀመርኩ። አጭሯን የሦስት ገጽ ሥራ ከጨረስኩ በኋላ ነው ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን በመገንዘብ በመጠኑ ሰፋ ያደረግሁት። በቃለ መጠይቁ ውስጥ ተጠያቂው ገሃድ ያደረጋቸው ጉልህ የስሕተት ትምህርቶች በቀላሉ መታየት የሌለባቸው መሆናቸውን ራሳቸው የሚገልጡ ናቸው። ይህ በመሆኑም ወደፊት ሌሎችም ሊመልሱት የተገባ ነው።  ጋዜጠኛዋ ከዚያ ያለፉ ገታሪና ተገዳዳሪ ጥያቄዎች እንድታቀርብ ብጠብቅም ከመሰናዶዋና ምናልባት ከአቅሟ አንጻር ማለፊያ ሥራ መሥራቷን አደንቃለሁ። አንድዳንዶቹ ጥያቄዎች ያላሰበችባቸውና ምናልባት ያልተዘጋጀችባቸው በመሆናቸው የተጠያቂውን መልሶች በአጸፋ መመከት እስከማትችል አክብደውባታል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ኃይለኛ ጥያቄ ተኩሳ ባሩድ አሽትቶ ሌላኛው እስኪተኩስ አድፍጣ የምትጠብቅ ትመስላለች። የማንነት መገኛ የሆኑትን የመጀመሪያ የሕይወት ታሪኮች እና ዳራ ጨርሶ አልነካችም። ከስነ ልቡናዊ ዝግጅት ባለፈ በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ስነ መለኮታዊ ዝግጅት አድርጋለች፤ ግን ተጠያቂው ከዐውድ የወጡ ጥቅሶችን እንደ ዶቃ ሲደረድር ወደ መስመር የሚያስገባ ከዝግጅቷም ያለፈ ዝግጅት መኖር ነበረበት። እንዲያም ሆኖ፥ መልካም ጅማሬና የተረጋጋ አረማመድ ነው ብዬ ማበረታታት እፈልጋለሁ። ምናልባት ጋዜጠኛዋ አወያይ (moderator) ሆና አንጻራዊ ጥያቄና ምላሽ ላይ ተሳታፊ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስነ መለኮት ላይ የቆመ ሰው አብራ ብታቀርብ መልካም ነበር። መጨረሻ ላይ ተስፋ ሰጥታለችና ይህ ወደፊት ይደረጋል። በጠቅላላው ድንቅ የቃለ ምልልስ ዝግጅት ነው። ከዝግጅቱ ጋር በተያያዥነት ለመጨመር፥ ጽሑፉን ከጨረስኩ በኋላ በExodus TV Show ያልተካተተ ክፍል ስላለ ያንን እንድመለከት ተነገረኝና ከተጠያቂው በኩል የተለጠፈውን ሁለት ቀዳሚ ክፍሎች አግኝቼ ተመለከትኳቸው። ሁለቱ ክፍሎች ጉልህ የሆኑ ልምምዳዊ አሳቦችን እንጂ ብዙም አስተምህሮታዊ ይዘት ስለሌላቸው፥ እንዲሁም በኢየሱስ ማንነት ላይ በተነገሩት ነገሮች ላይ ለውጥ የማይፈጥሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በእርግጥም የExodus TV Show የጀመረው ከ3ኛው በመሆኑ ከፊት የተቆረጠ ክፍል እንደነበረው በግልጽ ይታያል። ይህ የቪድዮ ዝግጅቱን በተመለከተ ነው።

በሰዎች ትምህርት ላይ ስጽፍ ልማዴ እንደመሆኑ የማደርገው ጽሑፉ ሳይታተምና ሳይበተን ለሚመለከተው ሰው መላክ ነው። ይህንን ጽሑፍም በሐዋርያ ፖዝ አገልግሎት ድረ ገጽ ላይ በሚገኘው የኢሜይል የመገናኛ አድራሻ እንዲሁም በሌላ ሊወክለው በሚችል አንድ ሰው በኩል April 10 ልኬአለሁ። ይህንን ለሚመለከታቸው የመላክ ተግባር የማደርገው ለአስተያየትና ለምላሽ ነው። ይህ የግል አሳብን ለመግለጥ ዕድል ለመክፈት እና የተጻፈው፥ የተነገረው፥ ወይም የተሰጠው ትምህርት እዚህ እንደቀረበው መሆን አለመሆኑ አይተው እንዲነቅሱ ወይም ምላሽ እንዲሰጡ ለማበረታታት ነው። ከፖዝም ከሌላው ሰውም እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም።

በዚህ ጽሑፍ የማቀርበው ባገጠጡት ስሕተቶች፥ በተለይም አስተምህሮታዊ በሆኑቱና በኢየሱስ ማንነት ላይ በተቃጡቱ ላይ ብቻ ነው።[1] ብዙ ጊዜ በስህተት ትምህርቶች ወይም በስሕተት አስተማሪዎች ላይ ስጽፍ የምጠይቃቸው ሦስት ጥያቄዎች አሉ። በነዚህ ጥያቄዎች ላይ የማገኘው መልስ ‘አዎን’ ሆኖ የሚያስጽፍ ነገር ከኖረ ብቻ ነው የምጽፈው። እነዚህ ጥያቄዎች፥

  1. ይህ ትምህርት ወይም ይህ ጉዳይ ከቅዱስ ቃሉ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጻረራል?
  2. ጌታ ክርስቶስን ከክብሩ ያወርደዋል?
  3. ይህ እንድጽፍበት ያደረገኝ ትምህርት የቅዱሳንን እምነት ያፈርሳል?

በዚህ መጣጥፍ ፖዝ ስለ ኢየሱስ የተናገራቸው ስሕተቶች ወይም የስሕተት ትምህርቶች ከላይ ያልኳቸውን ሦስት መስፈርቶች በትክክል ያሟላሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጻረራሉ፤ ክርስቶስን ያዋርዳሉ፤ የቅዱሣንን እምነት ያፈርሳሉ። ስለዚህ ነው የምጽፈው።  በቃለ መጠይቁ ውስጥ ይህ ሰው ኢየሱስን አራት ነገሮች አድርጎ አሳይቶአል። እነዚህ አራት ነገሮች፥

  1. ፖዝ አድራጊ/አስደራጊ (ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ)፤
  2. የሰየጠነው/ሰይጣን የሆነው (ሰይጣኑ ኢየሱስ)፤
  3. ሰው ብቻ/ሰው ብቻው (ሰውየው ኢየሱስ)፤ ታጃቢ (ታጃቢው ኢየሱስ)።  በቃለ መጠይቁ ውስጥ ብዙ ዝባዝንኬ የሆኑ ልምምዳዊ ጉዳዮች ቢነሡም የሚያስጽፉኝ ጉዳዮች ላይ ያነሳኋቸውን መስፈርት የማያሟሉ በመሆናቸው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በነዚህ አራት ነጥቦች ላይ ብቻ አተኩራለሁ። አራተኛውና የመጨረሻው ርእስ የታይታ ጥማትን አመላካች እንጂ አስተምህሮታዊ ጥንካሬ ወይም ጥቅምና ጉዳት የለውምና ልተወው ነበር። ሆኖም ግን ኢየሱስ በምሳሌነትና በሞዴልነት የተነገረበት ስሕተት ስለሆነ በመጨረሻ ላነሣው ሆኗል። ሌሎቹ ሦስቱ ነጥቦችም ቢሆኑ ቃለ መጠይቁን በሚመጥን በመጠነኛ ጥልቀት እንጂ እጅግ ጠልቄ አልጻፍኩበትም። ይህን ስል በራሱ ትምህርት ላይ ብቻ ምላሽ ለመስጠት ያህል ጻፍኩ እንጂ፥ ለምሳሌ ከእርሱ በፊት ስለነዚህ ስሕተቶች የተናገሩትን እና የጻፉትን ሰዎች ከማመልከት ብዙም ያለፈ አላደረግሁም። ለምሳሌ፥ ኢየሱስ ሰየጠነ የሚሉ  እና ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበረ የሚሉ ሌሎች ከፖዝ በፊት ኖረው ያውቃሉ። እነዚህን እዚህ ጽሑፍ ውስጥ በምልከታ ደረጃ ብቻ ነው በመጠኑ ያነሣሁት። ትኩረቴ ራሱ ፖዝ የተናገረው እና የቃሉ ምላሽ ነው።

እንደ መግቢያ ግን አንድ ጥያቄ መጣልና ከዚያ መንደርደር እሻለሁ። ያም፥ ‘እነዚህ እንደ ፖዝ ያሉት ሰዎች የሚናገሩት ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ነው ወይስ እነርሱ የፈጠሩት ኢየሱስ?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢና የመልሳችን መዝገብ ወደሚገኝበት ወደ ቃሉ እንድንሄድ የሚያደርገን ጥያቄ ነው። ዛሬ የምንሰማው ሐሰተኞች አስተማሪዎች የሚሰብኩን ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ሳይሆን በምናባቸው የፈጠሩት ወይም ሰይጣን ፈጥሮ ያቀበላቸው ሌላ ኢየሱስ ነው። በዚህ ሰው ትምህርቶች ውስጥ የምናገኘው ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ቆሮ. 11፥4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። ያለው ያኔም አሁንም እውነት ነው። ሌላ ኢየሱስ፥ ልዩ መንፈስ፥ ልዩ ወንጌል። ይህ ታዲያ የሚታገሡት ትምህርት መሆን የለበትም።

  1. ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ?

ፖዝ ከሚለው ቃል ልጀምር። ሐዋርያ ዘላለም የቅጽል ስሙ ፖዝ (pause) መሆኑን ይናገራል። Pause የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ቋንቋ በዘመናት የሚወለድና እየኖረ የሚያድግ ኖሮም ሊሞት የሚችል የመግባቢያ መሣሪያ ነው። አማርኛ ከግዕዝ አብራክ እንደወጣ፥ እንግሊዝኛ ላቲንንም (ሮማይስጥን) ጨምሮ ከተለያዩ ቋንቋዎች አብራክ የወጣ ነው። Pause ከሮማይስጥ የተወሰደ የእንግሊዝኛ ቃል ነው። አንድን ነገር ለዘለቄታው ሳይሆን ለጊዜው ማቆም ማለት ነው። ልክ በሙዚቃ ወይም መዝሙር ማጫወቻ መዝሙር ሲዘመር ቆይቶ ለጊዜው አቁሞ ኋላ እንዲቀጥል እንደሚደረገው ማለት ነው። ወይም አንድ መኪና ኬላ ላይ ቆም ብሎ ተፈትሾ ጉዞውን እንዲቀጥል ሲደረግ ማለት ነው። ሐዋርያ ፖዝ ስሙ ለምን ፖዝ እንደተባለ በቃለ መጠይቁ ሲናገር፥

እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የድህነትን፥ የኃጢአትን፥ የሞትን፥ የበሽታን አካሄድ ፖዝ አርጓል፤ አቁሟቸዋል። እነዚህ ነገሮች በሰው ሕይወት ውስጥ ፍሰታቸው ተከልክሏል። እኛ ግን እሱን ፓርት አናይም። የቆሙት በመስቀል ነው። ልክ ይኼ የቆሙትን ነገሮች ከዚህ ትውልድ ላይ ታቆምልኛለህ፤ አሁን በማስተምርሽ ትምህርት፥ በሚገባሽ እውቀት፥ ይህንን የጨለማ ፍሰት፥ ታቆምልኛለህ አለኝ ማለት ነው። . . . ፖዝ ታረግልኛለህ ሲል ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ  ታደርጋለህ፤ ባይ ዘ ዌይ፥ ፖዝ ማለት የቃሉ ፍቺ፥ ማቆም ማለት ነው።

. . . ፖዝ ማለት ፍቺውን ልንገርሽ፤ ፖዝ ማለት ጳውሎስ ማለት ነው። ሌላ ፍቺ የለውም። ጌታ ያለኝ በቀጥታ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? በዚህ ትውልድ መሐል ለኔ ጳውሎስ ነህ ነው ያለኝ። እኔ ጳውሎስ የሚለውን ቃል ትርጉሙን ወሰድኩኝና ጳውሎስ የሚለው ፊደል የግሪክ ቃል ላይ ሄጄ ሳጠናው የመጀመሪያው ላይ እመጀመሪያው ወርድ ማለት ነው፤ ሊትል ማለት ነው፤ ሩት ኦሪጂናል ኤግዞስቲቭ ኮንኮርዳንስ ሚባል አለ ግሪክና ሂብሩ ያለው፤ ሩት ወርዱ ላይ ሄጄ ስመለከተው ሩት ወርዱ ምን ይላል? ፖዝ ይላል። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጳውሎስ የተባለው የትጋ እንደሆነ ታውቂያለሽ? ምን አርጎ ጳውሎስ እንደተባለ ታውቂያለሽ? [ሐዋ. 13፥8-11 ከተነበበ በኋላ] . . . እስከ ጊዜው ፀሐይን አታይም አለው። በሌላ አማርኛ ሰውየውን ምን አረገው? ፖዝ አረገው። ጳውሎስ ፖዝ ነው። ጳውሎስ ማለት ፖዝ ማለት ነው።”

ይህች ናት ትርጎማ! ከስሙ ትርጉም ብንነሣ ለማለት እንጂ ልናገር የምወደው በኢየሱስ ማንነት ላይ ነው። ግን ስሙ ፖዝ ከፖዝ አስደራጊው ጋርም ስለሚገናኝና ‘ፖዝ ታረግልኛለህ’ ባዩ ኢየሱስ ስለሆነ ነው የማነሣው እንጂ እንዲህ ያለ የፌዝ፥ የቀለለና ወራዳ አተረጓጎም ሊጻፍበትም የተገባው እንኳ አልነበረም። ይህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችንም ያላሉትን እንዲል እያደረገ ሊፈታ የሚሞክረው በዚህ መንገድ መሆኑን ዝቅ ስንል እናየዋለን። ጳውሎስ Παῦλος የግሪክ ሳይሆን የሮማይስጥ ቃል ነው። ስም ሳይሆንም ቅጽል ነው፤ እንዳለውም ትርጉሙ ትንሽ፥ ታናሽ ማለት ነው። ከቃል በታች ያሉ ንዑሳን የቃል ቁርጥራጮችን ከፈለግን ፖዝንም ጨምሮ ሌላ ሌላ ትርጉምም ልናገኝ እንችላለን። ግስ እንደ ቃል መሠረት ስለሚታይ፥ ስም ወይም ቅጽል በተጻፈባቸው ስፍራዎች ትርጉም ፍለጋ ከግስ ጋር እንዲገናኝ ይገደዳል። ‘ይህ፥ ትንሽ የሚባለው ቅጽል ከምን ግስ ጋር ይቀራረባል?’ የሚለው ጥያቄ ለቅጽበት ወይም ለትንሽ ጊዜ ማቆም (παύω ፓዎ) ከሚለው ጋር ያቆራኘዋል። ይህ እንግዲህ ቅጽሉን (ትንሽ የሚለውን) ከግስ ጋር ለማቆራኘት የተሄደ አፈታት ነው እንጂ የጳውሎስ ጳውሎስነት ከቅጽበት ጋር የሚገናኝ ስለሆነ አይደለም።  ጳውሎስ የሚለው የጳውሎስ ስም በዚያ ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቀሰ እንጂ ሳውል ጳውሎስ የተባለው ቀድሞም ነበረ። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን የሚለው ሐረግ የሚነግረን ስሙ ቀድሞውኑ ጳውሎስ መሆኑን እንጂ ሰዎች ተሰብስበው የዳቦ ስም ሲያወጡለት አይደለም። የፌዝ አተረጓጎም ያልኩት ስለዚህ ነው። እዚያ ድረስ ሳይኬድ ግን ጳውሎስ ለቅጽበት ወይም ለጊዜው ወይም ለትንሽ ጊዜ ማቆም ማለት ሳይሆን፥ ከዚያም ጋር የሚገናኝ ሳይሆን እንዲያው ትንሽ ማለት ብቻ ነው።

‘ጳውሎስ ማለት ፖዝ ነው፤ ወይም ለጊዜው ማቆም ነው’ ከተባለማ፥ ‘ምስጉን ማለት መሰገ ከሚለው ግስ ስለወጣ መመሰግ ማለት ነዋ!’ እንደማለት ነው። ግን ነው? አይደለም። የፖል እና ፖዝ ግንኙነት ልክ እንደዚያ ነው ለማለት ይቻላል። ጳውሎስ ከዚያ በፊት ሳውል እንደነበረ እናውቃለን እንጂ ለምን ጳውሎስ እንደተባለ አልተጻፈልንም። ሳውል (שָאׁוּלּ ሻኡውል) የዕብራይስጥ ቃል ሆኖ መጠየቅ፥ የራስ ማድረግ፥ የኔ ነው፥ ይገባኛል፥ መብቴ ነው ማለት ነው። የጳውሎስ የሮማይስጥ ስም እና የግሪክ አጻጻፍ ሳውሎስ እና ጳውሎስ (Σαῦλος እና Παῦλος) እንደ ግጥም ቤት የሚመታ አጠራር ነው። ምናልባት ጳውሎስ ከአጠራሩ መመሳሰል ጋር አብሮ ከመብተኝነት ይልቅ ትንሽነትንና ትሕትናን የሚያመለክት ስም መምረጡ የማንነት መታወቂያ ቅየራ ይመስላል እንጂ የነገሮች ኬላ ወይም አስቆሚ የመሆኑ ገላጭ አይደለም። ይህን ስላደረገ (የጠንቋዩ በርያሱስ ወይም ኤልማስ እስከ ጊዜው ዕውር ስለሆነ) ፖዝ ተባለ ካልንማ ጳውሎስ ሺህ ነገር ስላደረገ ሺህ ስም ሊኖረው ነዋ! ደህና፤ ይህ በርያሱስ ዕውር የሆነበት ‘እስከጊዜው’ የተባለው ቃልስ ፖዝ ከሚለው ቃል ጋር ይዛመድ እንደሆነ ብለን ብንመረምር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸውም እናያለን። እስከ ጊዜው ማለት ፖዝ ማድረግ ከሆነ፥ እስከጊዜው ἄχρι καιροῦ አክሪ ካይሩ እና ለጊዜው ማስቆም παύω ፓዎ መመሳሰል ነበረባቸው፤ ግን እንኳን ሊመሳሰሉ ተያይተውም የማያውቁ ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሆድና ጀርባ ናቸው። ግሪኩን ትተን ከላይ የጻፍኩትን አማርኛ ብቻ የሚያነብብም ያስተውለዋል። ፖዝ የፌዝ ብቻ ሳይሆን የተምታቱ፥ የተዘባረቁና የተደናገሩ አፈታቶችን በማቅረብ እየተካነ መጥቶአል። ይህን በመጀመሪያ ያስተዋልኩት፥ ዝብርቅርቁ ዓለም በተባለች መጽሐፊት ነው። የመጽሐፊቷ ይዘት እንደ ርእሱ ዝብርቅርቅ ነው። ከዚያ በኋላ ተሻሽሎ ታትሞ እንደሆነ አላውቅም እንጂ የመጀመሪያው እትም እራስና እግሩን ለመለየት የሚያስቸግር ከአማኑኤል ሆስፒታል ማተሚያ ቤት የወጣ የሚመስል መጽሐፍ መሆኑን ያነበቡ ሊታዘቡት ይችላሉ። እዚህ የሚታየውም ከዚያ የባሰ የተደናገረና የሚያደናግር አፈታት ነው። ሌላው በዚህ ሰው አነባበብ እና አፈታት ውስጥ የሚታየው ጥቅሶችን በሚጠቅስበት ጊዜ የሚፈልገውን ስለሚሉ ብቻ እንጂ ዐውድ የሚባል ነገር ስለመኖሩም ግድ የሚሰኝ አይመስልም። ምንም የመጽሐፍ ቅዱስና የስነ መለኮት ትምህርት ዳራ ከሌለው ሰው ስለ ዐውድና ዳራ መጠበቅም አይቻልም። በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይም ያስተዋልኩት ይህንን ዐውድ-ዘለልነት ነው። ጥቅስን ከስፍራው ፈንቅሎ ከጥቅሱ ውስጥ ቃልን ብቻ ወስዶ መፍታት የስሕተት ትምህርቶች ዋና መታወቂያ ነው። ዋና መታወቂያ። የፖዝ ፍቺ የዚህ ጉልህ ምስክር ነው። ጳውሎስ ማለት ፖዝ ነው፤ ፖዝ ማለት እኔ ነኝ፤ በሽታ፥ ድህነት፥ ሞት፥ ኃጢአት ፖዝ ተደርገዋል ማለት ከፌዝ ያለፈ ጎጂ አፈታት ነው። ይህ ከዐውድ ውስጥ ጥቅስን ፈንቅሎ፥ ከጥቅስ ውስጥ ደግሞ ቃልን ነቅሎ አውጥቶ ማውለብለብ ቃሉን ለማያጠኑ ሰዎች ዕጹብ ድንቅ አፈታት መስሎ ሊታይ ይችላል። ግን የስሕተት አስተማሪዎች ባንዲራ ነው። እንድንጠነቀቅ የሚያደርገን ማስጠንቀቂያም ነው። ጳውሎስ ማለት ፖዝ ማለት ነው፤ እኔ ጳውሎስ ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ፖዝ አድራጊ ነኝ ማለት ከአፈታትና አገነዛዘብ ደንብ የተፋለሰ ብቻ ሳይሆን ብልሹ አፈታት ነው። ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውስጥ አለማለፉን በግልጥ እየተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች እየከፈተ የሚያስተምር መሆኑ እንዲህ ያሉ ብልሹና ጠማማ ፍቺዎችና አጣማሚ ፈቺዎች እየተባዙ የመምጣታቸውን መንገድ ቀያሽ መሆኑንም የሚያሳይ ነው። ዕውራን መሪዎችን የሚያሰለጥኑ ዕውራን አሰልጣኞች ማለት ይህ ነው። በእውነቱ በጸሎትም በትምህርትም ፖዝ መደረግ ያለበት ይህኛው ብልሹ አካሄድ ነው። ፖዝ ማድረግ ማቆም ከሆነ፥ ኢየሱስ እነዚያን አምስት ነገሮች (ድኅነትን፥ ኃጢአትን፥ ሞትን፥ በሽታን፥ ጨለማን) አቁምልኝ ብሎታል ማለት ነው።  Pause ማድረግ ከላይ እንዳልኩት ለዘለቄታ ሳይሆን ለጊዜው ማቆም፥ ወይም ቆም ማድረግ ነው። ኬላ ወይም የመንገድ መብራት ላይ ተሽከርካሪዎች ለትንሽ ጊዜ ቆም ብለው እንደሚቀጥሉት፥ እንደሚሄዱት እነዚህ ነገሮች አንድ ቀን እንደሚቀጥሉ ሆነው ለጊዜው ነው ልጓማቸው የተያዘው ማለት ነው? ከፖዝ ትርጉም ጋር ካቆራኘነው ይመስላል። ከልጆቻችን ጋር ሆነን በመኪና ወደ አንድ ቦታ ስንሄድ የምንሰማው መዝሙር ወይም የክርስቲያን ሬድዮ ጣቢያ ነው። ወሬ ስናወራ መዝሙሩን አቆመዋለሁ። ወሬያችንን ስንጨርስ፥ unpause አድርገው ይሉኛል። ከቆመበት ይቀጥል ማለታቸው ነው።  ፖዝ ለጊዜው ማቆም ከሆነ አንድ ቀን unpause ይደረጋል ማለት ነው? እነዚህን ነገሮች (ኃጢአት፥ ድኅነት፥ በሽታ፥ ጨለማ፥ ሞት) እንዳስቆማቸው ይቀራሉ ወይስ አንድ ቀን ከቆሙበት ይቀጥላሉ? የተደረጉት pause ከሆነ ይቀጥላሉ ማለት ነው። ምክንያቱም እስከወዲያኛው እንዳይቀጥሉ ከተፈለገ መደረግ ያለበት ፖዝ ሳይሆን ጨርሶ ማስቆም ወይም ማቆም ነው። ለፖዝ የተናገረው ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከዚህ ትውልድ ላይ ፖዝ ታደርግልኛለህ ሲለው፥ ያንን ያለውን ‘ኢየሱስ’ እስከመቼ መሆኑን ጠይቆ ይሆን? ያስቆመው እርሱ ከሆነ የሚያስቀጥለውም እርሱ ነው ማለት ይሆን? ወይስ እንዲቀጥሉ ካልፈለገ እርሱ እስከፈለገ ድረስ ሊያስቆማቸው ይችላል ማለት ነው? ይህ ከሆነ ይህን የማድረግ ሥልጣን በእጁ ነዋ!?

ለመሆኑስ እነዚህ ነገሮች እውነት ፖዝ ተደርገዋል? ቆመዋል? ይህ የጠማማና የተዘበራረቀ አተረጓጎም ችግር ነው እንጂ ፖዝ እነዚህን ነገሮች ፖዝ አላደረጋቸውም። ኦርጂናሌው የክርስቶስ ሐዋርያ ጳውሎስም ቀጥ አላደረጋቸውም። የሚደንቀው ነገር፥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ ፖዝ አላደረጋቸውም። እነዚህ ነገሮች (ድኅነት፥ ኃጢአት፥ ሞት፥ በሽታ፥ ጨለማ) አልቆሙም። የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በሥጋ የተገለጠው ታላቁ ጌታ ያላቆመውን ዘበናዩ ሐዋርያ ፖዝ እስኪወለድና እስኪያድግ፥ አገልግሎት እስኪጀምርና እነዚህን መርገሞች በእርሱ ‘ሪሞት ኮንትሮል’ ጠቅ አድርጎ ቀጥ እስኪያደርጋቸው ድረስ ሲፈስሱ መኖራቸውና አሁን ቀጥ ወይም ለጊዜው ቆም ማለታቸው ይህን ሰው የላቀና ልዩ አያደርገውም? የላቀ ልዩ ሰው የመሆን ጥማት አስቀያሚ አባዜ ነው።

እግዚአብሔር የአገርን ወይም የዓለምን ሁሉ ችግር ፈቺ የሆነ አንድ ሰው ሾሞ አያውቅም። ሰሎሞንም፥ ዳዊትም፥ አዳምም ጳውሎስም ለዚህ አቻ የለሽ ተግባር አልተሾሙም። ዛሬም ያ ሰው ሐዋርያ ፖዝ ሊሆን አይችልም። ነገም፥ ክርስቶስ ዳግም እስኪመጣም በክርስቶስ የሚሾም ሰው የለም። ቃሉ ይህንን አይልም። ስለራሳቸው የገዘፈ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በስነ ልቡና ጠበብት pathological egotist ወይም megalomaniacal ይባላሉ። ይህ እዚህ የምናየው አመለካከት ያንን ይመስላል። የትውልድ ታዳጊ እንደሆኑ ራስን መቁጠር የታዳጊነት ወይም የቤዛነት አባዜ ነው። Messiah complex ይሉታል። ይህ ራስን ክርስቶስን የማስመሰል፥ ሥልጣንን የመከናነብ፥ ራስን ቤዛ የማድረግም ጭምር ከጤናማነት የራቀ አመለካከት ነው። ቤዛችን አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ። ፖዝ እንደሚነግረን፥ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የድህነትን፥ የኃጢአትን፥ የሞትን፥ የበሽታን አካሄድ ፖዝ አርጓል፤ አቁሟቸዋል። እነዚህ ነገሮች በሰው ሕይወት ውስጥ ፍሰታቸው ተከልክሏል።”  ግን እውነት ተከልክሏል? አንዱና ብቸኛው ንጉሥ ኢየሱስም በመስቀሉ ላይ ስለ እኛ ተውላጣዊ ሞታችንን ሞቶ፥ ኃጢአታችንን ተቀብሎ ከአብ ጋር አስታረቀን እንጂ ኃጢአትን፥ ድህነትን፥ ሞትን፥ በሽታን፥ የጨለማ ፍሰትን ከዓለም ላይ አላጠፋም። ይህ ቢሆንማ ቀድሞውኑ ቆመዋልና አንድ ዘበናይ ‘ሐዋርያ’ እስኪነሣና ራሱን እስኪሾም ድረስ 2 ሺህ ዓመታት መጠበቅ የለበትም። ከተነሣና ከተሾመስ ወዲህ ምነው እነዚህ ነገሮች ሁሉ እየፈሰሱ አሉ? ፖዝ እኮ አልተደረጉም! ገናም ጌታ ክርስቶስ ዳግም እስኪመጣና እስኪወስደን ድረስ በጋና ክረምት እንደሚኖሩ እነዚህ ነገሮችም መኖራቸው ይቀጥላል። ፖዝ አስደራጊው የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱሱ ጌታና መድኃኒት ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ከምድር ላይ እንደሚወገዱ ወይም ተይዘው እንደሚቆዩ፥ ጠቅ ተደርገው ቀጥ እንደሚሉ አልተናገረም። በምድር ሳለን መከራ እንዳለብን ነው ያስተማረን። ይህ ሥጋ እስከሚዋጅበት ጊዜ ድረስ በዚህ ሥጋ እስከኖርን ድረስ የውድቀት መዘዞች፥ ጠንቆችና ውጤቶች ይፈራረቁበታል።  በሽታና ሞት በፖዝ ፖዝ አልተደረጉም፤ ልንታመም እንችላለን፤ ጌታ መጥቶ ካልተነጠቅን በቀር እያንዳንዳችንም በየተራችን እንሞታለን። በጸጋውና በምሕረቱ ብቻ ከበሽታ ብንጠበቅም እንኳ ሞትን ግን እንሞታታለን እንጂ ሞት ፖዝ አልተደረገም። ኃጢአትስ? እንኳን ያልዳኑ ፍጥረታውያን ይቅሩና በበጉ ደም የተዋጀን እኛም በየዕለት ኑሮአችን እየወደቅን የምንነሣ ነን እንጂ ፍጹማን አይደለንም። ፖዝም አይደለም። ቃሉ ወደ ፍጽምና እንደምናድግ እንጂ ፍጹማን እንደሆንን አያስተምርም።

ድኅነትስ? ዛሬ የየዋህ ክርስቲያኖችን ገንዘብ እየመዘመዙ እንደ እንጉዳይ ወይም እንደ ዮናስ ቅል በአንድ ሌሊት ባለጠጋ የሆኑ የዘመናችን ሐዋርያትና ነቢያት ቁጥር ብዙ ነው። እነዚህ ድኅነት እንዳሻራቸው መናገር ይችሉ ይሆናል፤ ጌታ እንዳበለጸጋቸውም በመናገር ሊሸነግሉ ይሞክሩ ይሆናል፤ ግን ይህንን ሽንገላ የሚሉት በንጹሕ ኅሊና ሊሆን አይችልም። ሽንገላ ንጽሕና የለበትም። ተደጋግሞ የተረጋገጠው እውነት እነዚህ ሰብኮ አደሮች በአንድ ጨረቃ ከበርቴ ሲሆኑ የሚያገለግሏቸው ሰዎች ግን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወርዱ መሆናቸው ነው።  የጨለማ ፍሰትስ? ጨለማውም የንጋቱ ኮከብ ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ ይቀጥላል። ዓለማችን ከትናንቱ ዛሬ ብሩኅ እየሆነች ሊመስለን ይችላል፤ ግን አይደለችም። ይህንን ፖዝ የማድረግ ነገር እንዲያብራራ ተጠይቆ ሲያብራራ ይህን የሚያደርገው በቃል፥ በስብከት መሆኑን ተናገረ፤ ይህ ደግሞ ሌሎች ከሚሰብኩት ቃል ልዩ የሆነው በምን መሆኑ ከቶም አልተነገረም። የቀደሙትን ሰባኪዎች ለማጥላላት ግን ብዙ ብሎአል። ለምሳሌ፥ “ኢዮብን የሚሰብኩ አሉ፤ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ እያሉ። አሁን እስኪ፥ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ይሰጣል እንጂ ይነሳል?” ሲል ጋዜጠኛዋን ይጠይቃታል። ፖዝ የሚሰብከው እግዚአብሔር መስጠት ብቻ እንጂ ለመንሳት እንዳይችል የተደረገ ሰው ፈጠር፥ ሰው ሠራሽ አምላክ ነው ማለት ነው። የጌታ ሐዋርያ ጳውሎስ መብዛትንና መጉደልን የማያውቅ ሰው ነበር? አልነበረም። ፖዝ፥ “ከመዝሙረ ዳዊት የሚጠቀሱ ጥቅሶች አሁን ኢየሱስን ያሳያሉ? አያሳዩም፤ መዝሙረ ዳዊትን ነው የሚያሳዩት። መዝሙረ ዳዊትን የሚያሳይ ነገር እኔ ማሳየት አልፈልግም፤ ኢዮብን የሚያሳይ ነገር ማሳየት አልፈልግም” እያለ በቃሉ ላይ ሲዘብት ቅንጣት ታህል ፍርሃት አይታይበትም። አለማወቅ የሚያከናንበው ድፍረት ከወኔ ይልቅ ያዳፍራል። ፖዝ ኢየሱስን ብቻ ማሳየት እንደሚሻ ይነግረናል። የሚያስፈራው ነገር ግን የሚያሳየን ኢየሱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚነግረን ሌላ ኢየሱስ መሆኑ ነው።

“ኃጢአት፥ ድህነት፥ በሽታ፥ ሞት የሰይጣን መገለጫ ናቸው” ሲል ክርስቲያኖች ከነዚህ ነገሮች የጸዱ ሊሆኑ ይገባል ማለት ነው። ከሞትም ጭምር። ከሞቱ መቼም ሙት ወቃሽ ስለማይኖር አይከሰሱም እንጂ ‘ክርስቲያን መሞት የለበትም’ የሚል ቅጥፈት የሚሰብኩም ደርዘን ሙሉ አሉን። ጌታ ክርስቶስ ዳግም እስኪመጣ ድረስ ይህች ምድር ምን እንደምትመስል መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ግልጽ አድርጎ ይነግረናል። ከነዚህ ግልጽ ነገሮች ውስጥ ግን ኃጢአት፥ ድህነት፥ ሞት፥ በሽታና፥ የጨለማ ፍሰት pause እንደሚደረጉ በአንድም ስፍራ አይናገርም። ፖዝ pause እንዳደርግ ነገረኝ የሚለው ኢየሱስ ማን መሆኑ መጠየቅ ያለበት ትልቅ ጥያቄ ነው። በመስቀል ላይ የሞተልን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ እንዲህ የመሰለ ቅሌታም ሹመትና ፌዘኛ ሹም የሚሾም ንጉሥ አይደለም። ታዲያ፥ እንዲህ ያለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ pause አድራጊ ሹም የሚሾም ማን ሊሆን ይችላል? መልሱ ግልጽ ነው። በኢየሱስ የሚመሰል ሰይጣን በሥራ ላይ መሆኑን የረሳንበት ቀን ትጥቃችን የተፈታበት ቀን ነው። ኢየሱስን በማንነቱ ለማወቅ ደግሞ ‘ታየኝ፥ ተናገረኝ፥ ተገለጠና ይህን አለኝ፥ ላከኝ፥ ሾመኝ፥ ቀባኝ፥ ሌላም ሌላም’ የሚሉንን ሰዎች ሳይሆን በቃሉ ውስጥ ራሱን የገለጠውን፥ የተጻፈውን ያንን ጌታ ነው መስማት ያለብን። ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ጋር ያለን ግንኙነት እንደ ደባል በልክና በድርበብ የሆነ ጓደኝነት ብቻ ከሆነ በተገመዱ ጥቅሶችና ‘መገለጥ’ በሚሉት ነገር በቀላሉ ልንታለልና ልንወሰድ እንችላለን። ያንን ኢየሱስ ካላወቅነው በሐሰተኛ ኢየሱሶች እንደ ዘበት ተጎትተን ልንወሰድ እንችላለን። እንደገና ከላይ የጠቀስኩትን ቃል ልድገም፤ የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። 2ቆሮ. 11፥4። ይህ ሐዋርያ የሚያስተዋውቀን ኢየሱስ ድህነትን፥ ኃጢአትን፥ ሞትን፥ በሽታንና ጨለማን ፖዝ የሚያስደርግ ብቻ ሳይሆን የሰይጣን ባሕርይ የተላበሰ ኢየሱስም ጭምር ነው። እንየው።

ይቀጥላል

[1] የቪድዮ ቃለ መጠይቁን ከዚህ ምንጭ ማየት ይቻላል፤ https://www.youtube.com/watch?v=vXh_XvSeR8o። በአራት መሰናዶዎች የተሰራጨ ሲሆን ቀጣዮቹን ክፍሎች ክፍል አንድ ሲከፈት ያገኙታል። ያልተካተቱትን ሁለት ክፍሎች ደግሞ ከ https://www.youtube.com/watch?v=r2RZ2A2nBSQ ላይ በመሄድ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎች ያገኙታል።

Zelalem Mengistu
Follow me

Zelalem Mengistu

ወንድማችን ዘላለም መንግሥቱ ጌታን ላለፉት 30 ዓመታት ሲከተል በወንጌላዊነትና በመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪነት ሲያገለግል የቆየ ወንድም ነው። አሁን ከቤተ ሰቡ ጋር በብሩክስ አልበርታ፥ ካናዳ እየኖረ በመጋቢነት ያገለግላል። የስሕተት ትምህርቶችና ልምምዶችን መፋለምና መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር ደስታው ነው።
Zelalem Mengistu
Follow me

About the author

Zelalem Mengistu

Leave a Comment